በውሃ ችግር በምትሰቃየው አዲስ አበባ ውስጥ ከዓመታት በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል?

ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ እና ዶ/ር ፍቃዱ ሞረዳ ይባላሉ። ሁለቱም ከፍተኛ የውሃ ሃብት ኢንጂነሮች ናቸው። ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ ነው። ዶ/ር ጥሩሰው ከፍሎሪዳ፣ ዶ/ር ፍቃዱ ደግሞ ከኖርዝ ካሮላይና።

በአዲስ አበባ የውሃ እጥረት ዙርያ ጠለቅ ያለ ጥናት ሠሩ። የጥናታቸው ግኝት መልሶ ራሳቸውን አስደነገጣቸው።

ከተማዋ ክፉኛ እንደተጠማች ደረሱበት። እሱ አይደለም ይበልጥ ያሳሰባቸው።

አንድ መፍትሄ ካልተበጀ አዲስ አበባን እንኳንስ ዲፕሎማቱ፣ ነዋሪዎቿም የሚሸሿት ከተማ እንደምትሆን የሩቅ ትንቢት ተነበዩ፤ ሳይንሳዊ ትንቢት።

የጥናታቸውን ርዕስ የተጠመደ ቦምብ (“Ticking Time Bomb”) አሉት።

ይህ ነገር የተጋነነ ፍርሃት ይሆን? ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ “በፍጹም አልተጋነነም” ይላሉ።

ለመሆኑ እነዚህን ምሁራን መጀመሪያውኑ የአዲስ አበባ የውሃ ችግር በተጠመደ ቦንብ እንዲመስሉት ያደረጋቸው ምንድነው? በእርግጥ ነዋሪዎቿ ይህ ነገር ሊያሳስባቸው ይገባል?

ዶ/ር ጥሩሰው “ያለውን የፍላጎት እና የአቅርቦት መጠን ማየት ብቻ’ኮ ብዙ ይነግረናል” ብለው ጀመሩ።

አሁን በትንሹ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ነዋሪ አዲስ አበባ ውስጥ እንዳለ ይገመታል። ሕዝቡ በ4% እየጨመረ ነው። ከተማዋ ተጨንቃለች። ተጠምታለችም።

“አዲሳ’ባ በትንሹ በቀን የሚያስፈልጋት 1.2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው። ከተማዋ እያቀረበች ያለችው ግን 480 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው።”

ይህ ስሌት የሚነግረን ምንድነው?

የአዲስ አበባ የውሃ ጄሪካኗ ከግማሽ በታች መሆኑን። በሌላ ቋንቋ ጄሪካኗ 60% ባዶ ነው።

መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም መሸማቀቅ

ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ያወያያቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በውሃ እጥረቱ መገረም ያቆሙ ይመስላሉ።

በፊት የውሃ ፈረቃ ቀን እና ማታ ተብሎ ይከፈል ነበር። ቀጥሎ የቧንቧ ውሃ አንድ ቀን እያለፈች መምጣት ጀመረች። አሁን በሳምንት አንድ ቀን ከመጣች ‘እልልታው ይቀልጣል’ ይላሉ ነዋሪዎች።

ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ፍሬ በሉኝ የምትለው የሰሚት ኮንዶሚንየም ነዋሪ፣ ትዳር ስትመሠርት ነው አድዋ ድልድይ አካባቢ ከነበረው የቤተሰቦቿ ቤት የወጣችው፤ የዛሬ አምስት ዓመት ግድም።

ከትዳር አጋሯ ጋር ሰሚት ኮንዶሚንየምን የመረጡት በዋናነት ያልተቋረጠ የውሃ አቅርቦት ስለነበረው ነው።

“አጋነንሽ አትበለኝና ያኔ የውሃው ኃይል ልነግርህ አልችልም። በተለይ ታችኛው ወለል ከሆንክ ኃይሉ ቧንቧ የሚሰብር የሚባል አይነት ነበር።”

ባለፉት 5 ዓመታት ግን የውሃ ፍሰቱ ታሪክ ፈጽሞ ተቀየረ። ውሃ እደላው በየዕለቱ መሆን ቀርቶ በየሰልስቱ፣ ብሎም በሳምንቱ ሆነ።

ይህ ዘገባ በሚሰናዳበት የግንቦት ወር በሰሚት አብዛኛዎቹ ብሎኮች ውሃ ለ15 ቀናት ዝር ሳትል ቆይታ እንደነበር ቢቢሲ ከነዋሪዎቿ ተረድቷል።

