ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ 28 ሰዎች ሲሞቱ ከ800 በላይ ቆሰሉ
በኢራን ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ ቢያንስ 28 ሰዎች ሲሞቱ፣ 800 ደግሞ መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ገለፁ።
ፍንዳታው የደረሰው ቅዳሜ ጠዋት በባንዳር አባስ ከተማ አቅራብያ በሚገኘው ሻሂድ ራጃኢ በተባለው የአገሪቱ ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ ነው።
በአካባቢው የሚገኙ ሕንጻዎች መስኮት እና ጣርያዎች የገነጠለ እንዲሁም መኪናዎችን ያወደመ ፍንዳታ ነበር ተብሏል።
ነዋሪዎች ፍንዳታው 50 ኪሜ ርቀት ድረስ ይሰማ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው እና ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ ከፍተኛ ፍንዳታ ከመድረሱ በፊት የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ነበር።
በምስሉ ላይ ሰዎች ከአደጋው ራሳቸውን ለማትረፍ ሲሮጡ እንዲሁም በፍንዳታው የተጎዱ መሬት ላይ ወድቀው ይታያል።
አንድ ከአደጋው የተረፈ ግለሰብ ለአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ "መጋዘኑ ሙሉ በሙሉ በጭስ፣ አቧራ እና አመድ ተሞላ።ራሴን ያገኘሁት ጠረጴዛ ሥር ነው። ጠረጴዛው ሥር እኔ ልግባ ወይም ፍንዳታው ይወርውረኝ የማስታውሰው ነገር የለም" ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ከአየር ላይ የተቀረፁ ምስሎች ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ቃጠሎው መስፋፋቱን የሚያሳዩ ሲሆን የኢራን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም እሳቱ ከኮንቴይነር ወደ ኮንቴይነር እየተስፋፋ መሆኑን አረጋግጠዋል።
እሁድ እለት በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ቢሮዎች ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል።
አንድ የግል የባሕር ኃይል ኩባንያ በእሳት ጉዳት የደረሰባቸው ኮንቴይነሮች ለባሌስቲክ ሚሳዔል ማምረቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነዳጅ ሳይዙ አይቀሩም ብሏል።
አምብሬ የተሰኘው የደኅንነት ተቋም የእሳት አደጋው "ለኢራን ባሌስቲክ ሚሳዔል ጥቅም ላይ የሚውል ነዳጅ ያለ ተገቢው ጥንቃቄ በመያዙ የተከሰተ" መሆኑን ተናግሯል።
አምብሬ የኢራን ባንዲራን የምታውለበልብ መርከብ "ሶዲየም ፐርክሎሬት የተሰኘ የሮኬት ነዳጅ በመጋቢት ወር 2025 አራግፋ ነበር" ብሏል።
ከዚህ ቀደም ብሎ ፋይናንሻል ታይምስ ሁለት የጭነት መርከቦች ከቻይና ወደ ኢራን ነዳጅ ማጓጓዛቸውን ዘግቦ ነበር።
የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ፍንዳታው የደረሰው እሳት ከተቀሰቀሰ እና "ተቀጣጣይ ነገሮችን" ወደ ያዘ እና ያልታሸገ ኮንቴይነር ከተዛመተ በኋላ መሆኑን ዘግቧል።
የአገሪቱ ጉሙሩክ መሥርያ ቤት ኃላፊዎች በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ ላይ በሰጡት መግለጫ ፍንዳታው የተከሰተው ምናልባት የአደገኛ ኬሚካሎች ማከማቻ ላይ እሳት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
አምብሬ የአገሪቱን ብሔራዊ አደጋ መከላከያ መሥርያ ቤት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደተናገረው በሻሂድ ራጃኢ ወደብ ኬሚካሎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲቀመጡ ማስጠንቀቅያ ሰጥተው ነበር።
ሻሂድ ራጃኢ ወደብ ኢራን ካሏት ዘመናዊ እና ትልቅ የንግድ ወደቦች መካከል አንዱ ነው።
ወደቡ ዋነኛ የነዳጅ ጭነት ማመላለሻ በሆነችው ሆርሙዝ የባህር ዳርቻ ላይ፣ ከባንደር አባስ በስተምዕራብ 20 ኪሜ ርቀት ላይ የኢራን ባሕር ኃይል ዋና መቀመጫ አካባቢ ይገኛል።
የኢራን ብሔራዊ ነዳጅ ማምረቻ ኩባንያ ፍንዳታው ከአገሪቱ ነዳጅ ማጣርያ፣ የነዳጅ ማከማቻ እና ማስተላለፊያዎች ጋር "ምንም ዓይነት ግንኙነት" እንደሌለው መናገሩን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ማሶድ ፔዜስኪያን በአደጋው የተሰማቸውን "ጥልቅ ሀዘን" ገልጸዋል።
አገሪቱ በፍንዳታው ዙርያ ምርመራ እንደምታደርግ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ይህንን እንዲመሩ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን ወደ ስፍራው ልከዋል።
ቅዳሜ ዕለት የደረሰው ፍንዳታ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር ፕሮግራሟን በሚመለከት ከምታደርገው ውይይት ጋር ተያይዟል።
አሜሪካ ቴህራን የኒውክሌር መሳርያዎችን እንዳትታጠቅ ለማድረግ ያለመ ድርድር ማድረግ ጀምራለች።
በኦማን አደራዳሪዎች በኩል እየተካሄደ ያለው ድርድርን ሁለቱም አገራት በመልካም ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ቢናገሩን የኢራን ከፍተኛ ልዑክ ተወካይ ልዩነቶችን ለማጥበብ መሰራት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ድርድሩ በሚቀጥለው ሳምንት ይቀጥላል ተብሏል።
ኢራን የተጣለባት ማዕቀብ የሚላላ ከሆነ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማጠፍ ዝግጁ መሆኗን ዩራኒየም ማበልጸጓን ግን እንደምትቀጥል ተናግራለች።
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዜጎች ጥቅም መሆኑን ትናገራለች።
ከአውሮፓውያኑ 2018 ወዲህ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በከፍተኛ ልዑካን የተመራ ውይይት ሲደረግ ይህ የመጀመርያው ነው።