ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኒጀር ወታደራዊ አመራሮች የፈረንሳይ አምባሳደር አገሪቷን በ48 ሰዓታት ለቀው እንዲወጡ አዘዙ
በኒጀር በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠሩት ወታደራዊ አመራሮች የፈረንሳይ አምባሳደር አገሪቷን በ48 ሰዓታት ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፉ።
በኒጀር እና በቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ መካከል ያለው ግንኙነት ከቀን ወደ ቀን እየሻከረ ባለበት ወቅት ነው ይህ የተሰማው።
ወታደራዊ አመራሩ የፈረንሳይ አምባሳደር ከኒጀር የውጭ ጉዳይ ሚነስትር ጋር ለመገናኘት ለቀረበላቸው የእንገናኝ የግብዣ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ብሏል።
ፈረንሳይ በበኩሏ “ሥልጣንን በኃይል የተቆጣጠሩ ግለሰቦች” እንዲህ ያለውን ማባረር ለማዘዝ “ሥልጣን የላቸውም” ብላለች።
ኒጀርን በአንድ ወቅት በቅኝ ግዛት ይዛት የነበረችው ፈረንሳይ በቅርቡ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የምትቃወም ሲሆን በኃይል ከሥልጣን የተገረሰሱት ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም ወደ ሥልጣን መመለስ አለባቸው ስትልም ትሰማለች።
የፈረንሳይ አምባሳደር እንዲወጡ ትዕዛዙ የተላለፈው በወታደራዊ አመራሩ በተሾሙት የኒጀር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነው።
መፈንቅለ መንግሥቱንም ተከትሎ የፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ የተቃጠለበትን ጨምሮ ሌሎች ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።
ኒጀር የፈረንሳይ የጦር ሰፈር መቀመጫ ስትሆን፣ በዓለምም ሰባተኛ የዩራኒየም ማዕድን አምራች አገር ናት።
የዩራኒየም ማዕድን ለኒውክሌር ኃይል በጣም አስፈላጊ ግብዓት ነው።
ሩብ የሚሆነው ይህ የኒጀር ማዕድን ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ቀድሞዋ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ይላካል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙ ወታደሮች ይህንን ጥያቄ የማቅረብ ሥልጣኑ የላቸውም። አምባሳደሩ በአገሪቱ እንዲቀመጡ የተደረጉት በሕጋዊ መንገድ በተመረጡ የኒጀር ባለሥልጣናት ብቻ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የኒጀር መንፈንቅለ መንግሥት መሪ የሆኑት ጄነራል አብዱራህማኔ ቺያኒ አገራቸውን በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመመለስ ቃል ገብተዋል።
ጄነራሉ ይህንን ያስታወቁት ከምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት ማኅበረሰብ ኢኮዋስ አሸማጋዮች ጋር በዋና ከተማዋ ኒያሚ ከተገናኙ በኋላ ነው።
ኢኮዋስ ፕሬዚዳንት መሃመድ ወደ ስልጣን መመለስ ድርድር ካልተሳካ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ መዛቱ ይታወሳል።
የወታደራዊ አመራሩ ኒጀር ጦርነት እንደማትፈልግ፤ ነገር ግን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ራሷን እንደምትከላከል ተናግረዋል።
ጄነራሉ በተጨማሪም ኢኮዋስ የባህር በር በሌላት እና ድሃ በሆነች አገር ላይ የጣለውን ማዕቀብ “ሕገወጥ እና ኢሰብዓዊ” ነው ሲሉም አውግዘዋል።