‘ዜግነታቸውን’ የሚቀይሩት የኢትዮጵያ ከብቶች

የሰው አዘዋዋሪዎች አሉ። አባብለው ዜጎችን ለስደት የሚዳርጉ።

ከደቡብ ክልል እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ከአፋር እስከ ሊቢያ።

የቀንድ ከብት አዘዋዋሪዎችም አሉ፤ ፍየል አባብለው ከአገር የሚያስወጡ። ከአፋር በጂቡቱ እስከ ሳዑዲ አረቢያ፥ ከሶማሌ ክልል፣ በሶማሊያ እስከ ኤምሬትስ።

አንዳንዴ ደግሞ ደላሎቹ ከብቶቹን ግጦሽ ፍለጋ አስመስለው ይነዷቸዋል፤ ከድንበር ያደርሷቸዋል።

ከዚያ አብረው ድንበሩን ይሻገሩታል። ከድንበር ማዶ አሰፍስፎ የሚጠብቅ ተቀባይ አለ።

ለፍየል በዶላር የሚከፍል። ለበግ የውጭ ምንዛሬ የሚመነዝር።

ከዚያ ወዲያ ፍየሉም የካልዲ አይደለም፤ በሬውም የሐረር ሰንጋ አይባል።

ከዚያ ወዲያ የቁም ከብቶቹ ‘ዜግነታቸው’ ፈጽሞ ይቀየራል። የጂቡቲ ፍየል፣ የሶማሊያ በግ፣ የሞያሌ ጠቦት፣ የሱዳን በሬ ይሆናል ስማቸው።

ድንበሩን ከተሻገሩ በኋላ ልክ እንደ ሰው ማቆያ ይገባሉ። ከዚያ የጤና ሁኔታቸው ማረጋገጫ ሲያገኝ ወደ ሦስተኛ አረብ አገር ይላካሉ። በመርከብ።

ደከም፣ ከሳ ካሉ እዚያው ታርደው ይበላሉ። ፈርጠምጠም ያሉት ባሕር ማዶ ለመሻገር መጠለያ ይገባሉ።

ሦስተኛው ተቀባይ አገር አውሮፓ አይደለም። አውሮፓ ከምሥራቅ አፍሪቃ በግ እና ፍየል አይቀበልም።

ለማንኛውም የእነዚህ ‘ትውልደ-ኢትዮጵያውያን’ በግ እና ፍየሎች መዳረሻ በዋናነት ሦስት ነው። ወይ ዱባይ፣ ወይ ባሕሬን ወይ ሳዑዲ አረቢያ።

እዚያ ያለው አረብ ተመጋቢ “ማሻላህ! እንዴት ያለ የጂቡቲ ጠቦት አጣጣምኩ መሰለህ” ይላል።

ያጣጣመው ግን የኢትዮጵያን ሥጋ ነው። ያን ሐቅ ከደላሎች በስተቀር ማንም አያውቅም።

ፍየሎቹን ለምን ዜግነት ያስቀይሯቸዋል?

ኢትዮጵያን በቀንድ ከብት የሚያህላት የለም። የምሥራቅ አፍሪካ ብቻም ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት ናት።

በኢትዮጵያ ከ60 አስከ 70 ሚሊዮን የቁም እንሰሳት እንዳሉ ይገመታል።

ምን ዋጋ አለው ክምችት እንጂ ጥራት የለም። ሃብት መቁጠሪያ እንጂ ሃብት መፍጠሪያ አልሆኑም።

ይህ ሁሉ ከብት ኖሮ ለአሥራ አንድ መለስተኛ ቄራዎች እንኳ የሚያጠግብ፣ በቂና አስተማማኝ አቅርቦት የለም።

ይህ ሁሉ የከብት ክምችት እያላት ሰፊ የግጦሽ እና የርቢ ማዕከል (ራንች) እንኳ የለም።

ሌላው ፈተና ይላሉ አቶ አብረሃ ነጋሽ “አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴት የቁም ከብቶች መሆናቸው ነው።”

አቶ አብረሃም የወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ናቸው።

እሳቸው እንዳስረዱን ከሆነ ከብት ሁሉ ወደ ውጪ አይላክም።

ዕድሜ፣ ጾታ፣ የከብቱ የሕይወት ታሪክ፣ የሥጋው ደልዳላነት ሁሉ ከግምት ውስጥ ይገባል።

ለምሳሌ ተቀባይ አገራት በዋናነት የሚፈልጉት የፍየል ሥጋ ነው። የሚላከው ደግሞ ወንድ ፍየል ነው። ሴት ፍየል ስብ ይበዛታል፤ አትፈለግም።

የፍየሉ ዕድሜ ደግሞ ከ1 እስከ 2 ዓመት መሆን አለበት። ይሄ ሥጋው ሲላክ ነው። ከነሕይወቱ ከሆነ ደግሞ ዕድሜው ከ2 አስከ 3 ዓመት ሊሆን ይችላል።

