ፈረንሳይን በመቃወም የሩሲያን አጋርነት እየሻቱ ያሉት ኒጀራውያን

በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በምዕራቡ ዓለም ላይ ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ይፋ ሆኗል።

የቀድሞዋ ቅዢ ገዢ ፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ በኒጀር አደባባዮች ሲቃጠል ታይቷል።

ፈረንሳይን መጥላት ብቻ ሳይሆን የሩሲያንም አጋርነት መሻት የታየበት ነው።

የሩሲያ ሰንደቅ አላማ ያለበትም ቲሸርትም ኒጀራውያን ለብሰው ታይተዋል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በጦሩ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል የቃላት ጦርነት ተጧጡፏል።

በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የተገረሰሱት መሐመድ ባዙም፣ በምዕራባውያን ዘንድ ጽንፈኝነትን በመዋጋት ረገድ እንዲሁም በምጣኔ ሃብቱ ጠንካራ አጋር ተደርገው ነው የሚታዩት።

ኒጀር የፈረንሳይ የጦር ሰፈር መቀመጫ ስትሆን፣ በዓለምም ሰባተኛ የዩራኒየም ማዕድን አምራች አገር ናት።

የዩራኒየም ማዕድን ለኒውክሌር ኃይል በጣም አስፈላጊ ግብዓት ነው። ሩብ የሚሆነው ይህ የኒጀር ማዕድን ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ቀድሞዋ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ያቀናል።

የፕሬዚዳንቱ የክብር ዘብ መሪ የነበሩት ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ሥልጣንን በመፈንቅለ መንግሥት ከተቆጣጠሩ በኋላ በጎዳናዎች ላይ የሩሲያ ሰንደቅ አላማ መታየቱን ቀጥሏል።

ባለፈው ሳምንት እሁድ በዋና ከተማዋ ኒያሚ በተደረገ የአደባባይ ተቃውሞ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በዚህም ተቃውሞ በርካቶች የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ፣ ሌሎች ደግሞ በፈረንሳይ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

በአሁኑ ወቅት ይህ ንቅናቄ በመላው አገሪቱ እየተስፋፋ የመጣ ይመስላል።

ከመዲናዋ በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዚንደር ከተማ ቢቢሲ ያገኘው ነጋዴ የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት ቲሸርት ለብሶ ነበር።

ግለሰቡ ለደኅንነቱ ሲል ስሙም ሆነ ማንነቱ እንዳይጠቀስ ቢቢሲን ጠይቋል።

“እኔ የሩሲያ ደጋፊ ነኝ። ፈረንሳይን አልወዳትም” የሚለው ይህ ግለሰብ “ከልጅነቴ ጀምሮ ፈረንሳይን እቃወም ነበር። ፈረንሳይ የአገሬን ሃብት ሁሉ እንደ ዩራኒየም፣ ነዳጅ እና ወርቅ እየበዘበዘች ነው። በፈረንሳይ ምክንያት ነው በጣም ድሃ የሆኑ ኒጀራውያን በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ መብላት የተሳናቸው” ይላል።

ነጋዴው እንደሚናገረው ሰኞ በዚንደር ከተማ በተካሄደው የአደባባይ ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉትም ለመፈንቅለ መንግሥቱ ድጋፋቸውን ለመግለጽ ነው።

በአካባቢው ለሚገኝ ልብስ ሰፊ ገንዘብ ከፍሎ የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የሆኑትን ነጭ፣ ሰማያዊ እና ቀይ ያሉት ቲሸርት እንዳሰፋ ተናግሯል።

በሩሲያ ደጋፊ ቡድኖች ተከፍሎ ነው የተሰፋው የተባለውንም አጣጥሎታል።

ኒጀር በቀን ከ2.15 ዶላር ባነሰ ገቢ ከአምስቱ ሁለቱ ዜጎቿ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩባት የ24.4 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ናት።

ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አውሮፓውያኑ 1960 ነጻ ከወጣች በኋላ፣ የአገሪቷን መሪ እንዲተኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ ዴምክራሲያው ምርጫ በ2021 የተመረጡ መሪ ናቸው።

ነገር ግን መንግሥታቸው ከእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ቡድን እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ባላቸው እንዲሁም በሰሃራ በረሃና ከፊል በረሃማ በሆነው ሳህል በኩል የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ኢላማ ሆነዋል።

በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች በነበሩት በማሊ እና በቡርኪናፋሶ ጦር ሠራዊቱ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ጽንፈኞቹንም ለመዋጋት ያግዛል በሚል ነበር ወታደራዊ አመራሮቹ ወደ አመራሩ የመጡት።

