ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢሰመኮ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በርካታ እስረኞችን በአዋሽ አርባ መጎብኘቱን ገለጸ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉትን የተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችን መጎብኘቱን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከአቶ ክርስቲያን በተጨማሪ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገርን እንዲሁም የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ 53 ታሳሪዎችን ጎብኝቻለሁ ብሏል።
ከታሳሪዎቹ መካከል ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም ይገኙበታል።
ጉብኝቱን ያደረገው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ 5 የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የሚገኙበት ቡድን ሲሆን ጉብኝቱን ያደረገው ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 26 ቀን 2015 አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ መሆኑን ጠቅሷል።
ጉብኝቱን ተከትሎ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ እነዚህ ታሳሪዎች ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 24 ባሉ ቀናት ውስጥ ተይዘው ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካመፕ መወሰዳቸውን መረዳቱን አስታውቋል።
በተለምዶ አዋሽ አርባ የሚባለው ቦታ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ መደበኛ ያልሆነ ጊዝያዊ እስረኛ ማቆያ ጣቢያ ነው።
እስረኞቹን ለምን ወደዚያ ሩቅ ቦታ መውሰድ እንዳስፈለገ ከፌዴራል ፖሊስ ማብራሪያ እንደተደረገለትና በአዲስ አበባ ያለው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ በመጣበቡ እስረⶉቹን ወደዚህ ማምጣት እንዳስፈለገ እንደተነገረው ኮሚሽኑ አውስቷል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ታሳሪዎቹን ለብቻቸው በተናጥል ማነጋገሩን፣ ያሉበትን ሁኔታ በዝርዝር መጎብኘቱን፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የጸጥታ ኃላፊዎችን በጉዳዩ ዙርያ ማነጋገሩን አውስቷል።
ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ ብዙዎቹ ታሳሪዎች የአማራ ብሔር ተወላጅና የኦርቶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ለእስር የበቁትም በማንነታቸው መሆኑን እንደሚያምኑ እንደገለጹለት በሪፖርቱ ጠቅሷል።
ወደ አዋሽ አርባ ከመወሰዳቸው በፊትና በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅት ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻ እንደደረሰባቸው፤ ሆኖም በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን ገልጸውልኛል ብሏል ኮሚሽኑ።
ፖሊስ በበኩሉ የእስረⶉቹ አያያዝ ሰብአዊ መብታቸውን የጠበቀ መሆኑን፣ ሕክምና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይህንኑ እንደሚያመቻችና በቤተሰባቸው እንዲጎበኙ እንደሚያመቻች ገልጾልኛል ብሏል ኢሰመኮ በሪፖርቱ።
ከዚህ በላይ ለሆነ የሕክምና አገልግሎት ወደ ሆስፒታልም መውሰድ እንደሚቻል እንደጠቀሰና እንደምሳሌም አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ተወስደው የህክምና አገልግሎት አግኝተው መመለሳቸውን ፖሊስ ገልጸዋል ሲል ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አውስቷል።
ፖሊስ ጨምሮ የቤተሰብ ጉብኝት ሊመቻች እንደሚችልና ነገር ግን ከቦታው ርቀት አንጻር አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ቤተሰብ እንዳይጉላላ ጉብኝቱ እንደማይፈልግ መግለጻቸውን ጠቅሶልኛል ብሏል ኮሚሽኑ።
ይልቁንም በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ መጠየቃቸውንና ይህም ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ስለሆነ በቅርቡ በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ እንደሚደረግ ፖሊስ መግለጹን ኮሚሽኑ አስታውሷል።
ፖሊስ ይህን ይበል እንጂ ብዙዎቹ እስረኞች ወደዚህ ጊዝያዊ ማቆያ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ አያውቁ እንደነበር ገልጸውልኛል ሲል ኢሰመኮ በመግለጫው አትቷል።
አሁን ቢሆን ያሉበት አዋሽ አርባ ምቹ እንዳልሆነ፣ ከፍተኛ ሙቀት እንዳለና ለጤናቸውና ለሕይወታቸው አስጊ እንደሀነ እንደገለጹለት ኢሰመኮ ገልጿል።
ይህን ተከትሎም ኢሰመኮ ከመንግሥት የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን እና ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶች እንደሚጣሩ ቃል መግባባት ላይ እንደተደረሰ ጠቅሷል። ታሳሪዎችም ቢሆን ከቤተሰቦቻቸው እንዲገናኙ ከመግባባት ተደርሷል ብሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ዓርብ ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።