ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በረሃብ እና በመድኃኒት እጦት እየተሰቃዩ ያሉት የትግራይ ህጻናት
ትንሹ ሃፍቶም አምስት ዓመት ሊሞላው ነው።
ስሙ በትግርኛ ቋንቋ ሃብታም የሚል ትርጉም ቢኖረውም በረሃብ ምክንያት መንምኗል።
ዶክተሮቹ ልብሱን አውልቀው ሲመረምሩት የእጆቹ እና የእግሮቹ ሥጋ አጥንቱ ላይ መጣበቁ ይታያል።
በራሱ መቆም የማይችል ሲሆን፣ በሕይወትም ለመቆየት እየታገለ ይገኛል።
እናቱም ትርጉም ባጣ መልኩ ልጇ እየሆነው ያለውን ትመለከታለች።
ስሟንም ለቢቢሲ መናገር አልፈለገችም።
ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በተደቆሰችው ትግራይ ክልል የሰፈነው ረሃብ እና የምግብ እጦት የነዋሪዎች የየቀን እውነታ ሆኗል።
የሰላም ስምምነቱ ውጊያውን ቢያቆመውም የጦርነቱ ዳፋ ክልሉን እንዳጠለሸው ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት በነሐሴ ወር ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ከሦስቱ አንዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃይ ይፋ አድርጓል።
የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች እየተፋለሙ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደ ትግራይ የሚደረገውን እርዳታ በመገደብ ወይም በማገድ ክልሏን በሙሉ እገዳ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
ከህክምና ተቋማት ባዶ እጃችንን ተመለስን
ከጦርነቱ ጋር እኩል ዕድሜ ያላት ማክዳ እናቷ ሕይወት እቅፍ ውስጥ ጋደም ብላለች።
ሰውነቷ ላይ ሥጋ የሚባል ነገር የለውም ጎልቶ የሚታየው ያበጠው ሆዷ ብቻ ነው።
“ምግብ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መብላት በጣም ከባድ ነው” ትላለች ሕይወት።
በተለይም ሆስፒታል ከገባች ጀምሮ የማክዳ ሁኔታ እየከፋ መጥቷል።
“ልጄ በዚህ የከፋ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው መድኃኒት የለም ስለተባልን ነው። ምንም ነገር ማግኘት አልቻልንም” ትላለች ሕይወት።
“ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ በነበርንበት ወቅት ምንም ነገር ማግኘት ስላልቻልን ባዶ እጃችንን ወደ ቤታችን ተመለስን” ብላለች።
የሃፍቶም እና የማክዳ ቤተሰቦች በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀለ ህክምና ሲሹ ቆይተዋል። ቢቢሲ በዚህ ወቅት ባለፈው ወር ቤተሰቦቹን ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ እና ቀረጻ ሲያካሂድ ቆይቷል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች ተጨማሪ ግዛቶችን የተቆጣጠሩ ሲሆን የትግራይ ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል።
ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሚገኙ ባለሥልጣናት ተጨማሪ እርዳታ እንደሚልኩ ተናግረዋል።
‘የደረሰን መድኃኒት ለአንድ ቀን ብቻ ነው’
ዶ/ር ክብሮም ገብረሥላሴ በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል በቀዶ ህክምና ሃኪምነት ለ15 ዓመታት አገልግለዋል።
አይደር ሆስፒታል በክልሉ ውስጥ ላለው ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ትልቁ ሆስፒታል ነው።
“ትናንሽ ጨቅላ ህፃናት እና እናቶች በየቀኑ ሲሰቃዩ እና ሲያለቅሱ ማየት በጣም አሳዛኝ ነው” በማለት ዶክተር ክብሮም ይናገራሉ።
“ብዙ ህፃናት በሆስፒታላችን ተቀጥፈዋል። ምክንያቱም ልጆች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካጋጠማቸው ምግብ ብቻ ሳይሆን መድኃኒት፣ አንቲባዮቲክስ፣ ቫይታሚኖች ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ መድኃኒቶች በእኛችን የሉም” ይላሉ።
የተወሰኑ መሠረታዊ መድኃኒቶች በክልሉ ቢደርሱም በቂ ግን አይደሉም።
የዓለም ዓቀፉን ቀይ መስቀል ኮሚቴ የህክምና ቁሳቁስ የያዙ ሁለት የጭነት መኪናዎች መቀለ መድረስ ችለው ነበር።
“የደረሰልን የመድኃኒት መጠን ካሉን ህመምተኞች ውስጥ ለግማሾቹ የሚሆን እና ለአንድ ቀን ቀን ብቻ የቆየ ነበር” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።
እርዳታ ወደ ሆስፒታል ባልመጣባት በእያንዳንዷ ዕለትም በርካታ ታካሚዎች ይሞታሉ።
