የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሕጻናት ተመልምለዋል መባሉን አጥብቆ አወገዘ

የአውሮፓ ሕብረት

የፎቶው ባለመብት, THE EUROPEAN PARLIAMENT

የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሕጻናት ለጦርነት ተመልምለዋል መባሉን አጥብቄ አወግዛለሁ አለ።

ፓርላማው በኢትዮጵያ ጉዳይ ከተወያየ በኋላ ትናንት ሐሙስ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ባውጣው የውሳኔ ሃሳብ የጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በተወሰኑ አካላት ልጆች ለጦርነት ተመልምለዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸው የሚወገዝ ነው ብሏል።

ፓርላማው በመግለጫው የጠቀሰው ሪፖርት የትኞቹ ተዋጊ ኃይሎች ሕጻናትን በጦር ግንባር እንዳሰለፉ ያለው ነገር ባይኖሩም የሰሜን ኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ግን ሕጻናትን ነፍጥ በማስነገብ አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ፣ ሄይቲ እና ማይናማር ተወያይቶ ባወጣው የውሳኔ ሐሰብ ላይ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።

የኅብረቱ ፓርላማ ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ በትግራይ እና በአዋሳኝ ክልሎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቋል።

“በግጭት በተጎዱ ስፍራዎች ላሉ በሙሉ የተሟላ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት ፍላጎት ነው” ይላል ትናንት የወጣው የውሳኔ ሐሳብ።

የኅብረቱ ፓርላማ ሰላማዊ ሰዎችን ሆነ ብሎ ዒላማ ማድረግ እና ሕጻናትን ለውትድርና መመልመል ከጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር እንደሚስተካከል አስታውሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሕብረቱ የኢትዮጵያን የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ካሉት ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት ሦስት ልጆች አንዱ የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥመው ገልጿል።

ከሕጻናቱ በተጨማሪ የትግራይ ነብሰ ጡር ከሆኑ እና ከሚያጠቡ እናቶች መካከል ገሚሱ የምግብ እጥረት ተጠቂ ናቸው ብሏል።

በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ከትምህርት የተቆራረጡ ሕጻናት ቁጥር ደግሞ 1.39 ሚሊዮን መሆኑን የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አስታውቋል።

ኅብረቱ ባውጣው የውሳኔ ሐሳብ ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የኅብረቱ ፓርላማ የተባበሩት መንግሥት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ላለው ችግር መፍትሄ መስጠት አለመቻሉ እጅጉን የሚያስቆጭ ነው ያለ ሲሆን፤ የፓርላማው አባላት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ ሰላማዊ ሰዎች እንዲጠበቁ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙት ለሕግ እንዲቀርቡ ትርጉም ያለው እና ወሳኝ እርምጃዎችን እንዲስድ ያሳስባሉ ብለዋል።