ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ለሁለተኛ ጊዜ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)ን የዋና ጸሐፊነት ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ።

የኢትዮጵያ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ ተጨማሪ የሥራ ዘመን እንዲራዘም የተወሰነው ሰኞ ሰኔ 5/2015 ዓ. ም. ድርጅቱ ባደረገው መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ነው።

“ጉባዔው በእኔ ላይ ሙሉ እምነት አሳድሮ ለሁለተኛ አራት ዓመታት የሥልጣን ጊዜየን ስላራዘመልኝ በጣም አመሰግናለሁ” ሲሉም ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ የዋና ጸሐፊነት ስፍራውን የተረከቡት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ ስድስተኛው መሪ ናቸው።

በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስትርነትን ጨምሮ በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ያገለገሉት ዶ/ር ወርቅነህ የአሁኑን ሥልጣናቸውን የተረከቡት ከኬንያዊው አምባሳደር ማህቡብ ማሊም በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።

ሰኞ በጂቡቲ በተካሄደው 14ኛው የመሪዎች ጉባዔ የቀጣናውን የድርጅታዊ ሊቀ መንበርነት ሥልጣን ጂቡቲ ተረክባለች።

ለአራት ዓመታት በሊቀ መንበርነት የመራችው ሱዳን የሥልጣን ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎም ነው የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኦማር ጉሌህ ሊቀ መንበርነቱን የተረከቡት።

ኦማል አልበሽር ከሥልጣን መገርሰሳቸውን ተከትሎ የመጡት የሽግግር መሪው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሊቀ መንበርነት ከአራት ዓመታት በፊት ከመመረጣቸው በፊት የኢትዮጵያ መሪዎች ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል።

ከሳቸው በፊት የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮም በተከታታይ በነበሩት ዓመታት የሊቀ መንበርነቱን ስፍራ ተቆናጥጠውት ቆይተዋል።

አገራቱ የሚይዟቸው የሊቀ መንበርነት ስፍራ ከዚህ በፊት ሲያጨቃጭቅ የነበረ ሲሆን ተቋሙ ይህንን ሊያስተካክል የሚችል አዲስ ስምምነት በዘንድሮው ጉባዔ ማጽደቁም ተሰምቷል።

በዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔም እንደ ሌሎች ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ድርጅቱ የሚከተላቸውን ደንቦች አውጥቷል።

በዚህም መሠረት ለኢጋድ መሠረት የሆነውን የአውሮፓውያኑኑ 1996 ስምምነትም በመተካት ሊቀ መንበርነት አመራረጥን ጨምሮ አንዳንድ ወሳኝ ለውጦች የተካከቱበት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አባል አገራቱ የሊቀ መንበርነቱን ስፍራ ለአንድ ዓመታት ያህል እየተቀያየሩ የሚረከቡ ሲሆን ይህም በፊደል ቀደም ተከተል በየዓመቱ በሚደረግ ጉባዔም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።

ከስምምነቱ በተጨማሪ የማዕቀብ ሂደትና መጣል ላይ እንዲሁም በየአገራቱ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በድርድር እንዲፈቱም ለምክር ቤቱ ሥልጣን የሚሰጥ እንደሆነም ተገልጿል።

የዘንድሮው ጉባዔ በዋነኝነትም በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ጦርነቶችና ሶማሊያ ላይ መክሯል።

ዋና ጸሐፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በጉባዔው መክፈቻ ላይ የሱዳንን ቀውስ አስመልክተው ተናግረዋል።

ዋና ጸሐፊው በሱዳን የተከሰተው ጦርነት አስከፊ ስቃይን አስከትሏል ያሉ ሲሆን “በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስዋል እንዲሁም ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ተፈናቅለዋል” ብለዋል።

በሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስም ተፋላሚ ወገኖችን “ለሰላም ውይይትም ዕድል ስጡት” ሲሉ ጠይቀዋል።

በጦርነት እየታመሰችው ያለችው ሱዳን ጉባዔውን ለመካፈል የተወከለችው የአገሪቱ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው በተሾሙት በማሊክ አጋር ነው።

ዋና ጸሐፊው ባለፈው ዓመት ሐምሌ በነበረው 39ኛው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በኢጋድ መሪነት በተካሄደው ውይይት በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በድንበር ተከስቶ የነበረው ውጥረት መርገቡን አስታውሰው በቀጣናው የታየ አዎንታዊ ለውጥ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው ጉባዔም ላይ ለዓመታት ሳትካፈል የቆየችው ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኦስማን ሳላህ ተወክላለች።

ዋና ጸሐፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በጉባዔው መክፈቻ ላይ የኤርትራን መመለስ አስመልክቶ በጎ እመርታ ነው ብለውታል።

ኢጋድ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ስምንት አገራትን ያቀፈ ቀጣናዊ ድርጅት ሲሆን እነርሱም ኢትዮጵያ ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ናቸው።

ተቋሙ ቀጣናዊ ትብብር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ መረጋጋትና የምጣኔ ኃብት እድገት እንዲገኝ የሚሠራ ነው።

ድርጅቱ የአሁኑን ስሙን የያዘው በአውሮፓውያኑ 1996 ሲሆን የተመሠረተውም በአውሮፓውያኑ 1986 ሲሆን በቀጠናው እየተፈጠረ ለነበረው ድርቅና ረሃብ ምላሽ ለመስጠት ነበር።

በአካባቢው በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረው የከፋ ድርቅ ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ረሃብ ያስከተሉ ሲሆን የችግሩ መጠንና ስፋት ቀጣናዊ ትብብሮችን እንዲኖርም በማስፈለጉም ነው።