በከተማው ያለውን የውሃ ሥርጫትን ኢፍትሐዊነት በተነተኑበት ጽሑፋቸው ዶ/ር ፍቃዱ እና ዶ/ር ጥሩሰው፣ “በዚህ የዕደላ ድልድል አንድ ሰፈር በአንዳች ምክንያት ከዕደላው ከተስተጓጎለ ማካካሻ የለውም፤ ሌላ ሳምንት መጠበቅ ይኖርበታል” ይላሉ።

ሰሚት እና አባዶ ኮንዶሚንየሞች በውሃ ረገድ መልካም ስም የነበራቸው ናቸው። አባዶ አሁንም በሳምንት ሦስት ጊዜ ውሃ የሚያገኝ ‘ዕድለኛ’ ሰፈር የሚባል ነው።

ሰሚት ግን ከውሃ ጋር ተኳርፋለች።

“ማክሰኞ ማታ ትመጣለች፤ ሌሊት እየተነሳን በርሜል ሞልቶ ማደር የሕይወታችን አንድ ገጽታ ሆኗል” ትላለች፣ ፍሬ።

ብዙ ነዋሪ ልብስ የሚያጥበው በውድቅት ሌሊት ሆኗል።

ከዚህ የሚከፋው ታዲያ በውሃ እጥረት የሚከሰተው የኮንዶሚንየም ነዋሪዎች በሃፍረት መሸማቀቅ ነው። ውሃ ስትዘገይ መጸዳጃ ቤት እና ያ መጥፎ ጠረኑ ይከተላል።

“እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ማንም ዘመድ አዝማድ ቤቴ እንዲመጣ አልፈልግም፤ ያው ይገባሃል የምልህ አደል?” ትላለች ፍሬ።

“አሁን አሁን ሰው ቤቴ መጥቶ መጸዳጃ ቤት ልጠቀም ካለኝ ድንግጥ ነው የምለው፤ ብድር ቢጠይቀኝ ይሻለኛል” ስትል የነገሩን አስከፊነት በዋዛ ለማስረዳት ትሞክራለች።

ፍሬ እንዲህ ያስባላት ከዚህ ቀደም ከመጸዳጃ ቤት ጋር በተያያዘ በባልዲ ውሃ ያልተቀረፈ መጥፎ አጋጣሚን ስለምታስታውስ ነው። መልሶ ለመተረክ እስኪያሳፍራት ድረስ።

“የምንኖረው እኮ በታላቅ ጥበብ ነው፤ የምር” ብላ ነገሩን አደባብሳ ታልፈዋለች።

በውሃ ችግር የምትሰቃየው ከተማ

ውሃ በቀን 24 ሰዓት፣ በዓመት 365 ቀናት የሚያገኝ ሰፈር አለ? የለም!

አዲስ አበባ ውስጥ የውሃ ያለህ የማይል ሰፈር የለም።

ቢቢሲ ከሳሪስ እስከ ሰሜን ማዘጋጃ፣ ከሸጎሌ እስከ ፒያሳ፣ ከቤቴል እስከ ኡራኤል፣ ከአባዶ እስከ ጎፋ መብራት ኃይል ነዋሪዎችን በመጠየቅ በሠራው ኢ መደበኛ ዳሰሳ ሳምንቱን ሙሉ ቧንቧ የምትፈስበት አንድም እርጥብ ሰፈር እንደሌለ ተረድቷል።

ፒያሳ አካባቢ የተሻለ ሥርጭት ያለ ሲሆን፣ እሱም ውሃ እንደ ቅርብ ዘመድ ዐርብ መጥታ እሑድ ማታ ትሰናበታለች።

ከዚያ ሌላ በዳሰስናቸው ሰፈሮች ሳምንታዊ ሥርጭቱ በቀን አንድ ጊዜ እሱም በሌሊት ነው የሚከሰተው።

የሳሪስ አዲሱ ሰፈር ነዋሪ የሆኑት አቶ ስለሺ ይልማ በሰፈራቸው ውሃ ማክሰኞ በመደበኛነት እንደምትመጣ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በቃ ምን ልበልህ ማክሰኞ ዕለት በኩባያ ሳይቀር ነው ውሃ የምንሞላው፤ በኪሳችን ራሱ ብንቀዳ ቅር አይለንም፤ መዝለቂያችንን የምናቁረው ማክሰኞ-ማክሰኞ ነው” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት በቀልድ መልክ ይናገራሉ።

“ሁሉም ቶሎ ገላውን ይታጠባል፤ ካልሲ ነሽ ፓንት ነሽ በቃ የተጠራቀመ ልብስ ሁሉ ቀን ይወጣለታል።”

