የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የግዛት ይገባኛል ጥያቄን ለመፍታት ምን አማራጭ አለ?

በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች አዲስ አይደሉም።

በአማራ እና በትግራይ ክልል የተከሰተው የይገባኛል ውዝግብ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ኃይልን የቀላቀለ መሆኑ ነው።

በምሥራቅ እና በምዕራብ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙት ቦታዎች ሁለቱ ክልሎች ለዘመናት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው ቦታዎች ናቸው።

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሁለት ዓመት የተደረገው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ይህንን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ እንዲባባስ አድርጓል።

የአማራ ክልል ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመሰለፍ ህወሓትን ከመዋጋት ባለፈ፣ ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል ስር ሲተዳደሩ የነበሩ እና የአማራ እና የትግይ ክልሎች የሚወዛገቡባቸውን ቦታዎች ተቆጣጥረዋል።

እነዚህን ቦታዎች ሲቆጣጠሩ በአካባቢዎቹ ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን በማፈናቀል እና የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በመባል በመብት ድርጅቶች ይወቀሳሉ።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ከፌደራሉ ሠራዊት ውጭ ያሉ ሌሎች ኃይሎች ከትግራይ ክልል ይወጣሉ ቢባልም ይህ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።

በአማራ ክልል በኩል ከዚህ በፊት ህወሓት በኃይል የወሰዳቻውን አካባቢዎች “እኛም በኃይል አስመልሰናል” በሚል የፌደራል መንግሥቱ ይዞታቸውን እንዲያጸናላቸው ይጠይቃሉ።

ለመሆኑ ይህ በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል መካል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በምን መልኩ ይፈታል? በሕግ መንግሥቱ፣ በሕዝበ ውሳኔ ወይስ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት?

ከእነዚህ ሁለቱ የሕግ መሠረቶች ውጭስ ሌላ አማራጭ ይኖር ይሆን? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ ቢቢሲ የሕግ እና የፌደራሊዝም ምሁራንን አናግሯል።

የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ እና ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማት የነበሩት አቶ ባይሳ ዋቅወያ፣ በዓለም ላይ ለመፍታት አዳጋች ከሆኑት ችግሮች ውስጥ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ።

የድንበር ይገባኛልን ውዝግብን ለመፍታት አዳጋች የሚያደርገው ሁሉም ወገኖች ተጎድቻለሁ፤ እዚያ ያለው የእኔ ወገን ተጎድቷል ተብሎ ስለሚነሳ ነው ይላሉ።

“እንዲህ ያለው ችግር አዲስ ነገር አይደለም። ብዙ ጊዜ ሲፈታ እናያለን። ሳይፈታም ብዙ ዘመናትን ሊያስቆጥር ይችላል” በማለት፣ በእስራኤል እና በሶሪያ ሳይፈታ ለ60 ዓመታት የቆየውን እንዲሁም የምዕራብ ሰሃራን ጉዳይ በምሳሌነት ያነሳሉ።

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረው የይገባኛል ጥያቄ ለመመለስ ሕገ መንግሥቱ ይህንን ይላል፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት ይህንን ይላል ከማለት በቅን ልቦና ተቀራርቦ በመወያየት ከስምምነት መድረስ መልካም እንደሆነ አቶ ባይሳ ይመክራሉ።

በዌስት ኬፕ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ዮናታን ተስፋዬ ፍሰሐ በበኩላቸው የሚነሱት ጥያቄዎች ከክልል ክልል የተለያዩ መሆናቸውን በማንሳት “የማንነት ጥያቄ ወይም የአስተዳደር ውዝግብ መሆኑን መለየት አስፈላጊ ነው” በማለት አጽእኖት ይሰጣሉ።

ፕሮፌሰር ዮናታን እንደሚሉት የማንነት ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመሄዱ በፊት ክልሎች ጉዳዩ ላይ መነጋገር እንዳለባቸውም ይናገራሉ።

‘በኢትዮጵያ ከሰው ይልቅ ለመሬት ዋጋ ይሰጣል’

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ውስጥ የመንቀሳቀስ እና መሥራት ሙሉ መብት አለው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የተለየ ግዛት እና ድንበር አላቸው። በዚህ መሠረትም አብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ላይ የይዞታ ጥያቄ ሲነሳ አንዳንድ ጊዜም ግጭቶች ሲያጋጥሟቸው ቆይተዋል።

በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው ችግርም ዋነኛው ነው። አስካሁን ሁለቱም ክልሎች የይገባኛል ጥያቄውን በንግግርም ሆነ በሌላ ሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጉት የሚታወቅ ሙከራ የለም።

