በደቡብ አፍሪካ የፌደራል መንግሥቱን እና ህወሓትን የሚያደራድሩት ይፋ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎችን መካከል የሚደረገውን ንግግር የሚመሩት ግለሰቦች ይፋ ሆኑ።
በመጪው ጥቅምት ወር መብቂያ ላይ ሁለት ዓመት በሚደፍነው ጦርነት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ወገኖች፣ ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሚያስችላቸውን ንግግር በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ በደቡብ አፍሪካ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ለወራት ሰላም እንዲወርድ ጥረት ሲያደርግ የነበረው የአፍሪካ ኅብረት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ፣ የትግራይ ኃይሎች እና የፌደራሉ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ተገኝተው ንግግር እንዲጀምሩ የግብዣ ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ከአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለሚካሄደው የሰላም ድርድር የቀረበለትን ግብዣ መቀበላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ሁለቱም ወገኖች ለኅብረቱ ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን አድንቀው፣ ለሰላም ዕድል እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህን ድርድር የአፍሪካ ኅብረት በበላይነት የሚመራው ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት ተወካዮችን የሚያደርጉትን ንግግር የሚመሩት እነማን እንደሆኑ ሐሙስ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሠረት የአደራዳሪ ቡድኑ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ናግኩካ የሚመራ ይሆናል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ አደራዳሪዎቹ ሰፊ ልምድ እና የአመራር አቅማቸውን በመጠቀም ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዘላቂ እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ገንቢ ውይይት ማድረግ እንደሚያስችሉ ሙሉ መተማመን እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት እና ኡሁሩ ኬንያታ
ከዚህ ቀደም የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋር የሚያደርገው ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ብቻ እንደሚሆን ሲገልጽ ቆይቷል።
የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥራ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ለመነጋገር የቀረበላቸውን ጥሪ ከመቀበላቸው በፊት ድርድሩ ከኅብረቱ ይልቅ በኡሁሩ ኬንያታ እንዲመረ ፍላጎት ነበራቸው።
ይሁን እንጂ የትግራይ ኃይሎች መስከረም 01/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የአቋም ለውጥ በማድረግ በአፍሪካ ኅብረት የመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን በአፍሪካ ኅብረት የቀረበው ግብዣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቁ በመሆናቸው በድርድሩ ለመሳተፍ ፈቃደኝነቱን መግለጹ ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎችም የቀረበላቸውን የሰላም ንግግር ግብዣን እንደተቀበሉ አሳውቀው፤ ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን የውይይት ተሳታፊዎችን፣ ታዛቢዎችን እና ዋስትናን ሰጪዎች እንዲሁም ለሚልኩት ተደራዳሪ ቡድን የጉዞ፣ የደኅንነት ዝግጅቶች እና ሎጂስቲክስን በተመለከተ ለኅብረቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
የህወሓት እና የመንግሥት ተደራዳሪዎች
በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሰላም ንግግር ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ወክለው እነማን በአካል እንደሚገኙ በግልጽ ባይታወቅም፤ ባለፈው ዓመት ግን ሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎቻቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪ ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ሰባት አባላትን ያካተተ መሆኑን መንግሥት ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጎ ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪ ቡድን አባላት 7 ናቸው።
እነዚህም የተደራዳሪ ቡድኑ አባላቱ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌ/ጀነራል ብርሃኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) እና አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር ናቸው።
ህወሓት በበኩሉ ሁለት አባላት ያሉትን የተደራዳሪ ቡድን አባላት ይፋ አድርጎ ነበር። እነዚህም የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ የጦር አመራር የሆኑት ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እና የህወሓት ቃል አቀባይ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ጌታቸው ረዳ ናቸው።