ይህ ዘገባ ተጠናቅሮ ለኅትመት ሲሰናዳ በሰሚት ኮንዶሚንየም ውሃ የቀረችበት አንደኛ ወር በታላቅ ቁዘማ እና ጽሞና ታስቦ እየዋለ ነበር።

ቢጫ ጄሪካን የሰፈሩ ባንዲራ እስኪመስል የትም ይታያል። ውሃ በትልቁ ጄሪካን እስከ 30 ብር ያስከፍላል። አብዛኛው ነዋሪ የዝናብ ውሃ ማቆር ጀምሯል፤ ልክ እንደ በረሃማ ክልሎች።

ዶ/ር ጥሩሰው እና ባልደረባቸው በተለያዩ አገራት የውሃ ልማት ጥናቶች ላይ ተሳትፈዋል።

ይሁንና የአዲስ አበባ እጥረት ከምናውቃቸው ከተሞች ሁሉ የከፋ ነው ይላሉ።

“ለእኔ አሁን ነዋሪው ችግሩን ተቋቁሞ መኖሩ በራሱ ተአምር ሆኖ ነው የሚታየኝ” የሚሉት ዶ/ር ጥሩሰው የኮሮና ዘመቻ ጊዜ ቶሎ ቶሎ በሳሙና እጃሁን ታጠቡ የሚለው ማስታወቂያ ሲሰሙ ሁሉ ይገረሙ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በቂ ውሃ ሳይኖር ታጠቡ መባሉ ነው የገረማቸው።

“እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ሁሉም ሰው ቶሎ ቶሎ ሊታጠብ የሚችለበት ውሃ አልነበረም፤ አሁን እኮ ውሃ በአዲስ አበባ ቅንጦት ነው፤ አይደለም እንዴ?” ብለው መልሰው ይጠይቃሉ።

አዲስ አበባ ያላት ውሃ ለስንት ዓመት ያዘልቃታል?

በዚህ ሰዓት በአዲስ አበባ የውሃ ጥያቄ ያልነካው ሰፈር፣ ያልዳሰሰው ሕብረተሰብ፣ ያላሳሰበው አካል የለም።

ነገሩ አኮኖሚን የሚጎዳበት ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የሚያሳስቡ ምሁራን አልጠፉም።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ሊያሽመደምደው ይችላል።

ብዙ የውጭ ባለሃብቶች ግዙፍ ፕሮጀክት ለመክፈት ሲያስቡ በዚያች አገር ሰላም አለ ወይ ብለው ይጠይቃሉ፤ በቅድሚያ።

ቀጥሎ የሚያሳስባቸው ኢንተርኔት፣ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይልን የመሰሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች በበቂ ስለመኖራቸው ነው።

ኮንዶሚንየም ቤቶች ሲሸጡ አንዱ ጥያቄ የውሃ አቅርቦት ጉዳይ ሆኗል። ወለል ላይ ያሉት የተሻለ ዉሃ ስለሚያገኙ የተሻለ ዋጋ ያወጣሉ ይባላል።

የቤት ልማት (ሪልስቴት) ማስታወቂያዎች የራሳችንን “ውሃ ቆፍረን እናቀርባለን” ማለት ጀምረዋል። ይሄም ስለከተማዋ መጻኢ ዕድል ብዙ የሚነግረን ነገር አለ።

ዶ/ር ጥሩሰው በግለሰቦች በዘፈቀደ ተቆፍረው የሚወጡ ውሃዎች አደጋቸውን ብዙ ሰው እንደማይረዳ ታዝበዋል።

ሰው ውሃ ተቆፍሮ መውጣቱን ነው የሚያየው።

የከርስ ምድር ውሃ እርስ በርሱ የተገናኘ ነው። ማን ምን ያህል ያወጣል የሚለው በቅንጅት ካልተሠራ መደረቅ ይጀምራል። ያኔ ነው ችግሩ የሚገለጥልን ይላሉ።

“አይደለም በግለሰቦች ጥልቅ ያልሆነ (Shallow) የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ይቅርና የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ በፈረንጅ 2000 አቃቂ ላይ በጥልቅ ካስቆፈራቸው ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት ጉድጓዶቹ ደርቀዋል።”

“የከርሰ ምድር ውሃ በሆይ ሆይታ አይቆፈርም፤ አሁን 500 ሜትር ጥልቀት እየተቆፈረም ውሃ ማግኘት ችግር ሆኗል። ይህ የሆነበት ምክንያትም ዝርዝር ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉ” ይላሉ ዶ/ር ጥሩሰው።

