ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቢዮንሴ ያልተለቀቀ ሙዚቃ የመኪና መስታወት ተሰብሮ መሰረቁ ተገለጸ
የታዋቂዋ አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ቢዮንሴ ያልተለቀቁ ዘፈኖችን ጨምሮ ላፕቶፕ እና ሌሎች በርካታ ዕቃዎች በአትላንታ ከመኪና ውስጥ መሰረቃቸው ተገለጸ።
ካውቦይ ካርተር የተሰኘ አልበሟ ጋር ተያይዞ የሙዚቃ ጉዞ ላይ ያለችው ሙዚቀኛዋ በአትላንታም የተገኘችው ለኮንሰርት ነው።
ከሙዚቃ ዝግጅቱ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎም ዘፈኖቿን የያዘው ሃርድ ዲስክ ከኪራይ መኪና ተሰርቋል ተብሏል።
ሃርድ ዲስኩ የቢዮንሴ ያልተለቀቁ ዘፈኖችን፣ የሙዚቃ ጉዞ የጊዜ ሰሌዳዎችን፣ የኮንሰርት ዕቅዶችን ይዞ እንደነበር የሙዚቀኛዋ አንደኛው ዳንሰኛ እና የዳንስ ዝግጅት አቀናባሪ መናገራቸውን ከፖሊስ ሪፖርት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ቢዮንሴ በአትላንታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምታደርገው የሙዚቃ ዝግጅት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ፣ ሐምሌ 1/ 2017 ዓ.ም መሰረቁ ተገልጿል።
የአትላንታ ፖሊስ የእስር ማዘዣ መውጣቱን ቢገልጽም የተጠርጣሪ ስም ይፋ አልተደረገም።
የዳንስ ዝግጅት አቀናባሪ ክርስቶፈር ግራንት እና ዳንሰኛው ዲያንደር ብሉ የተከራዪትን ጥቁር ጂፕ መኪና አቁመው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የምግብ አዳራሽ መግባታቸውን ለፖሊስ ተናግረዋል።
ግለሰቦቹም ሲመለሱ የመኪናቸው የኋላ መስኮት ተሰብሮ ሁለት ቦርሳዎች መወሰዳቸውን የፖሊስ ሪፖርት ያሳያል።
ግለሰቦች ለፖሊስ እንደተናገሩት እነዚህ ቦርሳዎች " የሙዚቀኛዋ ቢዮንሴን ግላዊ መረጃዎችን ይዘው እንደነበር" ነው።
ከነዚህም ውስጥ "የኮምፕዊተር መለያ የተጫነባቸው ዘፈኖች፣ ያልተለቀቁ ዘፈኖች፣ ያለፉ እና የወደፊት የሙዚቃ ዝግጅትን ዕቅድ የያዘ ቪዲዮ፣ እና የዝግጅቶች የጊዜ ሰሌዳን የያዙ አምስት ሃርድ ዲስኮች መሰረቃቸውን " የፖሊስ መረጃ ያሳያል።
የቢዮንሴ "ካውቦይ ካርተር" የተሰኘው አልበም የተለቀቀው ባለፈው ዓመት ነው።
ሌሎች ከመኪና የተሰረቁ እቃዎች ላፕቶፕ፣ ቅንጡ አልባሳት እና የሙዚቃ የጆሮ ማዳመጫ 'አፕል ኤርፖድስ' ይገኙበታል።
ባለስልጣናቱ በላፕቶፕ እና በሙዚቃ የጆሮ ማዳማጫዎች ላይ የተገጠሙ የክትትል መረጃዎችን ተጠቅመው የት እንዳሉ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም የፖሊስ ሪፖርት አትቷል።
ፖሊስ በተጨማሪም ከተሽከርካሪዎች ላይ የጣት አሻራዎችን ለማግኘት እየሞከሩ ሲሆን "ሁለት ደብዘዝ ያሉ አሻራዎች" መገኘታቸው ተገልጿል።
የተሰረቁት እቃዎች ስለመገኘታቸው የተባለ ነገር የለም።
ቢዮንሴ 'ካውቦይ ካርተር' የሙዚቃ አልበሟ ጋር በተገናኘ የሙዚቃ ጉዞ በአትላንታ እያደረገች ነው።
ከአምስት ቀናት በፊት የጀመረው የሙዚቃዋ ዝግጅት በትናንትናው ዕለት ይጠናቀቃል።
ባለቤቷ ራፐር ጄይዚ በቢዮንሴ የሙዚቃ ዝግጅት በሶስተኛው ዕለት በድንገት መድረክ ላይ መጥቶ ነበር።