ነገር ግን ባለፉት ወራት በክልል እና በፌደራል ባለሥልጣናት በኩል ይህንን ውዝግብ ሕዝበ ውሳኔ በማካሄድ መፍትሄ እንደሚበጅለት ሲነገር ተሰምቷል። ነገር ግን ይህም ሃሳብ ከተለያዩ ወገኖች ጥያቄ እና ተቃውሞ እየቀረበበት ነው።

አቶ ባይሳ እንደሚሉት በእነዚህ ክልሎች መካከል የተከሰተው ውዝግበ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት በሕዝበ ውሳኔ ይፈታ ቢባል ሌላ ችግር መጋበዝ እንደሚሆን ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

“ሕዝበ ውሳኔውን ማን ነው የሚያካሂደው? ማንስ ነው የሚሳተፍበት? በአካባቢው ለመቶ ወይም ለ50 ዓመታት የኖሩ ናቸው? ወይስ ከ1990 ጀምሮ እዚያ መኖር የጀመሩት? ወይስ ከ2020 በኋላ ያሉ ናቸው የሚሳተፉት? ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የትግራይ ሕዝብ ተፈናቅሎ ወጥቷል። እነሱ በሌሉበት ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ አይቻልም። ከዚያ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው መመለስ ያስፈልጋል” በማለት ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራቸጮች እንዳሉ አቶ ባይሳ ይናገራሉ።

አቶ ባይሣ የመፍትሄ ሃሳብ ነው ከሚሉት ውስጥ አንዱ የፌደራል መንግሥት ከሁለቱም ክልሎች በጀት በመቁረጥ ለተወሰኑ ዓመታት ቦታውን ራሱ ቢያስተዳድር ጥሩ አማራጭ ነው ይላሉ።

“ከዚያ በኋላ ወልቃይት ጠገዴ የሚባለው አካባቢ ነባር ነዋሪ የሚባለው የትኛው ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ምን ያህል ዓመታት እዚያ የኖረ ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ከተስማሙበት በኋላ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ይቻላል። የትግራይ እና አማራ ክልል መንግሥታት በዚህ ላይ መስማማት አለባቸው። እስከዚያ ድረስ በፌደራል መንግሥት ስር ቢተዳደር ጥሩ አማራጭ አድርጌ ነው የምወስደው።”

ይህ የአማራ እና የትግራይ ክልልን እያወዛገበ ያለው ጉዳይ የወሰን ብቻ ሳይሆን የምንነት ጥያቄንም በውስጡ መያዙ ነተደጋጋሚ ሲነገር ነበር።

የማንነት ጥያቄ በአንድ ክልል ውስጥ ሲነሳ መጀመሪያ ወደ ክልሉ ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበት የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር ዮናታን “በክልሉ ያለውን አማራጭ እስከ መጨረሻ አሟጦ መጠቀም ግዴታ ነው” ይላሉ።

ጥያቄው ለክልል ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት ዓመት ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠው ጉዳዩ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል። እዚያም ጥያቄው ቅድመ ሁኔታዎቹን ካሟላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ እንደሚወሰን ገልጸዋል።

“ጥያቄውን ያቀረበው ሕዝብ እና ክልሉ መጀመሪያ ጉዳዩን በውይይት እንዲፈቱ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” በማለት የውሳኔውን ሂደት ያስረዳሉ።

ነገር ግን ምክር ቤቶች ከአድልዎ ነጻ ናቸው በሚለው ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

“የቅማንት ጉዳይ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሲቀርብ የአማራ ተወካዮች ከአድልዎ ነጻ ናቸው ማለት ያስቸግራል። ወይም የወልቃይት ጉዳይ ሲነሳ የትግራይ ተወካዮች ከአድልዎ ነጻ መሆናቸው ያጠራጥራል” በማለት ፕሮፌሰር ዮናታን ያስረዳሉ።

አቶ ባይሣ በበኩላቸው ሁለቱ ወገኖች ሕግ እንደዚህ ይላል፤ ታሪክ እንደዚህ ይላል ከማለት ሰው ላይ አተኩረው ቢሠሩ እንደሚያዋጣቸው ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ለመሬት ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ባይሳ “የሚያሳዝነው በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ከሰው ይበልጣል። ስለሰው ትተን ስለመሬት ነው የምናወራው። የእኛ መሬት ይባላል እንጂ፣ የእኛ ሰው አይባልም” በማለት ከሕግ ቅድሚያ ሰውን ማቀራረብ ላይ መተኮር አለበት ይላሉ።

“የአማራ እና የትግራይ ክልል መንግሥታትም ተቀራርበው መፍትሔ መፈለግ አለባቸው። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ይህ አንቀጽ እንደዚህ ይላል የሚለውን ወስጄ ሥራ ላይ አውላለለሁ ቢባል የሰው ልጅ የሚመራው በቀመር ስላለሆነ አስቸጋሪ ይሆናል። ይህም ወደ ሌላ ጦርነት የሚያመራ ነው” ብለው አቶ ባይሳ ያክላሉ።

