በሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ትራምፕን በመቃወም አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የወሰዷቸውን እርምጃዎች በመቃወም ቅዳሜ ዕለት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች አደባባይ ወጥተዋል።
ራሳቸውን "50501" በማለት የሚጠሩት ሠልፈኞቹ አደባባይ የወጡት የአሜሪካ አብዮታዊ ጦርነት የተጀመረበትን 250ኛውን በዓል ታሳቢ በማድረግ ነው።
ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ "50 ተቃውሞዎች፣ 50 ግዛቶች፣ 1 ንቅናቄ" የሚለውን ለመግለጽ "50501" በማለት ራሳቸውን ይጠራሉ።
ከዋይት ሐውስ፣ከቴስላ መሸጫ ማዕከላት እንዲሁም ከበርካታ ከተሞች መነሻቸውን በማድረግ ቅሬታዎቻቸውን ገልጸዋል።
ብዙዎች በስህተት ወደ ኤል ሳልቫዶር የተወሰደው ኪልማር አብረጎ ጋርሲያ እንዲመለስ ጠይቀዋል።
አሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ተቃውሞዎች በጣም የተለመዱ እየሆኑ መጥተዋል።
በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በመላ አገሪቱ የተካሄደው "እጃችሁን አንሱ" የሚለው የተቃውሞ ሠልፍ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈውበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጋሉፕ የተሰኘው ተቋም በቅርቡ በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት 45 በመቶ መራጮች የትራምፕን የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ደግፈዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያው አስተዳደር ዘመናቸው በተመሳሳይ ወቅት የነበራቸው ድጋፍ ከ41 በመቶ ከፍ ያለ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1952 እስከ 2020 መካከል ለተመረጡት ፕሬዚዳንቶች በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአማካኝ 60 በመቶ የሕዝብ ድጋፍ አግኝተው ነበር።
ቅዳሜው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች የመንግሥትን ብቃት በሚገመግመው መስሪያ ቤት (ዶጅ) የተለያዩ ሥራዎች እንዲዘጉ መደረጋቸውን፣ የትራምፕ አስተዳደር የኤል ሳልቫዶር ዜጋ የሆነው አብረጎ ጋርሲያ እንዲመለስ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን ጨምሮ በርካታ የትራምፕ እርምጃዎችን አንስተው ተቃውሞ አሰምተዋል።
ጊሃድ ኤልጀንዲ ለሲኤንኤን እንደተናገረው ከሆነ የአብሬጎ ጋርሲያን መባረር ለመቃወም በዋይት ሐውስ የተደረገውን ተቃውሞ ተቀላቅሏል።
ትራምፕ "ኤል ሳልቫዶር እንድትመልሰው በቀላሉ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ" ብሎም ያምናል።
ምንም እንኳን ተቃውሞው በአጠቃላይ ሰላማዊ ነበር ቢባልም፣ የዲሞክራቱ ተወካይ ሱሃስ ሱብራማንያም አንድ ሰው የትራምፕ ምስል በመያዝ እና በሕዝቡ መካከል በማለፍ ቁጣ ለመቀስቀስ ሞክሯል ሲሉ በገጻቸው ኤክስ ላይ ቪዲዮ ለጥፈዋል።
ብዙ ሰልፈኞች አገሪቱ በእንግሊዝ አገዛዝ ላይ ያቀጣጠለችውን አብዮት የጀመረችበትን መግለጫ የሆነውን "ንጉሥ አያስፈልግም" የሚል ምልክት ይዘው ታይተዋል።
በማሳቹሴትስ ደግሞ የሌክሲንግተን እና ኮንኮርድ ጦርነቶችን እና የታዋቂው የፖል ሬቭር የፈረስ ግልቢያን በማስታወስ በተከበረበት ወቅትም ተመሳሳይ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ቅዳሜ ዕለት በቦስተንም የ 50501 ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ከትዳር አጋሩ፣ ከልጁ እና ከልጅ ልጆቹ ጋር ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ቶማስ ባስፎርድ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገረው "ይህ በአሜሪካ ውስጥ ለነፃነት በጣም አደገኛ ጊዜ ነው። ሰዎች የዚህችን አገር አመጣጥ እና አንዳንድ ጊዜ ለነፃነት መታገል እንዳለብን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተለይም በኢኮኖሚው ረገድ የትራምፕ ተወዳጅነት እያሽቆለቆለ ይመስላል።
በጥር ወር ስልጣን ሲረከቡ የነበራቸው ተቀባይነት 47 በመቶ ነበር ሲል ጋሉፕ ተናግሯል።
በቅርቡ በሮይተርስ/አይፕሶስ ባደረጓቸው የሕዝብ አስተያየቶች ተቀባይነታቸው ስልጣን በተረከቡበት ቀን ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 43 በመቶ ዝቅ ብሏል።
በተመሳሳዩ የሕዝብ አስተያየት 37 በመቶዎቹ ብቻ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን አፈጻጸም ደግፈዋል።
ቃለ መሐላ በፈጸሙበት ዕለት ይህ አሃዝ 42 በመቶ ነበር።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ወዲህ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ የተባለ የተቃውሞ ሠልፍ ለማድረግ ተሰባስበዋል።
ከዚህ በፊት የተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ፣ ቅዳሜ ዕለት ከተደረገው ይበልጣል የተባለ ሲሆን በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች በአንድ ሺህ 200 አካባቢዎች ተካሂዷል።












