ትራምፕ የኻሾግጂን ግድያ በተመለከተ 'ነገሮች ያጋጥማሉ' ሲሉ የሳዑዲውን ልዑል አልጋ ወራሽ ተከላከሉ

ትራምፕ እና ኤምቢኤስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ግድያን በተመለከተ የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን "የሚያውቁት ነገር አልነበረም" አሉ።

ትራምፕ፤ ልዑል አልጋ ወራሹን በዋይት ሀውስ ተቀብለው አስተናግደዋል። የፕሬዝዳንቱ ንግግር አገራቸው እአአ በ2021 ይፋ ካደረገችው የደኅንነት መረጃ ጋር ይቃረናል።

በደኅንነት መረጃው መሠረት፤ ልዑል አልጋ ወራሹ የኻሾግጂን ግድያ ላስከተለው ኦፕሬሽን ይሁንታ ሰጥተዋል። ልዑል አልጋ ወራሹ ይህንን አስተባብለዋል።

ከሰባት ዓመት በፊት ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ በኋላ መሐመድ ቢን ሳልማን በዋይት ሐውስ ሲገኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው።

ለመጨረሻ ጊዜ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር። ኻሾግጂ የተገደለውም በዚያው ዓመት ቱርክ፣ ኢስታንቡል ውስጥ ነው።

ልዑል አልጋ ወራሹ፤ ሳዑዲ እና ዋይት ሀውስ የኻሾግጂን ግድያ ለመመርመር "ሁሉንም ነገር በትክክል ፈጽመዋል" ብለዋል። ግድያውን "የሚያም" ሲሉም ገልጸዋል።

ትራምፕ እና መሐመድ ቢን ሳልማን በዋይት ሀውስ ከተገናኙ በኋላ ስለ ጋዜጠኛው ግድያ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተሰንዝሯል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቆጣ ብለው በሰጡት ምላሽ "እየጠቀሳችሁ ያላችሁት በጣም አወዛጋቢ ሰው ነው። ብዙ ሰዎች አይወዱትም ነበር። ወደዳችሁትም ጠላችሁትም ነገሮች ያጋጥማሉ" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም "እሱ [ልዑል አልጋ ወራሹ] ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። እንግዶቻችንን ማሳፈር የለባችሁም" ሲሉ ተናግረዋል።

ከትራምፕ ቀጥለው የተናገሩት ልዑል አልጋ ወራሹ "የሚያም" እና "ትልቅ ስህተት" ያሉትን የጋዜጠኛውን ግድያ ተከትሎ የተካሄደው ምርመራ "ሁሉም ነገር በትክክል የተከናወነበት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ መሐመድ ቢን ሳልማንን ባያስተናግዱም፤ በሳዑዲ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት አገሪቱን "የተገለለች" ለማድረግ መዛታቸው ይታወሳል።

ባይደን በ2022 ወደ ሳዑዲ አቅንተው በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የኻሾግጂን ግድያም ማንሳታቸውን አስታውቀዋል።

ባይደን ሥልጣን ላይ ሳሉ የተለቀቀው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ልዑል አልጋ ወራሹ ኻሾግጂ ኢስታንቡል ውስጥ "እንዲያዝ ወይም እንዲገደል" ለወጣው ዕቅድ ፈቃድ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ሳሉ ሪፖርቱ ይፋ እንዳይደረግ ቢወስኑም ባይደን መረጃው እንዲወጣ አድርገዋል።

ጋዜጠኛው የተገደለ ሰሞን የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ቢጣልም መሐመድ ቢን ሳልማንን በቀጥታ አይመለከተም።

በወቅቱ ሳዑዲ የአሜሪካን የደኅንነት ሪፖርት "ተቀባይነት የሌለው" ስትል አጣጥላለች።

ትናንት ልዑል አልጋ ወራሹ ዋይት ሀውስ ሳሉ የኻሾግጂ ባለቤት ሀና ኤልታር ኻሾግጂ ይቅርታ እንዲጠይቋት አሳስባለች።

"ልዑል አልጋ ወራሹ በጣም ማዘኑን ገልጿል። ስለዚህ ያግኘኝ እና ለባለቤቴ ግድያ ካሳ ይስጠኝ" ስትል በኤክስ ገጿ ጽፋለች። በአሜሪካ ጥገኝነት የጠየቀችው ሀና ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ትኖራለች።

መሐመድ ቢን ሳልማን እና ትራምፕ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሲቪል የኒውክሌር ኃይልን በተመለከተ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።

መሪዎቹ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሪያድ ተገናኝተዋል። አሜሪካ ለሳዑዲ 142 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ለመሸጥ ውሳኔ ማሳለፏም አይዘነጋም።

ስምምነቱ "በታሪክ ትልቁ" እንደሆነ ዋይት ሀውስ ገልጾ ነበር። የ600 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት ላይም ተደርሷል።

በተጨማሪም አሜሪካ ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶችን ለሳዑዲ አረቢያ እንደምትሸጥ ትራምፕ ተናግረዋል። ስምምነቱ በጦር መሣሪያ አምራቹ ሎክሄድ ማርቲም እና በሳዑዲ መካከል የሚፈጸም እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ልዑል አልጋ ወራሹ "አሜሪካ የዓለም ታላቅ አገር ናት" ያሉ ሲሆን ትራምፕ "ረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የዕድል በር ከፍተዋል" ሲሉም አመስግነዋል።

በዓለም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የሆነውን ኤፍ-35 የጦር ጄት መሸጥን በተመለከተ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ጥያቄ አንስተዋል።

ለሳዑዲ ኃይል የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር ሳዑዲ ቴክኖሎጂውን ለቻይና ልታጋራ እንደምትችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሳዑዲ እና ቻይና የደኅንነት መረጃ ለመለዋወጥ ስምምነት ተፈራርመዋል።

እስራኤልም የመሣሪያ ሽያጩ የደኅንነት ስጋት ሊሆንባት እንደሚችል አስታውቃለች። እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር ከመሆኗ ባሻገር በቀጣናው ብቸኛዋ የኤፍ-35 ጄት ባለቤትም ናት።

ትራምፕ ግን "ይህች [ሳዑዲ አረቢያ] ታላቅ አጋራችን ናት፤ እስራኤልም ታላቅ አጋራችን ናት። አነስተኛ አቅም ያለው አውሮፕላን ብታገኙ ደስተኛ ይሆናሉ። እኔ እንደማስበው ግን ሁለታችሁም እኩል ደረጃ ላይ መሆን ትችላላችሁ" ብለዋል።

ልዑል አልጋ ወራሹ በዋሽንግተን ዲሲ ሳሉ፤ በሳዑዲ የእግር ኳስ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶም ዋይት ሀውስን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።