በፍልስጤማዊ ታሳሪ ላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸም የተከሰሱ የእስራኤል ወታደሮችን የደገፉ ለተቃውሞ ወጡ

በፍልስጤማዊ ታሳሪ ላይ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ጥሰቶችን ፈጽመዋል ተብለው ለተከሰሱ የእስራኤል ወታደሮች ድጋፍ ለማሳየት የቀኝ አክራሪ ተቃዋሚዎች የጦር ሰፈሩን ጥሰው ገቡ።

የእስራኤል ፖሊሶች ምርመራ የተከፈተባቸውን እነዚህን ተጠባባቂ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ለማዋል በመጡበት ወቅት በርካታ ህዝብም ሴዴ ቴማን በተሰኘው ስፍራ ተሰብስበው ነበር።

በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘው ስዴ ቴይማን ታስረው ያሉ የጋዛ ነዋሪዎች ከባድ በደል እየተፈጸመባቸው እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጥምር መንግሥት አካል የሆኑ የቀኝ አክራሪ አባላትን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች “ ጓዶቻችንን ብቻቸውን አንተዋቸውም። በተለይም ለአሸባሪዎች” የሚሉ መፈክር በማሰማት የጦር ሰፈሩን በር ጥሰው ገብተዋል።

ሌሎች ደግሞ አጥሩን ዘለው ለመግባት ሲሞክሩ ታይተዋል።

በጦር ሰፈሩ የነበሩ አንዳንድ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸውን የመጡ ወታደራዊ ፖሊሶች ላይ አይናቸው ላይ የሚያቃጥል ነገር ረጭተውባቸዋል ተብሏል።

የቀኝ አክራሪ ተቃዋሚዎቹ ወታደሮቹ ለምርመራ ወደተወሰዱበት በማዕከላዊ እስራኤል በሚገኘው የቤቴልድ ወታደራዊ ካምፕን ጥሰው መግባታቸው ተዘግቧል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተቃዋሚዎቹ የጦር ሰፈሩን ጥሰው መግባታቸውን በማውገዝ ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በወታደሮቹ ድርጊት ላይ የሚደረገው ምርመራ ሊቀጥል ይገባል ብለው “በቁጣም ውስጥ ቢሆን ህጉ በሁሉም ላይ ተፈጻሚ ይሆናል” ብለዋል።

ሆኖም አንዳንድ የእስራኤል ፖለቲከኞች የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደሮችን መታሰር አውግዘዋል። የቀኝ አክራሪው የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታሚር ቤን ጊቪር እስራቸውን “አሳፋሪ” ሲሉ ጠርተውታል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደገዘገቡት ቢያንስ ዘጠኝ የሚሆኑ የእስራኤል ወታደሮች በጦር ሰፈሩ ታስሮ በነበረው ፍልስጤማዊ ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል። ግለሰቡ የሃማስ ተዋጊ ነው በሚል ተጠርጥሮ ለእስር እንደታደረገም ተዘግቧል።

ወታደሮቹ በእስረኛው ላይ አደገኛ የሚባሉ ወሲባዊ ጥቃቶችን እና ጉዳቶችን አድርሰውበታል። ግለሰቡ በፊንጢጣው ላይ በደረሰበት ጥቃትም መራመድ ተስኖት ሆስፒታል መግባቱ ተዘግቧል።

የእስራኤል አጣሪ ኮሚቴ በታሳሪው ላይ ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመጠርጠሩ እንዲጣራ ማዘዙን ጦሩ ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በእስር ማማቀቅ እና “የተንሰራፋ ሰቆቃ” እንድታቆም ጠይቋል።