አቶ አብረሃም ታዲያ በሥራ አጋጣሚ ብዙዎቹን የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።

ቦረና፣ ሱማሌ፣ አፋር ወዘተ።

የአፋር የቁም ከብቶች በአሳኢታ በኩል እየወጡ ለገበያ እንደሚቀርቡ ተገንዝበዋል።

በጂግጂጋ ደጋሐቡር ደግሞ የቁም ከብቶቹ በእግርም በመኪናም ከአገር ሲሾልኩ ታዝበዋል።

በየቀኑ እስከ አምስት የጭነት መኪና እንደሚወጣ ቢቢሲ ያገኛቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

“ይህ ሁሉ ለአገር የውጭ ምንዛሪ ሊያመጣ የሚችል ነበር፤ ያለመደታደል ሆኖ ብዙ እያሳጣን ነው” ይላሉ።

መንግሥት ቁጥጥር ለማድረግ ይሞክራል። ይሁንና ቁጥጥር እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም።

ለምሳሌ በጂግጂጋ በኩል ድንበሩ ሰፊ ነው። ለቁጥጥር ፈተና የሚሆነውም ለዚሁ ነው።

“እዚያ አካባቢ እንሰሳት አቅራቢዎችን አግኝተን ነበር። ለምን ለአገር ውስጥ ገበያ ከብቶቻችሁን አታቀርቡም ስትላቸው በዶላር እንሸጠዋለን ይላሉ።”

በዚህ የተነሳ “ትውልደ ኢትዮጵያዊ” እንሰሳት በገፍ ይሰደዳሉ።

በአሳኢታ ወደ ጂቡቲ፣ በሁመራ መተማ ወደ ሱዳን፤ በደገሃቡር፣ በቶጎ ጫሌ ወደ ሐርጌሳ እና ሶማሊያ፤ በሞያሌ በኩል ደግሞ ወደ ኬንያ።

“የሚገርመው ኬንያ እና ሶማሊያ ካላቸው እንሰሳት በላይ ወደ ውጭ ይልካሉ፤ የሌላቸውን ከየት አምጥተው መሰለህ የሚልኩት? ከኢትዮጵያ በድንበር በኩል ከብት ስለሚወጣ ነው” ይላሉ አቶ አብረሃም።

ጠቦትን በዶላር መለወጥ

ከኢትዮጵያ የእርድ ሥጋ ብቻ አይደለም ወደ ውጭ የሚላከው።

በግ እና ፍየል በቁማቸው ወደ ውጭ ይላካሉ።

የቁም ከብት ወጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ 41 ሕጋዊ ድርጅቶች ተመዝግበዋል። ዘርፉም የቁም እንሰሳት የውጭ ንግድ ይባላል።

ነገር ግን ደላሎች ለእነዚህ ሕጋዊ ላኪዎች ከብቶቹን ከመሸጥ በድንበር አውጥቶ በሕገ ወጥ መሸጥ ያዋጣናል ይላሉ።

ይህን በቀላሉ ለመረዳት የእርድ ሥጋን ዋጋ ማነጻጸር በቂ ነው።

ለምሳሌ የእርድ ሥጋ በሰሞኑ ገበያ ወደ ውጭ ሲላክ በኪሎ 6 ዶላር ነው የሚሸጠው።

ይህ ደግሞ በ300 ብር ኪሎ ሥጋ መሸጥ ማለት ነው።

አገር ውስጥ ኪሎ ሥጋ ከ700 መቶ ብር በላይ ነው የሚሸጠው።

ይህ ላኪዎችን የሚያበረታታ አይደለም።

የቁም ከብትም ተመሳሳይ ነው።

ፍየል በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ወጥቶ ሲሸጥ ዶላሩ በጥቁር ገበያ ስለሚሰላ እጥፍ ገቢ ያስገኛል።

አቶ ከሊፋ ሁሴን የአላና ግሩፕ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

ድርጅታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ሥጋን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች አንዱ ነው።

እንሰሳት በቁጥር ደረጃ አለ ይባላል እንጂ ለገበያ የሚሆን ብዙ ቁጥር የለንም ይላሉ።

“ለምሳሌ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ 70 ሚሊዮን ከብት አለ ይላል። ከዚህ ውስጥ ግን 70 ከመቶው ሴት ነው። ያ ማለት ለእርድ አይውልም ማለት ነው። በጎችም ፍየሎችም ላይ እንደዚያ ነው።”

ወደ ዕድሜ፣ ክብደት፣ የደንበኛ ፍላጎት ሲኬድ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም እያነሰ እንደሚሄድ ያወሳሉ።