አገሪቱ ለሁለት ዓመት ከተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ዳፋ ሳታገግም በወራት ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል ግጭቶች እየተካሄዱ ነው።

የአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎቹ ጉዳይም ቢሆን ምንም አይነት መፍትሄ አላገኘም። በትግራይ ክልል በኩልም የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የአማራ ኃይሎችን ከያዟቸው ግዛቶች እንዲያስወጣ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነው።

‘የሰው ልጅ የፈጠረውን ችግር የሰው ልጅ ነው የሚፈታው’

አሁን አገሪቱን እንደገጠማት አይነት በክልሎች መካከል የይገባኛልም ይሁን የማንነት ጥያቄን ለመፍታት ቀና ፍላጎት ካለ የሚያዳግት አይሆንም ይላሉ አቶ ባይሳ።

“የሰው ልጅ የፈጠረውን ችግር የሰው ልጅ ነው የሚፈታው። ፈጣሪ ያመጣውን ችግር ብቻ ነው መፍታት የማይቻለው” በማለት “ይህ መሬት የእኔ ነው፣ የአንተ አይደለም ከማለት መሬቱ ላይ ስላለው ሕዝብ ማውራት መልካም ነው። ትግሬም ይሁን አማራ በዚያ መሬት ላይ የትኛው ሰብዓዊ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ተተገበሩ ብለን መጠየቅ አለብን።”

በሌላ በኩል ሁለቱ ክልሎች ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቃቸው በማንሳት በቅን ልቦና እና በሠላም ሕዝቦቹን ማቀራረብ ቀዳሚ ሥራቸው መሆን እንዳለበት የሁለቱን ክልሎች ፖለቲከኞች እና መሪዎችን መክረዋል።

ፕሮፌሰር ዮናታንም የተለያዩ አገራትን ምሳሌ በማንሳት ምክክር የተሻለው መፍትሔ እንደሆነ ያነሳሉ።

“በሌሎች አገራት ተመሳሳይ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ነው የሚበራታታው። ካልተቻለ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ይወሰዳል። በኢትዮጵያ ግን ሥልጣኑ ለፍርድ ቤት ሳይሆን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው የተሰጠው።”

የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ የገለልተኝነት ጥያቄ እንደሚነሳበት ያሰምራሉ።

አቶ ባይሳም ሁለቱ ክልሎች ለቀጣይ ትውልድ የቤት ሥራ ከማስቀመጥ ጉዳዩ ተመልሶ እንዳይነሳ ተመካክረው መፍታት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።

በቅርቡ የመከላከያ ሚንስትሩ ዶ/ር አብረሃም በላይ የትግራይና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

አቶ ባይሳ እንዲህ ዓይነቱ ንግግሮች በዚህ ሰዓት መፍትሄ ስለማያመጡ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በማንሳት “ከላይ ሆነው ስለተናገሩ ብቻ መሬት ላይ አይፈጸምም። በሰው ላይ እንጂ ወረቀት ላይ አይደለም ሥራው መሠራት ያለበት” በማለት ሕግ የሚለውን ብቻ ጠቅሶ መሬት ላይ ማስፈጸም አዳጋች እንደሆነ ይናገራሉ።

“የአማራ ሕዝብ ለብዙ ዓመታት መብታችን ተነፍጎ፤ ቋንቋችን ተገፍቶ ነበር ይላል። ይህንን መስማት አለብን። የትግራይ ሕዝብ ደግሞ ትውልዳችን እዚያ ነው ይላሉ። ይህም ሊሆን ይችላል። ቁጭ ተብሎ ካልተነጋገሩ ከላይ ሆኖ እንዲህ ይሆናል ማለት አይቻልም። አንተ እንደዚህ ስትል ሌሎች ምን ይሰማቸዋል። የሌሎችንም ስሜት ማዳመጥ ያስፈልጋል” በማለት የሚንስትሩን አስተያየት ተችተዋል።

አቶ ባይሳ አካልውም መንግሥት በነገሮች ላይ በደፈነው ከመወሰን ይልቅ ጥናት ማድረግን ማስቀደም እንዳለበት እና በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት መቀራረብ ዋነኛው መፍትሄ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።

“ሁለቱ ሕዝቦች ተቀራርበው እንዲሠሩ ዕድል ይፈጠር። ከሌላ አገር የመጣ ሕዝብ ከሆነ ከአገር ይውጣ ሊባል የችላል። እነዚህ ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው። የፈለጉት ቦታ ለመኖር መብት አላቸው” በማለት ሁለቱን ህዝቦች ማቀራረብ ላይ ቢሠራ የአሁኑ መጠላላት እና በዐይነ ቁራኛ መተያየት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይቀራል ብለዋል።