ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ቻይና ወታደራዊ እርምጃ ትወስዳለች ተብሎ ተሰግቷል
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋን ውስጥ ያደርጉታል ከተባለው ጉብኝት ጋር በተያያዘ ቻይና ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ለፕሬዝዳንት ባይደን ጽህፈት ቤት በቀረበው መረጃ መሠረት ቻይና ምናልባትም በታይዋን አቅራቢያ ሚሳኤል መተኮስን ጨምሮ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የአየር ወይም የባሕር ላይ እንቅስቃሴዎችን ልታደርግ እንደምትችል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።
ናንሲ ፔሎሲ በእስያ አገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለው ዛሬ ማክሰኞ ማሌዢያ ገብተዋል።
የታይዋን እና የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን አፈ ጉባኤዋ ዛሬ ማታ ታይዋንን ለመጎብኘት ታያፒ ይገባሉ ብለው ቢዘግቡም አስካሁን የተረጋገጠ መረጃ የለም።
ይህንንም ተከትሎ ታይዋን የግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና፣ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ “ከባድ መዘዝ” እንደሚከተል አስጠንቅቃለች።
ቻይና ታይዋን ወደ እናት አገሯ መመለስ ያለባት አፈንጋጭ ግዛቷ እንደሆነች ትመለከታታለች። ይህንንም ለማሳካት ወደፊት ቤይጂንግ ኃይል መጠቀምን እንደ አንድ አማራጭ ታየዋለች።
አሜሪካ ከቻይና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ከታይዋን ጋር ግን “ይፋዊ ያልሆ ጠንካራ” ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት አላት ይባላል።
የታይዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ጉብኝቱን በተመለከተ ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዳሉት፣ ደሴቲቱ የትኛውንም የውጭ እንግዳ “በአክብሮት ትቀበላለች” ብለዋል።
ጨምረውም ታይዋን የትኛውም ጎብኚ ለመቀበል “ተገቢ የሆነውን ዝግጅት ታደርጋለች” ብለዋል።
የፔሎሲ ጉብኝት ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ራስ ምታትን በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ መፍጠሩ እየተነገረ ነው።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ጦር ኃይል ፔሎሲ ወደ ታይዋን ሊያደርጉ ያሰቡት ጉብኝት “በአሁኑ ወቅት ጥሩ ሃሳብ አይደለም” ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት፣ ናንሲ ፔሎሲ “ታይዋንን የመጎብኘት መብት አላቸው፣ ይህም የእሳቸው ውሳኔ ነው” በማለት ዋይት ሐውስ የአገሪቱን ምክር ቤት ነጻነት ያከብራል ብለዋል።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ ፔሎሲ በአገሪቱ የሥልጣን አርከን ውስጥ ከፕሬዝዳንቱ እና ከምክትላቸው ቀጥሎ ሦስተኛ ሰው ናቸው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው የከፍተኛ ባለሥልጣኗን ጉብኝት በተመለከተ የጉዳዩን ክብደትና አሳሳቢነት በተመለከተ ከዋሽንግተን ጋር ግንኙነት መደረጉን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በደሴቲቱ አቅራቢያ የሚካሄዱ የትኛውንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ መሆኑን እና ከቻይና የሚመጣን ማንኛውንም ስጋት ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ናንሲ ፔሎሲ በቻይና የሰብአዊ መብት አያያዝ የተነሳ የአገሪቱን መሪዎች ለረጅም ጊዜ ሲተቹ ቆይተዋል። በተጨማሪም ከዲሞክራሲ ደጋፊ ቻይናውያን ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ የታይናሚን አደባባይ ጭፍጨፋ ሰለባዎችን ለማስታወስ አደባባዩን ጎብኝተዋል።
አፈ ጉባኤዋ የእስያ ጉብኝታቸውን ባለፈው እሁድ ወደ ሴንጋፖር በመጓዝ ጀምረዋል። የጉዞ ዕቅዳቸውም ማሌዢያን፣ ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ያካተተ ሲሆን ታይዋን ግን አልጠቀሰችም።
ፔሎሲ ታይዋንን ለመጎብኘት አቅደው የነበረው ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በኮቪድ በመያዛቸው ጉዟቸውን አዘግይተውት ቆይተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት “ለታይዋን ያለንን ድጋፍ ማሳየት ለእኛ አስፈላጊ ነገር ነው” ብለው ተናግረውም ነበር።
ከጉብኝቱ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ቀናት የታይዋን ሰርጥ ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ መተላለፊያ አይደለም የሚለውን ጨምሮ፣ ቻይና “ተቀባይነት የሌለው ሕጋዊ ጥያቄዎችን” ልታነሳ ትችላች ሲሉ ቃል አቀባዩ ኪርቢ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቤይጂንግ ወደ ታይዋን የአየር ክልል እያደረገችው ካለው ጥሶ የመግባት እርምጃ ጋር በተያያዘ በረራዎችን ልታደርግም ትችላለች ብለዋል።
በ1997 የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሪፐብሊካኑ ኒውት ጊንግሪች ታይዋንን አንደጎበኙ እና ባለፈው ሚያዚያ ወርም ስድስት የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ቃል አቀባይ ኪርቢ አስታውሰዋል።
“ስለዚህም ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ሊወራለት የሚችል ድራማም የለም። ስለዚህም የአፈ ጉባኤዋ የታይዋን ጉዞ ከዚህ በፊት ያልተደረገ አዲስ ነገር አይደለም” በማለት ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉብኝት በአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት የቻይና አምባሳደር የሆኑት ዣንግ ጁን የፔሎሲ ጉብኝት በ1997 ከተደረገው ጋር የማይነጻጸር መሆኑኑንና የአሁኑ በጠብ አጫሪነት የሚታይ ነው ብለዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ኒው ዮርክ ውስጥ በተደረገ የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ወቅት ለጋዜጠኞች ጉብኝቱን አስመልክተው እንደተናገሩት “አፈ ጉባኤዋ ታይዋንን ለመጎብኘት ወስነው ቻይና ቀውስ እንዲፈጠር ወይም እንዲባባስ ከሞከረች ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ትሆናለች” ብለዋል።