ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም አንድ የተሳሳተ እርምጃ በኒውክሌር ያጠፋታል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ
የዓለም አንድ የተሳሳተ እርምጃ በኒውክሌር እንደሚያጠፋት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አስጠነቀቁ።
አለም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ታይቶ በማይታወቅ አደጋ ላይ መሆኗን የገለጹት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ለመግባት እየተንደረደረች መሆኑንም አስረድተዋል።
“እስካሁን ድረስ እድለኞች ነበርን” ብለዋል አንቶኒዮ ጉተሬዝ
አለማችን በከፍተኛ ውጥረት ተይዛ ባለችበት በአሁኑ ወቅት “አለመግባባቶች፣ የተሳሳተ ስሌት አለማችንን በኒውክሌር ለማጥፋት ተቃርቧል” ሲሉም አክለዋል።
ዋና ጸሐፊው ይህንን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኒውክሌር ጦርነት መከላከከል ስምምነት የተፈራረሙ ሃገራት ጉባኤያቸውን በከፈቱበት ወቅት ነው።
ይህ በአውሮፓውያኑ 1968 የተደረሰው ስምምነት የተደረሰው የኩባ ሚሳኤል ቀውስን ተከትሎ ነው። የሚሳኤል ቀውሱ ዓለም ወደ ኒውክሌር ጦርነት ለመግባት ተቃርባ የነበረበት በሚልም ነው አብዛኛውን ጊዜ የሚገለጸው።
ስምምነቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያን በርካታ ሃገራት በባለቤትነት እንዳይዙ ለመግታት እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የኒውክሌር የጦር መሳሪያንም ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚል የመጨረሻ ግብን አንግቧል።
አምስቱ ታላላቅ የኒውክሌር ሃይሎች ጨምሮ በርካታ ሃገራት ይህ ኤንፒቲ የተሰኘውን ስምምነት ፈርመዋል።
ነገር ግን ካልፈረሙ ጥቂት ሃገራት መካከል አራቱ የኑክሌር የጦር መሳሪያዎች እንዳላቸው የሚታወቁ ወይም የሚጠረጠሩት ህንድ፣ እስራኤል፣ ሰሜን ኮሪያ እና ፓኪስታን ይገኙበታል።
ዋና ጸሓፊ ጉቴሬዝ እንዳሉት አለም የኒውክሌር ጥፋትን በማስቀረት እድለኛ ሆና መቆየቷን ገልጸው ይህ እድል ዘላቂ ላይሆን እንደማይችል ጠቁመው እናም አለም እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ለማጥፋት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያድስም አሳስበዋል።
"ዕድል ስትራቴጂ አይደለም ወይም ወደ ኒውክሌር ግጭት ሊያመራ ከሚችል ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች የሚከላከል ጋሻ አይደለም" ብለዋል።
በተለይም በዩክሬን ላይ የተፈጸመው ወረራ፣ በኮሪያ ግዛትና እና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ለአብነት በመጥቀስ እነዚህ አለም አቀፍ ውጥረቶች አዲስ ስጋቶችን ደቅነዋል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ከቀናት በኋላ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኒውክሌር ሃይሎች በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ሩሲያ ውጥረቱን በማባባስ ተከሳለች።
በተጨማሪም በሩሲያ መንገድ ላይ የቆመ ማንኛውም አካል “በታሪክ ታይቶ አይታወቅም” በሚል ሊከተል የሚችለውንም አስፈረራተዋል። ሩሲያ በያዘችው ስትራቴጂ መሰረት የሃገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ከወደቀ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀምን ያጠቃልላል።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ እለት ፕሬዚዳንት ፑቲን “በኒውክሌር ጦርነት አሸናፊዎች ሊኖሩ አይችሉም እና በፍጹም ሊጀመር አይገባም" ሲሉ ጉቴሬዝ በከፈተቱት ጉባኤ ላይ ፅሁፋቸውን ልከዋል።
ነገር ግን ሩሲያ በዚህ ኤንፒቲ ጉባኤ ላይ ትችት ገጥሟታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩስያን ያወገዙ ሲሆን ዩክሬን በሶቪየት ዘመን የነበረውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከሩሲያ እና ከሌሎችም ሃገራት የወደፊት ደህንነቷ ማረጋገጫ ከተቀበለች በኋላ በአውሮፓውያኑ 1994 ማስረከቧን አስታውሰዋል።
"በሉዓላዊነቷ እና ነጻነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መያዝ አለብኝ ብሎ ሊያስብ ለሚችል ማንኛውም የአለም ሀገር ምን መልእክት ያስተላልፋል?" ብለው የጠየቁት አንቶኒ ብሊንከን የሩሲያ ወረራ "በጣም መጥፎ መልእክት" ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት 13 ሺህ የሚሆኑ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች በዘጠኝ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በታጠቁ ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ከተከማቹት 60 ሺህ በጣም ያነሰ ነው።