ሊዮኔል ሜሲ የኢንስታግራም ልጥፍ እና ሌሎች የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ክብረ ወሰኖችን ሰበረ

ሊዮኔል ሜሲ የአርጀንቲና ቡድን የዓለም ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ያጋራቸው የፎቶ ስብስቦች በኢንስታግራም ታሪክ ከፍተኛውን መወደድን [ላይክ] ያገኘ ሆኖ ተመዘገበ።

የአገሩን ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ክብር ያበቃው የ36 ዓመቱ ሜሲ ያጋራቸው የኢንስታግራም የፎቶግራፍ ስብስቦች ከ60 ሚሊዮን ከሚልቁ ሰዎች መወደድን አግኝተዋል።

ድንቅ በተባለው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ አርጀንቲና ፈረንሳይን በመለያ ምቶች በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቷ ይታወሳል።

ይህ የሜሲ የኢንስታግራም ልጥፍ ከዚህ በፊት ከፍተኛውን የመወደድ ምላሽ በማግኘት ክብረወሰን ይዞ ከነበረው የእንቁላል ምስል ከአንድ ሚሊዮን በላይ በልጧል።

ከሜሲ በፊት በኢንስታግራም ላይ በመወደድ ክብረወሰኑን የያዘው እንቁላል ምንም የተለየ ነገር ያልነበረው ሲሆን፣ በወቅቱ ክብረወሰኑን የያዘችውን ካይሊ ጀነርን ለመብለጥ ሰዎች ቅስቀሳ ያደረጉበት ምስል ነው።

በመዋቢያ እቃ ምርቶችን የነጠጠች ሀብታም የሆነችው ጀነር ክብረ ወሰኑን ይዛ የነበረው ከአራት ዓመት በፊት ኢንስታግራም ላይ የለጠፈችው የልጇ ፎቶ ነበር። በወቅቱ ፎቶው 18 ሚሊዮን ላይኮችን አግኝቶ ነበር።

በተጨማሪም ካይሊ ጀነር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ 300 ሚሊዮን ተከታዮችን በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት ስትሆን፣ ሜሲም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን ተከታዮች አፍርቷል።

ከጀነር በመቀጠል ክብረ ወሰኑን ይዞ የቆየው የእንቁላል ምስልን በኢንስታግራም ላይ በማውጣት ዝነኛ ያደረገው ማን እንደሆነ እና በፍጥነት ያን ያህል ተወዳጅነትን እንዴት ለማግኘት እንደቻለ ከግምት በስተቀር የሚታወቅ ነገር የለም።

አንዳንዶች በርካታ ተከታዮችን ለማግኘት በአንድ ድርጅት የተደረገ የገበያ ማማለያ ነው ሲሉ፣ ብሪታኒያዊው የግብይት ባለሙያ ክሪስ ጎድፍሬይ ከሌሎች ጋር በመሆን የፈጠሩት እንደሆነ ይናገራል። ዋነኛ ዓላማውም የተቻለውን ያህል ላይክ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር።

በዚህ ወቅት የእንቁላሉ ምስል በአጠቃላይ 56 ሚሊዮን መወደድን በማግኘት የጀነርን ክብረወሰን ሰብሮ ይዞት ቆይቷል። አሁን ግን የዓለም ዋንጫን ድል ተከትሎ ክብረወሰኑ በሜሲ እጅ ገብቷል።

ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማብቃት በኋላ የዓለም የክብረ ወሰን መዝገብ የሆነው ጊነስ በባለድሉ ሊዮኔል ሜሲ የተሰበሩ ክብረ ወሰኖችን መመዝገቡን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በጀርመኑ ሉተር ማቲያስ ተይዞ የነበረውን በበርካታ የዓለም ግጥሚያዎች በመሳተፍ ክብረ ወሰን ሜሲ ተረክቦታል። በተጨማሪም በበርካታ የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎች የጨዋታዎች ኮከብ በመሆን፣ በአምበልነት በበርካታ የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎች በመጫወት እና በሌሎችም ክብረወሰን እንደያዘ ተመዝግቧል።