የጦር ቀጠና የሆነችው ትግራይ በጨለማ እንደተዋጠች የናሳ ምሥሎች አሳዩ

በምሽት ከሕዋ ላይ የተነሱ አዳዲስ ምሥሎች በጦርነት ቀጠና ያለችው የትግራይ ክልል ሕዝብ፣ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሰብአዊ ቀውሶች አስከፊውን እየተጋፈጠ መሆኑን አሳይተዋል።

በክልሉ የመብራት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ከተሞች በ20 ወራት ውስጥ እየደበዘዙና እየጨለሙ እንደመጡም የናሳ ሳተላይት ምሥሎች ማሳያ ናቸው።

የናሳ ሳተላይት ምሥሎች ለቢቢሲ የተጋሩት ከጎረቤት ኤርትራ ሠራዊት ጋር በመሆን ከትግራይ ጦር ጋር እየተዋጋ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የበላይነቱን እየተቀዳጀ በሚመስልበት ሁኔታ ነው።

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ትልልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችው የሽረ ከተማን ጨምሮ ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በስተደቡብ የሚገኙትን የአላማጣ እና ኮረም ከተሞችን መያዙን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎችም አገራትና ተቋማት በከባድ ሁኔታ ጦርነቱ መባባሱ ቀድሞውንም በነዋሪዎች ላይ አስከፊ የነበረውን ሁኔታ ወደ በለጠ ቀውስ ሊከተው እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

ቢቢሲ ከትግራይ ጤና ቢሮ ያገኘው አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው፤ ሰብአዊ እርዳታ፣ የባንክ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶችን ያቆመው በክልሉ ላይ የተጣለው እገዳ የሕጻናትን ሕይወት እየቀጠፈ ነው።

አኃዞቹ በባለፉት ሁለት ዓመታት በምግብ እጥረት የሞቱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላዎች ጦርነቱ ከመጀመሩ አራት ወራት በፊት ከነበረው በሚያስደነግጥ ሁኔታ በ1 ሺህ 533 በመቶ እንደጨመሩ ያሳያሉ።

የትግራይ ጤና ቢሮ መረጃን የሚመሩት ዶክተር ኮከብ ሐጎስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከሐምሌ 2013- ሐምሌ 2014 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 450 ሕጻናት በሆስፒታል ውስጥ ሞተዋል።

የጤና ባለሙያው ለቢቢሲ እንዳስረዱት ይህ አኃዝ መሬት ላይ ያለውን እውነተኛ ገጽታ በጭራሽ እንደማያሳይ ነው።

የጤና ሠራተኞች በነዳጅ እጥረት ምክንያት በክልሉ መረጃ አለመሰብሰብ አለመቻላቸው እንዲሁም የስልክ መስመሮችና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው መሬት ላይ ያሉ መረጃዎችን ለመሰብሰብ አዳጋች አድርጎታል ይላሉ።

ከክልሉ መረጃዎች ተሰብስበው ትራንስፖርት ሲገኝ ወደ ጤና ቢሮው መላክ ያለበት ሲሆን፤ በከፋ የተመጣጠነ የምግብ እጦት እየተሰቃዩ ያሉ 70 በመቶ ሕጻናት በመድኃኒት እጦት ምክንያት ሕክምና እንዳልተደረገላቸው ቢሮው መረጃ አግኝቷል።

በዚህ ዓመት ከሞቱ ሕጻናት መካከል አንዱ ሱራፌል ማዕረግ ነው። ቢቢሲ ስለ ሱራፌል ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አንድ ዘገባ ሠርቶ ነበር።

በወቅቱ የሦስት ወር ልጅ የነበረው ሱራፌል በምግብ እጦት መንምኖ ክብደቱ 2.3 ኪሎግራም ብቻ ነበር። ሲወለድ ከነበረውም አንድ ኪሎግራም ያነሰ ነበር።

ወላጆቹ ሥራ ካጡ በኋላ ልጃቸውን መመገብ አቅቷቸው ሱራፌል ለሕክምና መቀለ አይደር ሆስፒታልም ገብቶ ነበር።

በአይደር የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ሕጻኑ ሆስፒታል ከገባ ከአንድ ወር በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ነግረውናል።

የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በቦምብ መደብደብ

ከናሳ የተገኙት የብላክ ማርብል ምሥሎች፤ ከኅዳር 2013 ዓ. ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ. ም. የጦርነቱን አካሄድ የሚያሳዩ ናቸው።

በሽረ፣ አክሱም እና መቀለ ከተሞች የመብራት መጠን እየቀነሰ፣ እየደበበዘና እየጨለመም ሲሄድ ያሳያል።

በየወሩ በከተሞቹ የሚታየው መብራት መደብዘዝና መጨለም ያለውንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት መቋረጥና መቆም ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ብሔራዊውን የኃይል ክምችት የሚቆጣጠር ሲሆን፤ በትግራይ ሆን ብሎ መብራት አቋርጧል ተብሎ ይከሰሳል።

ከጦርነቱ በፊት በክልሉ በነበሩ ከተሞች የነበረው የመብራት አቅርቦት ወጥነት እንደነበረው በርካታ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች በመስከረም ላይ ባወጡት የምርመራ ሪፖርት መሠረት፤ መንግሥት ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ. ም. መብራት፣ ኢንተርኔት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎቶችን ማቋረጡን ይፋ አድርጓል።

ከናሳ የተገኙት ምሥሎች ከጥቅምት 24/2013 ዓ. ም. በኋላ በሽረና አክሱም በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰውን የብርሃን መጠን ያሳያሉ።

በሁለቱ ከተሞች ውስጥ ያለው የመብራት ሽፋን ከተሞቹ በመንግሥት ኃይል ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ከመጋቢት እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ውስጥ ከፍተኛ መሆኑንም ያሳያሉ።

የመቀለን ከተማ በምናይበት ወቅት የትግራይ ኃይሎች እስከተቆጣጠሩበት ሐምሌ 2013 ዓ. ም. ድረስ በከፍተኛ መብራት ደምቃ ትታይ ነበር።

ጦርነቱ በተጀመረበት ወር ተቋርጦ የነበረው የመብራት አገልግሎት ከተማዋ በመንግሥት ኃይል ቁጥጥር ከገባች በኋላ የተመለሰ ሲሆን በቀጣዮቹም ሰባት ወራት ከተማዋ በርታ ትታያለች።

“የትግራይ ኃይሎች ሰኔ/2013 ዓ. ም. መቀለን ጨምሮ ሰፊ የትግራይ ቦታዎችን እንደገና ሲቆጣጠሩ የፌደራል መንግሥት የሰጠው ምላሽ የክልሉን መብራት፣ የኢንተርኔት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎቶችን በድጋሚ በመዝጋት ነው” ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ገልጿል።

በጦርነቱ ወቅት ሰባት ሚሊዮን ለሚሆነው የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ የኃይል ምንጭ የነበረው የተከዜ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ነበር። ይህም ግድብ በታኅሳስ 2014 በቦምብ ተደበደበ።

እነዚህ ምሥሎች፤ የተከዜ ግድብ ጥቃት ከደረሰበት ከታኅሳስ ወር በኋላ የመቀለ ከተማ እንዴት መደብዘዝና መጨለም እንደጀመረች ያሳያሉ።

በተከዜ ላይ የደረሰው ጥቃት ከአራቱ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሁለቱን እንደጎዳ መቀመጫቸውን ካናዳ ያደረጉት ምሁር ተባባሪ ፐሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ ይናገራሉ።

“መሃንዲሶች ከሁለቱ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መለዋወጫ በመውሰድ ሁለቱ ተርባይኖች አገልግሎት እንዲሰጡ ቢያደርጉም ችግሩ አስከፊ ነው። አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ሁለት ተርባይኖች በርካታ ብልሽቶች ስላለባቸውም በበቂ መንገድ ኃይል እያመነጩ አይደለም። መለዋወጫዎች ቢገኙ እነዚህ ብልሽቶች መስተካከል ይችሉ ነበር” በማለት በካልጋሪ ዩኒቨርስቲ የዘላቂ ዲዛይን (ሰስቴይኔብል ዲዛይን) ተባባሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትግራይ በአውሮፓውያኑ 2013 ዓ. ም. በመቀለ ሲጀመር በአፍሪካ ትልቁ የተባለው 84 ተርባይኖች ያሉት የአሸጎዳ የነፋስ የኃይል ማመንጫ ነበራት።

ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ የኃይል ማመንጫው አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያስረዳሉ።

በትግራይ ያሉ መኃንዲሶች 19 ተርባይኖች እንዲሠሩ ቢያደርጉም ለትግራይ ብቻ የመብራት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ አልቻሉም።

በሐምሌና በነሐሴ 2013 ዓ. ም. የሽረ እና አክሱም ከተሞች በጨለማ የተዋጡ ሲሆን መቀለም እየጨለመች መሄዷንም ያሳያል።

በባለፈው ዓመት ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ የታየው የኃይል መቋረጥ ከግድቡ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

የኃይል ማመንጫው የተቀናጀ የኃይል አቅርቦት አካል እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ሁልጊዜም ኤሌክትሪክን ማምረት ስለማይችል እንደሆነም ፕሮፌሰር ጌታቸው ያስረዳሉ።

ለወደፊቱ የተደቀኑ ፍርሃቶች

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የመብራት፣ የባንኮች እና የኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን መከልከሉን ቀጥሏል።

ነገር ግን በዚህ ሳምንት ሽረን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ አሁን በሚቆጣጠራቸው የክልሉ ስፍራዎች በከተማዋ አየር መንገድ በኩል ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማድረስ ቃል ገብቷል።

ጥምር ኃይሉ ከሽረ ተነስቶ ወደ አክሱም፣ አድዋ እና አዲግራት ከተሞች እየገሰገሰ መሆኑን በጦር ግንባር ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በፊትም የኢትዮጵያ መንግሥት ሽረን ይዞ ሌሎች ከተሞችን በመቆጣጠር መቀለ ከተማን መያዙ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም የጦርነቱ ድጋሚ ገፅታ ይመስላል።

የአምስት ወራት የሰብአዊ ተኩስ አቁም በነሐሴ ወር መፍረሱን ተከትሎ የትግራይ ከተሞች በተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

500 ሺህ ለሚገመቱት የመቀለ ነዋሪዎች አስፈሪ ጊዜ ነው።

“ጦርነቱ ተባብሷል። ሁልጊዜም ሰው አልባ አውሮፕላኖች መቼ ይመጣሉ በሚል ስጋት ተሸብብን ነው ያለነው። ልጆቼንስ በሕይወት አገኛቸው ይሆን?” እያለች እንደምትጨነቅ የአይደር ሆስፒታል ነርስ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በክልሉ ከቀሩት ጥቂት የእርዳታ ሠራተኞች መካከል አንዷ እንደተናገረችው ባልደረቦቿ በአሁኑ ወቅት በረሃብ ላይ ናቸው።

"የተረፈው ምግብ ተሟጦ ሕዝቡ በሙሉ በረሃብ እየተሰቃየ ነው" ብላለች።

"በመቶ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ ነዋሪዎች ድጋፍ ለማግኘት በራችንን ያንኳኳሉ። በቤታቸው ምግብ ሳያገኙ ለቀናት የቆዩና በረሃብ እየተሰቃዩ ያሉትን ብዙዎች ቤቱ ይቁጠራቸው” በማለት አስረድታለች።

ምን ሊፈጠር ይሆን? የሚለው የየቀኑ ስጋታቸው ነው። በተለይም ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ወታደሮች ሊደርስ የሚችለው የበቀል እርምጃ።

ለፕሮፌሰር ጌታቸው የተጣለው እገዳ ቢነሳም ጦርነቱ በክልሉ መሠረተ ልማት ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

በአሁኑ ወቅትም በሽረ ዝርፊያዎች እየተፈጸሙ ወደ ኤርትራ እየተላኩ መሆኑን ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ዝርፊያ በመፈጸም ወደ ኤርትራ መውሰዳቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል።

“እውነት ከሆነ ወታደሮቹ ከኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት የቀረውንም አያስተርፉትም” ብለዋል።