ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብራዚል ፖሊስ በአሜሪካዊቷ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የቦምብ ጥቃት አከሸፈ
በብራዚል የሪዮ ዲ ጄኔሮ የሲቪል ፖሊስ እና ፍትህ ሚኒስቴር በጋራ በቤት ውስጥ የተሰራ ተቀጣጣይ ፈንጂን በመጠቀም ጥቃት ለማድረስ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ዕውቅና ለማግኘት አስበው የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገለፁ።
ፖሊስ ጥቃቱን ያቀደውን እና አንድ ታዳጊን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
የድምጻዊት ሌዲ ጋጋ ቡድን ስለጥቃቱ ከሙዚቃ ዝግጅቱ በኋላ ማለዳ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ገልጸዋል።
በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ካፓካባና የባሕር ዳርቻ የሌዲ ጋጋን የሙዚቃ ድግስ በነጻ ለመታደም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መገኘታቸው ተገልጿል።
ፖሊስ ጥቃቱን ለመፈፀም ያሰበው ቡድን በሕጻናት፣ አዋቂዎች እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ የጥላቻ ንግግር ሲያሰራጭ ነበር ብሏል።
ጥቃቱን አቀነባብሯል በሚል በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ በሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ደቡባዊ ግዛት ሕገወጥ የጦር መሳርያ ይዞ በመገኘት በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ታዳጊው ደግሞ በሪዮ ሕጻናት የሚታዩበት የወሲብ ፊልም በማከማቸት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ያውቃል።
ጥቃቱን ለመፈጸም ያቀዱት ግለሰቦች ታዳጊዎችን አክራሪ እንዲሆኑ በመቀስቀስ እንዲሁም "የአንድ ቡድን አባል መሆናቸውን ለመግለጽ እና ሌሎች ወጣቶችን ለማነሳሳት" በሚል ራሳቸውን እንዲጎዱ እንዲሁም ጸብ ቀስቃሽ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ተወንጅለዋል።
የሌዲ ጋጋ ቃል አቀባይ ለ ዘ ሆሊውድ ዘጋቢ "ሊደርስ ነበር ስለተባለው ጥቃት የሰማነው ዛሬ ማለዳ ከመገናኛ ብዙኃን ነው። ከትርዒቱ አስቀድሞም ሆነ በሚታይበት ወቅት ምንም ዓይነት የታወቀ የደህንነት ስጋት አልነበረም። እንዲሁም ለሌዲ ጋጋ ከፖሊስም ሆነ ከባለስልጣናት ሊኖር ስለሚችል ጥቃት የደረሰ መረጃ የለም" ብሏል።
የፍትህ ሚኒስቴር ተጠርጣሪዎቹ ራሳቸውን "ሊትል ሞንስተርስ" ሲሉ የሚጠሩት የድምጻዊት ሌዲ ጋጋ አድናቂዎች ነን እንደሚሉ ገልጿል።
ፖሊስ በሪዮ ዲ ጄኔሮ፣ ሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል እንዲሁም ሳኦ ፖሎ የመበርበርያ ትዕዛዝ ያወጣ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች እና ሌሎች መሳርያዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
የሪዮ ግዛት ደህንነት መስርያቤት በኦንላየን ታዳጊዎችን ለተለያዩ አመጾች የሚቀሰቅሱ እና ሚስጥራዊ ኮዶችን እና ትዕምርታዊ ምልክቶችን ስለሚጠቀም ቡድን መረጃ ከደረሰው በኋላ "ሐሰተኛ ሞንስተሮች ላይ የሚደረግ ዘመቻ" መጀመሩ ተገልጿል።
የድምጻዊቷ ግዙፍ የሙዚቃ ድግስ ነበር የተባለው የዚህ ኮንሰርት ወጪ የተሸፈነው "የሪዮን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት" በሚል በከተማዋ አስተዳደር ነው።
እንደ ባለስልጣናቱ ከሆነ ኮንሰርቱ 100 ሚሊዮን ዶላር የአገር ውስጥ ገቢን ያስገኛል ተብሎ ተገምቷል።
ሌዲ ጋጋ ቅዳሜ ዕለት በሪዮ ዲ ጄኔሮ ያቀረበችው የሙዚቃ ድግስ ስምንተኛውን አልበሟን የማስተዋወቅ አካል ነው።
ሜይሄም (Mayhem) በሚል የሚጠራው አዲሱ የሙዚቃ ሰንዱቋ፣ 'አብራካዳብራ' እንዲሁም 'ዳይ ዊዝ ኤ ስማይል' የተሰኙ ሙዚቃዎች የተካቱበት ነው።
ሌዲ ጋጋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 በብራዚል ዝግጅቷን አቅርባ ነበር።
በዝግጅቱ ላይ የሚታደሙትን ለመጠበቅም 5000 ፖሊሶች የተመደቡ ሲሆን ጥብቅ ፍተሻ እንደነበርም ተገልጿል።
የከተማይቱ ባለስልጣናት የፖሊስን ሥራ ለማገዝ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ፊትን የሚለይ ካሜራ ጥቅም ላይ አውለዋል።