በዚህ የተነሳ ለእርድ የሚቀርበው የእንሰሳት ቁጥር አነስተኛ እየሆነ ይመጣል።

ለአቶ ከሊፋ የቁም ከብት ኮንትሮባንድን በተመለከተ ዋናው ገፊ ምክንያት ግን የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ነው። ዶላር በጥቁር ገበያ ያለው ተመን ከባንክ ተመን እጥፍ መሆኑ ዘርፉን እየፈተነው ነው።

በዚህ የተነሳ አሁን ባለው ሁኔታ ለአገር ውስጥ ሥጋን ማቅረብ ወደ ውጭ ከመላክ የበለጠ ትርፍ ያስገኛል።

ይህም በቁም ከብት ላይም ይንጸባረቃል።

አቶ ከሊፋ የኮንትሮባንድ ሰንሰለቱን ሲያስረዱ ቦረና፣ ባሌ፣ ጉጂ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጂንካ ኮንሶ አካባቢዎችን አብረው ያነሳሉ።

ንግዱ የሚካሄደው በደረጃ ነው። መጀመሪያ አርሶ አደሩ ከየቦታው እንሰሳቱን እየነዳ ገበያ ይሄዳል።

ይህ የመጀመርያ ደረጃ ገበያ ይባላል።

አነስተኛ ነጋዴዎች ከዚህ ገበያ 20ም፣ 30ም ይገዙና ብዙ ነጋዴዎች የሚገኙበት መካከለኛ ገበያ ይወስዷቸዋል።

በመካከለኛ ገበያ ደግሞ ከብቶችን ገዝተው ለቄራ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ይገኛሉ።

“እነሱ ከብቶችን ይገዙና ለትላልቅ አቅራቢዎች ይሸጡላቸዋል። ትላልቅ አቅራቢዎች ደግሞ ለእኛ ለትላልቅ ደርጅቶች ያቀርቡልናል።”

“በዚህ መካከል መአት ደላላ ነው ያለው። በሁሉም ደረጃ።”

በዚህ ሂደት ለትልልቅ ሥጋ ላኪዎች ማቅረቡን ትተው ወደ ድንበር የሚወሰዱ የበግ እና የፍየል ደላሎች ይኖራሉ።

በሕጋዊው መሥመር ሲሆን ደግሞ የቁም እንሰሳት ኤክስፖርት በሚሆኑበት ጊዜ የኳራንቲ ጊዜ አለ፤ ከበሽታ ነጻ ስለመሆናቸው ለአንድ ወር ይታያሉ።

ለበግ እና ለፍየል እስከ 21 ቀን።

ክትባት እየተሰጣቸው ከበሽታ ነጻ መሆናቸው ይረጋገጣል። በዚህ ሂደት መኖው የላኪው ወጪ ነው።

ይህ በብዛት አዳማ እና ሚሌ አካባቢ ነው የሚካሄደው።

ከዚህ ሂደት በኋላ ጂቡቲ ይወሰዳሉ። ጂቡቲም ኳራንቲን ይገባሉ።

ጂቡቲ በድጋሚ ኳረንቲን የሚገቡት በሁለት ምክንያት ነው።

አንዳንዴ ገዢ አገራቱ የጂቡቲን ሰርተፍኬት ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ሲባል ይገባሉ። በብዛት ግን ተቀባይ አገራት ያን ባይጠይቁም ጂቡቲዎች በጫና በግና ፍየሎቹን ኳረንቲን እንዲገቡ ያደርጋሉ።

ይህ ላኪዎችን ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳርጋቸዋል። የጂቡቲ ነጋዴዎችን ኪስ ያደልባል። ምክንያቱን በጂቡቲ በከብት ለማቆያ እስከ 30 ዶላር ስለሚከፈል ነው።

ሁሉም ሕጋዊ የቁም ከብት ላኪዎች ይህን ሂደት ያልፋሉ። ለብዙ ድካምና እንግልት የሚዳርጋቸው ይህ አሠራር ነው።

የከብት ኮንትሮባንዲስቶች በዚህ ረዥም ሂደት ማለፍ ይታክታቸዋል።

ስለዚህ ከብቶቻቸውን ከተመቸ በእግር እየነዱ አልያም በአይሱዙ መኪና ጭነው ከአገር ያስወጧቸዋል።

መንገድ ላይ ከበት እየነዱ መሄድ በብዙ ኬላዎች ፍተሻን ያስከትላል። ነገር ግን ኮንትሮባንዲስቶች ወዴት ነው ሲባሉ ወደ ማቆያ እያሉ ይነዳሉ።

“ቁጥጥር ይደረጋል ይባላል፤ ሆኖም በቁጥጥር የሚያዘውም እጅግ በጣም አነስተኛው ነው።”

