ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ታላላቅ የዓለም መሪዎች በተገኙበት ተፈጸመ
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከዓለም ዙሪያ የመጡ እንግዶች እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሐዘንተኞች በተገኙበት ቫቲካን ውስጥ ተፈጸመ።
የበርካታ የዓለም አገራት መሪ ፖለቲከኞች፣ ንጉሣውያን፣ ታዋቂ ሰዎች እና 400 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና በቫቲካን ጎዳናዎች ላይ በመውጣት በጳጳሱ የመጨረሻ ስንብት ላይ ተሳትፈዋል።
ደማቁ እና በካቶሊክ ዕምነት ባሕል እንዲሁም የፀሎት ሥርዓት የታጀበውን የጳጳሱን የቀብር ሥነ ሥርዓት የመሩት ካርዲናል ቻምበርሌይን ኬቪን ፋረል ናቸው።
በዓለም ዙሪያ ከ1 ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ሆነው ከ10 ዓመታት በላይ በመንበራቸው ላይ የቆዩት ፖፕ ፍራንሲስ ለስደተኞች፣ ለተጨቆኑ እና ለተፈጥሮ አካባቢ ያላቸው ተቆርቋሪነት በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ጎልቶ ተሰምቷል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አገራት ለስደተኞች መጠጊያ በመሆን እንክብካቤ እንዲያደርጉ ከመወትወታቸው ባሻገር ድጋፍ እንዲያገኙ እና እንዲጽናኑ በግላቸው በርካታ ነገሮች ማድረጋቸው ይነገራል።
በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን ጦርነቶችን ለማስቆም ለድርድር ጥሪ በማድረግ እንዲሁም የዓለም የአየር ሁኔታ ለውጥ ትኩረት እንዲሰጠው ሲጥሩ ቆይተዋል።
ጣሊያናዊው ካርዲናል ጂዮቫኒ ባቲስታ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር "ለሰው ካላቸው ፍቅር እና በዘመናችን ለገጠሙን ፈተናዎች ካላቸው ጥልቅ ግንዛቤ የተነሳ ፖፕ ፍራንሲስ በዚህ ሰዓት ጭንቀታችንን፣ ሰቆቃዎችን እና ተስፋችንን ይጋራሉ" በማለት ተናግረዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ በሕይወት ሳሉ የቀብር ቦታቸው ቀለል ባለ ሁኔታ የተዘጋጀ እንዲሆን እና በስፍራው "ፍራንሲስ" የሚለው የጵጵስና ስማቸው ብቻ እንዲሰፍር ጠይቀው ነበር።
ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም. ከምሳ ሰዓት በኋላ የተጠናቀቀውን የቀብር ሥነ ሥርዓት ተከትሎ የውጭ አገራት መሪዎች ከሮም በመውጣት ወደ የመጡበት ሲመለሱ፣ ሐዘንተኞች እና ለሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የመጡ ሰዎች ባቫቲካን ይቆያሉ።
ከጳጳሱ ሕልፈት በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራ የነበረው ለርዕሳነ ሊቀ ጳጳሱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጅት ማድረግ እና ቀብሩን መፈጸም የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ ለዘጠኝ ቀናት የሚቆይ የሐዘን ሥነ ሥርዓት ይኖራል።
ከቀብር ዕለት ጀምሮ የሚካሄደው እና ለዘጠኝ ቀናት የሚቆየው የሐዘን ሥርዓት 'ኒቬምዲያሌስ' የሚባል ሲሆን፣ በየዕለቱም ጳጳሱ የሚዘከሩበት በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበት የፀሎት ሥነ ሥርዓት ይኖራል።
የጳጳሱ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ በቀጣይ የካቶሊኩ ዓለም ዋነኛ ትኩረት የሚሆነው የፖፕ ፍራንሲስን ቦታ ተረክበው ታላቋን ቤተክርስቲያን የሚመሩ ተተኪን የመሰየም ሂደት ነው።
ለዚህም ከዓለም ዙሪያ በቫቲካን ሲቲ የሚሰባሰቡት ካርዲናሎች ተለይተው የሚያካሂዱት ሥነ ሥርዓት በእያንዳንዱ ካቶሊክ ተጠባቂ ነው።
ነገር ግን የጳጳሱን ምርጫ በምሥጢር የሚያካሂዱት ካርዲናሎች ለምርጫው የሚቀመጡበትን ቀን እስካሁን አላሳወቁም። በተለምዶው ግን ይህ ስብሰባ ጳጳሱ ካረፉበት ቀን በኋላ ከ15 እስከ 20 ቀናት ባሉት ጊዜያት ሊካሄድ ይችላል።