“የካንሰር ህሙማንን ብናይ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው። በመላው ትግራይ ምንም አይነት ኬሞቴራፒ የለም” ይላሉ ዶክተር ክብሮም።
“በእያንዳንዷ ቀን፣ ሳምንት እና ወር የካንሰር ህመማቸው ደረጃ እየተባባሰና እየከፋ ይሄዳል።”
“ከዚህ ቀደም መታከም የሚችልበት ደረጃ ላይ ከነበረ በአሁኑ ወቅት መዳን የማይችልበት ሁኔታ ላይ ላይ ነው። በከፋ ህመም ላይ ላሉ ሰዎች እያንዳንዷ ሰዓት ትርጉም አላት” ብለዋል።
የእርዳታ ጥረት
ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የረድዔት ድርጅቶች የምግብ እና የህክምና አቅርቦትን የያዙ ከ1 ሺህ 600 በላይ የጭነት መኪኖች መላክ መቻላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከኅዳር ወር ጀምሮ ቢያንስ 38 የጭነት መኪናዎችን ወደ መቀለ እንደላከ እና ሌሎችም በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።
“ሁሉም የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች ጥረቶችን እያደረጉ ቢሆንም ካለው ችግር ጋር ሲነጻጸር በቂ አይደለም” በማለት በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ቃለ አቀባይ ጁድ ፉህንዊ ተናግረዋል።
በክልሉ ያሉ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር አስከፊ ደረጃ ላይ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ 2.1 ሚሊዮን ለሚሆን የትግራይ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የማድረስ እቅድን ይዟል።
“ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ብዙ ነገር ተሻሽሏል” ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ እና የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር አስረድተዋል።
“ከሁለት ዓመት ግጭት በኋላ በአንድ ጀምበር ወደ መደበኛ ሁኔታ እንመለሳለን ብለን አንጠብቅም”ብለዋል።
ሽረና አካባቢውን የፌደራል ኃይሎች የተቆጣጠሩት ሲሆን መቀለ በትግራይ መንግሥት ቁጥጥር ስር ትገኛለች።
በአይደር ሆስፒታል ለህክምና የመጡና ጡረተኛው መምህር አቶ ፍቃዱ ጀምበር የስኳር ህመማቸውን ለማስታገስ መድኃኒት ባለፉት ሦስት ወራት ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
“ለህክምና ወደዚህ ስንመጣ አብዛኞቹ የህክምና መሳሪያዎች የሚሰሩ አይደሉም። በሁሉም ቦታ እየሞከርን ነው ነገር ግን በተጣለው እገዳ ምክንያት ምንም ማግኘት አልቻልንም” ይላሉ።
"በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች እየረገፉ ነው። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ መድኃኒት እንደምናገኝ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ምንም አልደረሰንም” በማለትም ያስረዳሉ።
በትግራይ ያሉ ዶክተሮች መሠረታዊ የሆኑ አቅርቦቶች የላቸውም።
“ቀዶ ጥገናዎችን ለማካሄድ የሚያስችሉ በቂ ጓንቶች የሉንም። እያጠብን እስከ ሦስት ጊዜ ለመጠቀም ተገደናል” ብለዋል ዶክተር ክብሮም።
“በባንካችን ውስጥ ደም ስለሌለን የደም ልገሳ ማድረግ አንችልም። ስለዚህም አንድ ታካሚ የደም ልገሳ የሚያስፈልገው መሆኑን ካወቅን ቀዶ ህክምና ማካሄድ አንችልም” ሲሉ አክለዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት መመለስ
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የዚሁ የአይደር ሆስፒታል ዶክተር እያገኙት ያለው መድኃኒትም ሆነ የህክምና ቁሳቁስ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
“ሆስፒታሉ በቆሰሉ ወታደሮች እና ሲቪል ታማሚዎች የተሞላ ነው” በማለት የሚናገሩት ዶክተሩ። “አብዛኞቹ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው አይደለም” ይላሉ።
የፌደራሉ ባለሥልጣናት ያደረጉት ብቸኛው አዎንታዊ ነገር መቀለ ላይ መብራት እንዲመለስ ማድረግ ብቻ ነው ይላሉ።
ሆስፒታሉ የኤችአይቪ መድኃኒቶች እና መመርመሪያ ቁሶች መምጣት መጀመራቸውን በቅርቡ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
ነገር ግን በርካቶች በህይወታቸው ከፍተኛውን ዋጋ ከፍለዋል።
“ለእሷ ለወደፊቱ የተሻለ ህይወት እንድትመራ እመኛለሁ። ማሰብ የምችለው እሱን ብቻ ነው” በማለት የማክዳ እናት ሕይወት ትናገራለች።