ይህ ራሱን የቻለ ሰፊ ጉዳይ በመሆኑ ሌላ ጊዜ ብቻውን ብንመለስበት ይሻላል።

ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ቀጣይ ዓመታት ዕጣ ፈንታዋ እንመለስ።

በነገራችሁ ላይ አዲስ አበባ አሁን 65 ከመቶ ውሃዋን ከከርሰ ምድር ነው የምታገኘው። የቀረውን ደግሞ ከገጸ ምድር ነው የምታገኘው። የገጸ ምድሮቹ ለጋዳዲ ድሬና ገፈርሳ ናቸው። አቅማቸው ግን በጣም ትንሽ ነው።

“ሁሉም በማቆሪያቸው ሙሉ እንኳ ቢይዙ አዲስ አበቤን ከሁለት ወር በላይ ሊያጠጡ አይችሉም።”

የቀጣይ ዓመታት ስጋት

አዲስ አበባ የአገሪቱን 29 ከመቶ ጥቅል አገራዊ ምርት (GDP) የምትሸከም ከተማ ናት። ይህ ማለት የውሃ አቅርቦት በከተማዋ ማነስ በቀጥታ ኢኮኖሚውን ያደርቀዋል።

ሆስፒታልን፣ ብዙ ሕዝብ ቀጣሪ ነው የሚባለውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን፣ ቱሪዝሙን በሙሉ የውሃ አለመኖር ያሽመደምደዋል።

ብዙ ሕዝብ የሚተዳደረው በአገልግሎት ሰጪ (service industry) ነው። ይህ ደግሞ ውሃን አሟጦ የሚጠቀም ዘርፍ ነው።

አዲስ አበባ በፍጥነት ነው እያደገች ያለችው። ከፍተኛ ግንባታዎች ይካሄዳሉ። የውሃ እጥት እንደ ሲሚንቶ እጥረት የግንባታ ሥራዎችን የሚያስተጓጉልበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል።

ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መቼስ በጄሪካን እየተቀዳ፣ በአህያ እየተመላለሰ ሊገነባ አይችልም።

“አደጋው በሁሉም መስመር ነው ያለው፤ በግላጭ ላይታየን ይችላል። ሲከሰት ብቻ ነው የሚገባን” ይላሉ ዶ/ር ጥሩሰው።

እንደሳቸው ትንቢት አሁን ያለው አስከፊ ሁኔታ ቢበዛ ለመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ቢያዘልቅ ነው።

ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባ በዚህ መልኩ በፍጹም 10 ዓመት ሊያጠጣት የሚችል ውሃ የላትም።

“የሚቀጥሉትን ጥቂት ዓመታትን ካለፈች ራሱ ይደንቀኛል” ይላሉ ዶ/ር ጥሩሰው።

አራተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እየተባለች የምትቆላመጠው አዲስ አበባ አይበለውና ጠረኗ መቀየር ከጀመረ ማንም አብሯት መቆየት አይሻም።

“ጥለው ነው የሚጠፉት፤ ሌሎች ተወዳዳሪ ከተሞች በቅርብ ካሉ ምርጫቸው ወደዚያ ነው የሚሆነው” ይላሉ ዶ/ር ጥሩሰው፤ ጎብኚዎች፣ ባለሀብቶች እና ዲፕሎማቶች እንደ ነዋሪው ከችግሩ ጋር የመኖር ትዕግስቱ እንደሌላቸው ሲያስረዱ።

ለነገሩ ውሃ በሌለበት እንኳን ሰው ይቅር እና ከብቱስ ይኖራል እንዴ? ግመልም ብትሆን የቋጠረችው አልቆ እስኪጠማት ነው፤ ትዕግስቷ።

በታሪክ ዳቦ ያስነሳው አብዮት አይተናል፤ ሰምተናል። የውሃ እጥረት የሚቀሰቅሰው የከተሜ ስስ አብዮት ሊመጣ ስንት ዓመት ይቀረናል?

አዲስ አበባ እና የብልጽግና ዘመን ሃብታም-ተኮር ፕሮጀክቶቿ ከብልጹግ አገራት ጋር የሚቀራረቡ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይን የሚጠይቁ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ከተማዋ የትልልቅ ፓርኮች ባለቤት እየሆነች መጥታለች። ውሃ ግን ተጠምታለች።

ከፓርክ ግንባታ የውሃ ቁፋሮ መቅደም እንደነበረበት ማን ይጠፋዋል? ፓርኮቹም ቢሆን’ኮ ዉሃ መጠጣት አለባቸው።

ቶሎ መላ ካልተፈለገ ችግኞች እና ሰዎች ውሃ ተሻምተው የሚጠጡባት አዲስ አበባን የምናይበት ዘመን ሩቅ አይመስልም።