ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ እና ትግራይ አወዛጋቢ ቦታዎች ያለው አስተዳደር እንዲፈርስ ይደረጋል - የመከላከያ ሚኒስትሩ
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ውዝግብ እና ግጭት ምክንያት በሆኑት አካባቢዎች ያሉ አስተዳደሮች በፌደራል መንግሥቱ እንዲፈርሱ እንደሚደረግ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገለጹ።
ሚኒስትሩ የአሸናዳ በዓልን ምክንያት በማድርግ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በትግርኛ ባሰፈሩት ሰፋ ያለ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላይ ነው የአወዛጋቢ ቦታዎችን እና የተፈናቃዮችን ጉዳይ በማንሳት ሃሳባቸውን የገለጹት።
አብርሃም (ዶ/ር) “በአካባቢዎቹ ቀደም ሲል የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንዲፈርሱ” እንደሚደረግ እና በአካባቢዎቹ ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ውጭ የታጠቀ ኃይል አንዳይኖር እንደሚደረግ አስፍረዋል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የሆነው የአገሪቱ ፌደራላዊ ሥርዓት ሲዋቀር ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ተካተዋል በተባሉ ቦታዎች ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተው፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አካባቢዎቹ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወቃል።
በተለይ በትግራይ በኩል ምዕራብ ትግራይ፣ በአማራ በኩል ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ በመባል የሚታወቃው ሰፊ አካባቢ ዋነኛው በሁለቱ ክልሎች መካከል ፍጥጫን ፈጥሮ ያለ ቦታ ነው። እንዲሁም በምሥራቅ በኩል በተመሳሳይ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት የራያ አካባቢ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህም በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር ይገኛል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ የትኞቹንም አካባቢዎች በስም ሳይጠቅሱ ባሳፈሩት መልዕክት፣ በጥቅሉ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከጦርነቱ በኋላ የተመሠረቱ አስተዳደሮች ሕገወጥ በመሆናቸው እንደሚፈርሱ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊትም ኃላፊነቱን ወስዶ ይህንን እንዲያስፈጽም ታዞ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
አብርሃም (ዶ/ር) የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባሰፈሩት መልዕክት “ሕዝባችን ከደረሰበት ጉዳት ገና ባላገገመበት፣ ጥያቄዎቹ በተሟላ መልኩ ባልተመለሱበት፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ባልተመለሱበት፣ . . . በአጠቃላይ ጥያቄዎቹ በአስቸኳይ እንዲመለሱለት በሚጠይቅበት ወቅት” የሚከበር መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ምላሽ ለመስጠት የፌደራሉ መንግሥት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት “የአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ጉዳይ በሕግ እና በሕገመንግሥቱ መሠረት መፍትሄ እንዲያገኝ እየተሠራ” መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ “ለሕዝባችን እና ለወዳጆቻችን ግልጽ ማድረግ የምፈልገው” በማለት አምስት ነጥቦችን በዝርዝር በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
በዚህም ለአወዛጋቢ ቦታዎች መፍትሄ ስለመስጠት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ፣ በአወዛጋቢ ቦታዎች ያሉ አስተዳደሮችን በማፍረስ ወደ ቀየው የተመለሰው ነዋሪ የራሱን አስተዳደር እንዲመሰርት ማድረግ፣ ከፌደራል ኃይሎች ውጪ የታጠቀ ኃይል አንዳይኖር ማድረግ፣ ሕዝቡ ዝግጁ ሲሆን ሪፈረንደም እንደሚካሄድ እና ከሕግ ውጪ የሚሆነ ካለም የፌደራል መንግሥት ሥርዓት እንደሚያስከብር አመልክተዋል።
በትግራይ እና በአማራ ክልል መካከል በይገባኛል ምክንያት ውዝግብ እና ግጭት የተካሄደባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ባለፉት ዓመታት የሁለቱም ክልሎች ባለሥልጣናት የማይታረቅ አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል።
በትግራይ በኩል ያሉ ባለሥልጣናት ሕገመንግሥታዊ ዕውቅና ያላቸው ግዛቶቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ ያላቸውን አቋም በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ በአማራ በኩልም እንዲሁ አላግባብ ወደ ትግራይ በኃይል የተካተቱ ቦታዎች በመሆናቸው ሕጋዊ ባለቤቶች ነን በማለት ያለው ሁኔታ እንደማይቀለበስ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ የይገባኛል ጥያቄዎች ለሚነሱባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሕዝበ ውሳኔ የማካሄድ ጉዳይ ከተለያዩ ወገኖች ሲነሳ ቆይቷል።
ከዚህ አንጻር የመከላከያ ሚኒስትሩ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ያለውን አቋም በይፋ ሲገልጹ የመጀመሪያው ሲሆኑ፣ በግጭት ውስጥ ካለው የአማራ ክልል አመራሮች በኩል ይህንን በተመለከተ አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ የተዋቀረችበት የፌደራል ሥርዓት ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ዋነኛው አወዛጋቢ ቦታ የሆነው የወልቃይት ጠገዴ በጎንደር ክፍለ አገር ሥር የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ አወቃቀር ወደ ትግራይ ክልል ተካቶ ምዕራብ ትግራይ በመባል በክልሉ ስር ሲተዳደር አስርታት ተቆጥረዋል።
በአማራ በኩል ይህ አካባቢ አላግባብ ወደ ትግራይ ተካሏል በሚል ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ የዘለቀ አቤቱታ ሲቀርብ ነበረ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ የአማራ ኃይሎች አካባቢውን ተቆጣጥረው ይገኛሉ።
ከጦርነቱ በኋላ ወልቃይት ጠገዴ ወይም ምዕራብ ትግራይ ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ እያስተዳደሩ ካሉት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለወልቃይት ጉዳይ መፍትሄው ሕጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆን አለበት ሲሉ በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሕዝበ ውሳኔ “ተገቢም፣ እውነትም ነው ብለን አናስብም” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ “ወልቃይት ጠገዴ በጉልበት ወደ ትግራይ የተጠቃለለ በመሆኑ፣ . . . ዘላቂ መፍትሄ የሚገኘው የተፈጸሙ በደሎችን እና ታሪካዊ እውነታዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው” በማለት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚጠብቁ ተናግረው ነበር።