ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያዊው ‘ኮማንደር’ ማሊ ውስጥ በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥቃት ተገደሉ
የሩሲያዊው የቅጥረኛ ወታደር ቡድን አዛዥ የሆኑት ግለሰብ በአማፂያን በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት መገደላቸውን ቡድኑ አስታወቀ።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ያለው ወታደራዊ አገዛዝ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጂሃዲስቶች እና ተገንጣይ ቡድኖችን ለመዋጋት በአውሮፓውያኑ 2021 ነው የሩሲያውን ቫግነር ቡድን የቀጠረው።
አሁን መጠሪያውን አፍሪካ ኮር ያደረገው የሩሲያው ቡድን ሰኞ በሰጠው መግለጫ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከማሊ ጦር ሠራዊት ጋር በማበር ከተገንጣይ አማፂያንና ጂሃዲስቶች ጋር “ከፍተኛ ውጊያ” ውስጥ መግባቱን አሳውቋል።
ነገር ግን ለአፍሪካ ኮር ቀረብ ያሉ ሰዎች ለቢቢሲ በሰጡት መረጃ መሠረት ተገንጣይ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት ከ20 እስከ 50 የሚሆኑ ቅጥረኛ ወታደሮችን ገድለዋል።
በርካታ የሩሲያ ወታደራዊ ጦማሪዎችም እንዲሁ በተመሳሳይ በሰሜን ምስራቋ ቲንዛዎቴን ከተማ በደረሰ ድንገተኛ ጥቃት ቢያንስ 20 ወታደሮች መገደላቸውን ፅፈዋል።
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን በቴሌግራም ገፁ በለቀቀው መግለጫ ምን ያህል ወታደሮች መገደላቸውን ይፋ ባያደርግም የደረሰበት “ሽንፈት” አረጋግጧል።
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል የጦር አዛዡ ሰርጌ ሼቭሼንኮ እንደሚገኙበትም አስታውቋል።
መግለጫው እንደሚለው ወታደራዊው ቡድን መጀመሪያ “በርካታ የኢስላማ ቡድኑ አባላትን አጥፍቶ ሌሎቹን ደግሞ ከሥፍራው አባርሮ ነበር።”
“ቢሆንም በጊዜው የተከሰተው የአሸዋ አውሎ ነፋስ አክራሪው ቡድን አንሰራርቶ እንደገና በመደራጀት ቁጥሩን ወደ 1000 አሳድጎ እንዲመጣ አግዞታል።”
ቱዋረግ በተሰኘው ብሔር የተመሠረተው ፐርማነንት ስትራቴጂክ ፍሬምዎርክ ፎር ፒስ፣ ሴኪዩሪቲ ኤንድ ዲቨሎፕመንት የተባለው ተገንጣይ ቡድን ለጥቃቱን ኃላፊነት ወስዷል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ “ቅዳሜ ዕለት ኃይሎቻችን የጠላትን አከርካሪ ሰብረዋል” ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ አክለው “ብዙዎች ተማርከዋል፤ እንዲሁም በጣም ብዙ ንብረት እና የጦር መሣሪያ ወድሟል አሊያም ተማርኳል” ማለታቸው ተሰምቷል።
ተገንጣዩ ታጣቂ ቡድን ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የወታደር ልብስ የለበሱ በርካታ ነጮች አሸዋው ላይ ያለምንም እንቅስቃሴ ተኝተው ያሳያል።
በሌላ ቪድዮ ደግሞ በአብዛኛው ጥቁር የሆኑ ሰዎች ዓይናቸው በጨርቀት ተሸፍኖ፤ እጃቸው ወደኋላ ተጠፍሮ ይታያሉ።
ቢቢሲ ተንቃሰቃሽ ምስሎቹን ትክክለኛ ስለመሆናቸው በራሱ እስካሁን አላረጋገጠም።
ጀማል ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን የተባለው የአል-ቃኢዳ አጋር ቡድን በበኩሉ ለጥቃቱ ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ አስታውቋል።
ኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን “ውስብስብ በሆነ ድንገተኛ ጥቃት” 50 የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን መግደሉን ገልጧል።
የማሊ ማዕከላዊ መንግሥት ከዓመታት በፊት ነው የቱዋረግ አመፅን ተከትሎ አብዛኛውን የሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍልን ቁጥጥር ያጣው። አማፂያኑ ከማሊ ተገንጥለው የራሳቸውን ሀገር መመሥረት ይፈልጋሉ።
ኢስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ይህን ግጭት ከተቀላቀሉት በኋላ የሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት የበለጠ ላሽቋል።
በ2020 እና 2021 በተደረጉ መፈንቅለ መንግሥቶች ሥልጣን የያዘው የማሊ ወታደራዊ አገዛዝ ከታጣቂዎቹ የሚደርስበትን ጥቃት ማስቆም ተስኖታል።
አዲሱ ወታደራዊ ጁንታ ከማሊ ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት ካላት ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይን አስወግዶ በምትኩ ከሩሲያ ጋር በማበር በሀገሪቱ ያለውን ውጥረት ለማርገብ እየጣረ ነው።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት የቫግነር ቡድን ኃላፊ የሆኑት የቭገኒ ፕሪጎዢን መሞታቸውን ተከትሎ ቡድኑ አፍሪካ ኮር በተባለ አዲስ ቅጥረኛ ተተክቷል።