ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በወንጀል ይከሰሱ የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ ቀጣይ ዕጣቸው ምን ሊሆን ይችላል?
ታኅሣሥ ማብቂያ 2013 ዓ.ም. በአሜሪካ መንግሥት የምክር ቤት ሕንጻ ካፒቶል ሂል ላይ የተፈጸመውን ወረራ ሲመረምር የቆየው ከኮንግረስ አባላት የተወጣጠው ኮሚቴ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወንጀል ክሶች መጠየቅ አለባቸው ማለቱ ይታወቀል።
ክስተቱን ሲመረምር የቆየው ኮሚቴ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው በርካታ የፌደራል ሕጎችን በመተላለፍ በአመጽ የካፒቶል ሂል ሕንጻ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ አነሳስተዋል እንዲሁም ደግፈዋል ብሏል።
“የታኅሣሥ 28ቱ ክስተት ያለ እርሳቸው አይከሰትም ነበር” ይላል የምርመራው ማጠቃለያ ሪፖርት።
የኮሚቴ አባላቱ ዶናልድ ትራምፕ ላይ አራት ክሶችን ለመመስረት በቂ ማስረጃ አለ ብለዋል። ትራምፕ ክስ ሊመሰረትባቸው የገባል ያሉት
ክሶቹ
- ይፋዊ መንግሥታዊ አካሄድን በማደናቀፍ
- ዩናይትድ ስቴስትን ለማጭበርበር በማሴር
- ሐሰተኛ አቋም ለማንጸባረቅ በማሴር እና
- አመጽን ማነሳሳት፣ መደገፍ ወይም አመጸኞችን በማበረታታ የሚሉት ናቸው።
ኮሚቴው ባለፉት ሁለት ዓመታት ለበርካታ ሰዎች ቃለ መጠይቅ አድርጎ፣ በርካታ ሰነዶችን አገላብጦ እና የቀረቡለትን ማስረጃዎች በርብሮ ከጨረሰ በኋላ ነው ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው።
የኮሚቴ አባላቱ ትራምፕ ከላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች መጠየቅ አለባቸው ባሏቸው ወንጀሎች ተከሰው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢያመራ፤ የቀድሞ ፕሬዝደንት እስከ 20 ዓመት በእስር ሊማቅቁ፣ ዳግም ለፖለቲካዊ ኃላፊነት ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ሊታገዱ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሊቀጡ ይችላሉ።
አሁን ትራምፕ ላይ ክስ የማቅረቡ ሥራ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አካል የሆነው የፍትሕ ቢሮ ኃላፊነት ይሆናል።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች የኮሚቴው ውሳኔ በትራምፕ ላይ ፖለቲካዊ እንጂ ሕጋዊ ትርጉም እምብዛም ነው ይላሉ።
ይህ ማለት ይላል የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ተንታኝ አንቶኒ ዙርከር፤ ትራምፕ ፍርድ ቤት በገንዘብ ወይም በእስር የመቀጣት ዕድላቸው አናሳ ነው።
ትራምፕ የተጋረጡባቸው ሕጋዊ ፈተናዎች
በእአአ 2024 ለዳግም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሳታፊ እንደሚሆኑት የገለጹት ትራምፕ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ሊገደቡ የሚችሉ ሕጋዊ ጉዳዮች ከፊታቸው ተጋርጠዋል።
ከታኅሣሡ የካፒቶል ሂል አመጽ በተጨማሪ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ከዋይት ሐውስ ከወጡ በኋላ ምስጢራዊ የሆኑ የመንግሥት ሰነዶችን በመኖሪያ ቤታቸው ከተገኘ በኋላ የሰነድ አያያዛቸውን እየመረመረ ይገኛል።
ይህ ብቻ አይደለም የጆርጂያ ግዛትም የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይፋ ከተደረገ በኋላ ትራምፕ የጆርጂያ ግዛት ኃላፊዎች ጋር ስልክ መደወላቸው የምርጫ ሕጎችን የተላለፈ እንደሆነ እየመረመ ይገኛል።
ትራምፕ ግን ይህ ሁሉ ምርመራ የሚካሄድባቸው ዳግም ወደ ፖለቲካው እንዳይመለሱ የሚደረግ ጥረት አካል እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ።
የኮንግረስ አባላት ኮሚቴ ያስላለፈው ውሳኔ በትራምፕ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት የማድረጉ ዕድል አነስተኛ ቢሆንም በፖለቲካ ሕይወታቸው ጫና ለበዛባቸው ትራምፕ ሌላ ራስ ምታት እንደሚሆን ግን እርግጥ ነው።
የቢቢሲው ተንታኝ አንቶኒ ዙርከር የመገናኛ ብዙኃን የኮሚቴውን ውሳኔ በስፋት መዘገባቸው አሜሪካውያን የታኅሣሥ 28ቱ ክስተት እንዳይዘነጉት የሚያደርግ ነው ይላል።
በቅርብ የተካሄዱ የሕዝብ አስተያየቶች በመላው አሜሪካ እንዲሁም በሪፐብሊካን ዘንድ የትራምፕ ተቀባይነት እየቀነሰ መምጣቱን አሳይቷል።
ከትራምፕ ይልቅ የፍሎሪዳው ገዢ ሮን ዲሳንቲስ ሪፐብሊካን ፓርቲ በመወከል በቀጣይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የመሳተፍ ዕድላቸው ሰፊ ነው እየተባለ ነው።