ልክ እንደ ኒጀር ቡርኪናፋሶ እና ማሊም ቀደም ሲል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፈረንሳይ ወታደሮች በአገራቱ ተሰማርተው እየረዷቸው ነበር። ነገር ግን ጥቃቱ መቀጠሉን ተከትሎም ፀረ ፈረንሳይ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታዎች ተቀጣጥሏል።

በሦስቱም አገራት ሰፍረው የነበሩ የፈረንሳይ ወታደሮች የጽንፈኞቹን ጥቃት ለማስቆም በቂ ጥረት አላደረጉም በሚልም በዜጎቹ ተወንጅለዋል።

የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነርን በማስገባት የፈረንሳይ ወታደሮችን አስገድዶ አስወጥቷል። ከዚያም በሺዎች የሚቆጠሩ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ገፋፍቶ አስወጥቷል።

በማሊ የነበሩ ጥቃቶች ቢቀጥሉም የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አመራር የሩሲያ አጋርነትን በመምረጥ በአገሪቱ ተሰማርተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፈረንሳይ ጦርን አስወጥቷል።

በኒጀር ቀደም ሲል ፀረ ፈረንሳይ ተቃውሞዎች ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ቢነሱም አስተዳደራቸው በተደጋጋሚ አግዷቸዋል።

በተለይም ከማሊ ለቀው እንዲወጡ የታዘዙትን የፈረንሳይ ጦር ኃይል በኒጀር እንዲሰማሩ የባዙም አስተዳደር ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ በርካታ የሲቪል ማኅበራት ፀረ ፈረንሳይ ተቃውሞዎችን ማሰማትም ጀምረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሲቪል ማኅበራት እና በሠራተኛ ማኅበራት ጥምረት የተመሠረተው ኤም62 የተሰኘው ንቅናቄ ነው።

ጥምረቱ በአገሪቱ ውስጥ እያገረሸ ያለው የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የፈረንሳይ ኃይል በአገሪቱ ተሰማርቶ መገኘትን በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል።

በንቅናቄው ታቅደው የነበሩ የአደባባይ ተቃውሞዎች በኒጀር ባለሥልጣናት ተከልክለዋል፣ እንዲሁም የተደረጉ ተቃውሞዎችም በፀጥታ ኃይሎች ችግር ገጥሟቸዋል።

መሪው አብዱላየ ሰይዱም “ሕዝባዊ ሰላምን በመረበሽ” ለዘጠኝ ወራት ታስረዋል።

ሆኖም ከፕሬዚዳንት ባዙም ከሥልጣን መውረድ በኋላ የንቅናቄውም አካሄድ የታደሰ ይመስላል። ባልተለመደ ሁኔታም የንቅናቄው አባላት ወታደራዊ መንግሥቱን በመደገፍም በቴሌቪዥን ዘገባዎች ላይ ሲጠቀሱ ተሰምቷል።

እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር የሆነው ኢኮዋስ የጣለውን ማዕቀብም አውግዘዋል። ንቅናቄው መፈንቅለ መንግሥቱን ካካሄደው የአገር ጥብቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ሲኤንኤስፒ) ከተሰኘው ወታደራዊ አመራር ጋር ግንኙነት ይኑረው ግልጽ አይደለም።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት እሁድ የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጀው የንቅናቄው አባል የሆነ አንድ ድርጅት ሲሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ትግል አስተባባሪ ኮሚቴ (ሲሲኤልዲ) ቡካታ እና የወጣቶች ተግባር ለኒጀር (ዩዝ አክሽን ፎር) ለኒጀር ያሉ አናሳ የሲቪል ማኅበራትም ተሳታፊ ሆነዋል።

በዚንደር ወደነበረው ተቃውሞ ስንመለስ የሩሲያ ደጋፊ የሆነው ነጋዴ ሞስኮ የትውልድ አገሩን መርዳት ትችላለች ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።

“ሩሲያ የደኅንነት እና የምግብ እርዳታ እንድታደርግልን እፈልጋለሁ። ሩሲያ የእኛን ግብርና ለማሻሻል የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ማቅረብ ትችላለች” ብሏል ነጋዴው።

ነገር ግን በዚንደር ነዋሪ የሆነ አርሶ አደር በዚህ አይስማማም፣ መፈንቅለ መንግሥቱ ማንንም እንደማይጠቅም ያስረዳል።

“ሩሲያውያንን ወደዚህ አገር መምጣትን አልደግፍም፤ ምክንያቱም ሁሉም አውሮፓውያን ስለሆኑ ማንም አይረዳንም። አገሬን እወዳለሁ እናም በሰላም እንደምንኖር ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል ሞቱካ የተሰኘው አርሶ አደር።