አቶ ከሊፋ እንዲያውም ነገሩ በቁጥጥር የሚቆም ነገር ሆኖ አይታያቸውም። እርሳቸው ዋናው የችግር ምንጭ የሚሉት በሽያጩ ሂደት ያለው የውጭ ምንዛሪ ልዩነት ነው።

ይህን በተጨባጭ ያስረዱናል።

“እኛ ለምሳሌ ስንገዛቸው በብር ነው። የምንገዛቸው የባንክ ተመንን መሠረት አድርገን ነው” ይላሉ አቶ ከሊፋ።

“ፍየል 2500 ብር ብንገዛቸው፤ በ50 ዶላር ገዛናቸው ማለት ነው። በትይዩው (ጥቁር) ገበያ የውጭ ምንዛሪ 90 እና መቶ ብር ደርሷል። በኮንትሮባንድ ፍየሉን 50 ዶላር ቢሸጡት እስከ 5ሺህ ብር መነዘሩት ማለት ነው።”

ከዚያ በዶላሩ ሌላ ዕቃ ገዝተውበት ይመለሳሉ። ትርፉ አይወዳደርም፤ ከነችግሩም ኮንትሮባንድን የሚመርጡትም ለዚሁ ነው።

የቁም ከብት ኮንትሮባንድ ከወርቅ ኮንትሮባንድ ጋር የሚመሳሰል ነው።

ወርቅ አቅራቢያው ኢንሴንቲቭ ካገኘ ሕገ ወጥ የወርቅ ንግዱን በጉልህ ይቀንሰዋል። ከሰሞኑ ብሔራዊ ባንክ ይህን በማድረጉ መሻሻል ታይቷል።

“ለቁም እንሰሳትም ይህ ተመሳሳይ ማሻሻያ ካልተወሰደ በዘላቂነት ይቀንሳል የሚል ግምት የለኝም” ይላሉ አቶ ከሊፋ።

የኢትዮጵያን ከብቶች ለዓለም የምታቀርበው አገር

አቶ ደስነት በዚህ ሕገ ወጥ የቀንድ ከብቶች ዝውውር ዙርያ ጥናት የሠሩ ባለሙያ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ዉጫሌ፣ ጋሻሞ፣ ጎላዲ፣ ፈርፈር፣ በምሥራቅ፤ ዶሎ ኦዶ እና ሞያሌ በደቡብ፣ ኦኮቦ፣ ባምቦዴዬ ኩምሩክ ሁመራ እና አልማሃል በምዕራብ ዋነኞቹ የኮንትሮባንድ መስመሮች ናቸው።

አቶ ደስነት እንደሚሉት አንዱ ችግሩ እንዳይቀንስ ያደረገው ክልሎች እና የከተማ መስተዳደሮች ከፌዴራል ጋር በቅንጅት አለመሥራታቸው ነው።

“ክልሎች በቁም እንሰሳት ሕገ ወጥ ግብይት ላይ በቂ ቁጥጥር አያደርጉም” ይላሉ።

ሌላው ይቅርና በክልሎች ተገንብተው ያለቁትን የቁም እንሰሳት የኳረንቲን ማዕከላትንም ሥራ አላስጀመሯቸውም።

የሕጋዊው መንገድ ቢሮክራሲ ረዥም መሆኑ ደግሞ ከአገራችን የቁም እንሰሳት በሕገ ወጥ እየወጡ በድጋሚ ለሚልኩ አገራት እንዲሸጡ አድርገዋቸዋል ባይ ናቸው አቶ ደስነት።

አቶ ከሊፋ ይህን የሚያጠናክር ሌላ ማስረጃን ያቀርባሉ።

ጎረቤት አገራት ካላቸው የቁም ከብት የበለጠ ወደ አረብ አገራት መላክ የቻሉት ይህ ሕገወጥ መንገድ በመኖሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ለምሳሌም፤ ሶማሌላንድ 5 ሚሊዮን የቁም እንሰሳት በዓመት ወደ አረብ አገራት ትልካለች፤ ከዚያ ውስጥ 60 ከመቶ ከእኛ እንደሚሄድ ጥናቶች ያሳያሉ።”

ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ለመስጠት በኤሜይል እና በስልክም ከቢቢሲ ቢጠየቅም ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም።

የከብቶቻችን ስደት ግን ቀጥሏል።

ምናልባትም በቀን አያሌ የቁም እንሰሳት ከመሀል አገር ሳይቀር ተነስተው በጂግጂጋ አድርገው በውጫሌ በኩል ወደ ሐርጌሳ ይገባሉ።

መዳረሻቸው ሳዑዲ አረቢያ፣ ዱባይ፣ የመን፣ ኦማን ወይም ባሕሬን ነው የሚሆነው።

የዜጎችን ስደት ማስቆም አዳጋች ሆኖ ቢያቅትም፣ ኢትዮጵያ የገዛ ከብቶቿን ማገድ እንዴት ተሳናት?