ዩቲዩብ "በብዛት ለሚመረቱ" እና "ተደጋጋሚ" ይዘቶች ክፍያ መፈጸም ሊያቆም ነው

ግዙፉ የቪድዮ ማሰራጫ መድረክ ዩቲዩብ፤ "በብዛት የተመረቱ" እና "ተደጋጋሚ" ቪድዮዎችን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከማስታወቂያ ገቢ መጋራት ስርዓት እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ሰው ሠራሽ አስተውህሎትን (ኤአይ) በመጠቀም የሚሰሩ ይዘቶችን ከዩቲዩብ የክፍያ ስርዓት እንደሚያስወጣ ተገምቷል።

ዩቲዩብ ይፋ ባደረገው አዲስ ፖሊሲ ከሚቀጥለው ሳምንት ሐምሌ 8/2017 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ሁለት ማሻሻያዎችን አስተዋውቋል።

የመጀመሪያው ማሻሻያ ይዘት ፈጣሪዎች "የተጋለጠ ቆዳ" የሚታይበት ማስታወቂያ በቪድዮዎቻቸው ላይ እንዳይታይ ማድረግ የሚችሉበትን አማራጭ ያስወገደ ነው።

ይህ አማራጭ ይዘት ፈጣሪዎች በሚለቁት ቪድዮ የሰውነት ክፍሎች የተጋለጡበት ማስታወቂያ በይዘቶቻቸው ላይ እንዳይተላለፍ ለመገደብ ይጠቀሙበት ነበር።

በአዲሱ ፖሊሲ ይህ አማራጭ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን በምትኩ ወሲብ ነክ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን በሚለቁት ቪድዮ ላይ እንዳይታይ ማድረግ የሚችሉበትን "ሪፈረንስ ቱ ሴክስ" የተባለ አማራጭ መጠቀም እንደሚችል ኩባንያው ገልጿል።

ሁለተኛው ማሻሸያ፤ ተቋሙ በዩቲዩብ ቪድዮዎች ላይ ከሚተላለፈው ማስታወቂያ የሚገኘውን ገቢ ከይዘት ፈጣሪዎች ጋር ለሚጋራበት "ዩቲዩብ ፓርትነር ፕሮግራም" የተሰኘ ስርዓት ብቁ የሚሆኑ ቪድዮዎች ላይ የተቀመጠውን መስፈርት ያጠበቀ ነው።

ዩቲዩብ ከዚህ ቀደም በነበረው ፖሊሲም ይዘት ፈጣሪዎች ለዚህ ፕሮግራም ብቁ ሆነው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው "ኦርጅናል" እና "እውነተኛ" ቪድዮዎችን እንዲለቅቁ እንደሚያስገድድ አስታውሷል።

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ይህንን መስፈርት ቁጥጥር የሚያደርግበትን አሰራር እንደሚያሻሽል ገልጿል።

አዲሱ ማሻሻያ የሚደረገው "በብዛት የተመረቱ እና ተደጋጋሚ ይዘቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመለየት" እንደሆነ ኩባንያው አብራርቷል።

"ይህ ማሻሻያ ዛሬ ላይ 'እውነተኛ ያልሆነ' ይዘት ምን እንደሚመስል በተሻለ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ነው" ብሏል።

ኩባንያው ይህንን ማሻሻያ በግልፅ ባያብራራም "ዛሬ ላይ 'እውነተኛ ያልሆነ' ይዘት" የሚለው የኩባንያው አገላለጽ በሰው ሠራሽ አስተውህሎት (ኤአይ) የሚሰሩ ቪድዮዎችን ሊያመለክት እንደሚችል ተገምቷል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የኩባንያው ፖሊሲ "እውነተኛ ያልሆነ" በሚል ምድብ በብዛት ያመለክት የነበረው የሌሎች ሰዎችን ቪድዮ መልሶ የመለጠፍ ተግባርን ነው።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ቪድዮዎችን በጥራት የሚሰሩ የኤአይ ሞዴሎች ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ ዩቲዩብ እና ቲክቶክን ጨምሮ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በእነዚህ መገልገያዎች የተሰሩ ቪድዮዎች በብዛት እየተለቀቀባቸው ነው።

በኢትዮጵያም ካለፈው ወር አንስቶ በተለይም በቺፓንዚ እንዲሁም ቃለ መጠይቅ በሚደረግላቸው ሰዎች ገጸ ባህሪዎች የተሰሩ የኤአይ ቪድዮዎች ቲክቶክ እና ፌስቡክ ላይ በብዛት ተሰራጭተዋል።

እነዚህ ቪድዮዎች በብዛት አስቂኝ ይዘት ያላቸው ሲሆን አልፎ አልፎም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ትችቶችን የሚያቀርቡ ሆነው ተስተውለዋል።

አዲሱ የዩትዩብ ፖሊሲ ከክፍያ ስርዓቱ ከሚያስወጣቸው ቪድዮዎች ውስጥ፤ "በኤአይ የተፈጠሩ ይዘቶች፤ በተለይም በኤአይ የተፈጠሩ ድምጾች ላይ የሚመረኮዙ ወይም በአነስተኛ ቪድዮ ኤዲቲንግ [በድጋሚ የሚጫኑ] የሌሎች ሰዎች ይዘቶች" እንደሚገኙበት የሕንዱ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋዜጣ ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ ዘግቧል።