ታሊባን ሴቶችን ከዩኒቨርሲቲዎች አገደ

ታሊባን በአፍጋኒስታን የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሴቶች ዝግ መደረጋቸውን በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ሌላ ማስታወቂያ እስከሚነገር ድረስ ዩኒቨርሲቲዎች ለሴቶች ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ አስታውቋል።

ሴቶችን ከዩኒቨርሲቲ የማገዱ ውሳኔው ወዲያው ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተነግሯል።

ቀደም ብሎ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለታገዱት ሴቶች አዲሱ ውሳኔ ከመደበኛ ትምህርት ይበልጥ የሚያርቃቸው ሆኖኗል።

በካቡል ዩኒቨርሲቲ የምትማር አንዲት ሴት ዜናውን ከሰማችበት ጊዜ ጀምሮ እያለቀሰች እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከሶስት ወራት በፊት በመላው አፍጋኒስታን በሺዎች የሚቆጠሩ ሴት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ፈተናን ወስደዋል።

ታሊባን ባለፈው ዓመት በአፍጋኒስታን ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ጾታን መሰረት ያደረገ መግቢያና መማሪያን ክፍልን አዘጋጅቷል።

ሴት ተማሪዎች መማር የሚችሉት በሴትና ዕድሜያቸው በገፋ ወንድ መምህራን ብቻ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራት አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አግዳውን በተመለከተ አስተያየት ስትሰጥ “ከወደፊቱ ህለሜ ጋር ሊያገናኘኝ የሚችለውን ድልድይ ሰብርውበታል” ብላለች።

“እንዴት ስሜቴን ልግለጸው? ተምሬ ህይወቴን እቀይራለሁ ወይም ህይወቴን ብሩህ አድረጋለሁ ብዬ አምን ነበር። ግን ይህንን እምነቴን ናዱብኝ” ስትል አክላለች።

ታሊባን ወደ ስልጣን ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ የአፍጋኒስታን የትምህርት ዘርፍ ክፉኛ ተጎድቷል። የአሜሪካ ጦር ከሀገሪቱ መውጣቱን ተከትሎ በርካታ ምሁራን አገሪቱን ለቀው ተሰደዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ውድ አዲሱን የታሊባንን ውሳኔ አውግዘዋል።

“ታሊባን የሁሉንም አፍጋኒስታናዊ መብት እስካላከበረ ድረስ ተቀባይነት ያለው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አካል ሊሆን አይችልም” ያሉት አምባሳደሩ “በተለይም የሴቶች ሰብአዊ እና መሰረታዊ መብቶች” ሊከበሩ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ታሊባን ከወራት በፊት እስላማዊ ህጎች አይከበሩም በሚል ሴቶች በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በሚገኙ መናፈሻዎች እንዳይገቡ አግዷል።