ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ህወሓት’ በሚል መጠሪያ አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
‘ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)’ በሚል መጠሪያ አዲስ ክልላዊ ፓርቲ ለማቋቋም የቀረበ የቅድመ ዕውቅና ፍቃድ ጥያቄን ውድቅ ማድረጉን ብሔራዊ መርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ ‘ህወሓት’ በሚል ስም የአዲስ ፓርቲ መቋቋምን የማይቀበለው ከዚህ ቀደም መሠረቱን በትግራይ ያደረገው እና አገሪቱን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በበላይነት ሲያስተዳደር ከነበረው ፓርቲ መጠሪያ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ በመራጮች ዘንድ ግርታን ሊፈጥር ይችላል የሚለው አንዱ ምክንያት ነው።
ግንቦት 12/2015 ዓ.ም. አቶ ገ/ሚካኤል ተስፋይ በተባሉ የአደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢ የተፈረመ ደብዳቤ ቦርዱ ‘ህወሓት’ በሚል መጠሪያ ለሚመሠረት አዲስ ክልላዊ ፓርቲ ቅድመ እውቅና እንዲሰጥ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቀርቦ ነበር።
ምርጫ ቦርድም ከላይ በተጠቀሱት ግለሰብ እና በሌሎች ሦስት ግለሰቦች አወያይነት የ120 መሥራች አባላት ዝርዝር በማያያዝ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በሚል ክልላዊ ፓርቲ ለመመሥረት የቅድመ እውቅና ፈቃድ እንዲሰጥ ጥያቄ እንደቀረበለት ገልጿል።
ቦርዱ የኢትዮጵያ በምርጫ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና በምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት የቀረበለትን የጊዜያዊ ፈቃድ ጥያቄ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር አነጻጽሮ መመርመሩን ገልጿል።
ስለዚህም የምዝገባ ጥያቄ የቀረበበት ስያሜ በምርጫ ጊዜም ሆነ ከምርጫ ውጪ በዜጎች ዘንድ መምታታትን ወይም ግርታን የማይፈጥር መሆኑን ሊረጋገጥ ይገባል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚል ስያሜ እየተጠራ በትግራይ ክልልም ይሁን በሌሎች የአገራችን ክፍሎች በሚገኙ መራጮች ዘንድ ለረጅም ዓመታት የሚታወቅ ፓርቲ እንደነበር ግልጽ ነው” ብሏል።
በዚህም ምክንያት ቦርዱ በዚህ ስም አዲስ ፓርቲ ቢቋቋም መራጮችን የሚያደናግር በመሆኑ የቀረበለትን የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ ጥያቄ እንዳልተቀበለው አስታውቋል።
ይህ የአሁኑ የሕጋዊ ዕውቅና ጥያቄ ከህወሓት ከእራሱ ወይም ከሌሎች ወገኖች የቀረበ ይሁን አይሁን የተገለጸ ነገር የለም።
ከጥቂት ወራት በፊት በደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሊቀመንበርንት የሚመራው ህወሓት ሕጋዊ ዕውቅናው እንዲመለስለት ጠይቆ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ይታወሳል።
መሠረቱን በትግራይ ክልል ያደረገው እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኖ የቆየው ህወሓት የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነትን ተከትሎ ሕጋዊ እውቅናው በቦርዱ ከመሰረዘሙም በላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ቡድን ተብሎ ተፈርጆ ነበር።
በርስ በርስ ጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ጦርነቱን ለማቆም የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ፓርቲው አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው ቢነሳለትም ሕጋዊ እውቅናው ግን ከምርጫ ቦርድ መልሶ አላገኘም።
ይህን ተከትሎም ፓርቲው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈበትን የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ስረዛ እንዲነሳለት ጥያቄ ቢያቀርብም ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ምርጫ ቦርድ ግንቦት 05/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው በተደነገገው አዋጅ መሠረት በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን ተረጋግጧል በሚል የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ፣ የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንዳይችሉ፣ እንዲሁም የፓርቲው ንብረት ፓርቲው ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፣ ቀሪው ገንዘብ እና ንብረት ደግሞ ለሥነ ዜጋ መራጮች ትምህርት እንዲውል የሚደነግግ ነው።
በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላም በመቋጨቱ እና በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነትም በመጥቀስም ፓርቲው የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል የሚለው ድምዳሜ አሁን ላይ መለወጡን ታሳቢ በማድረግ ቦርዱ ከዚህ ቀደም ያስተላለፋቸውን የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ስረዛና ሌሎች ብያኔዎች እንዲነሳ ሲል መጠየቁንም ምርጮ ቦርድ አስፍሯል።
ቦርዱ ምንም እንኳ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ ባይሆኑም የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1162/ 2011 ተደንግጎ እንደማይገኝ ጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት ቦርዱ በህወሓት የቀረበለትን የሕጋዊ ሰውነት ጥያቄ የማስመለስ ጉዳይን በሕግ የተደገፈ ሆኖ ባለማግኘቱ አንዳልተቀበለው መጥቀሱ ይታወሳል።