ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከምድቧ ‘ተንጠልጥላ’ አልፋ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነችው አይቮሪ ኮስት
ለአንድ ወር ያህል በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ዋንጫውን አንስታ ወድድሩ ተፈጿሟል።
የቦሪያሱያ ዶርትመንዱ አጥቂ ሰባስቲያን አለር ሀገሩ አይቮሪ ኮስት ከመመራት ተንስታ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ከፍ እንድታደርግ ቁልፉን ሚና ተጫውቷል።
ከ13 ወራት በፊት ከዘር ፍሬ ካንሰር አገግሞ ከአልጋ የተነሳው አለር ሀገሩ ለፍጻሜው ጨዋታ እንድትደርስም ጎል አስቆጥሯል።
ትላንትና ሀገሩ አሸናፊ የሆነችብት ጎል ግን አቢጃንን በደስታ ‘ያንቀጠቀጠች’ ሆናለች።
ዊልያም ትሩስት-ኤኮንግ የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃ ሲቀር ‘በቴስታ’ ያስቆጠራት ጎል ንስሮቹን ቀዳሚ አድርጋለች።
ሆኖም ከእረፍት መልስ ፍራንክ ኬሰዬ በ62ኛው ደቂቃ ከማእዘን የተሻመውን ኳስ ወደ ጎል በመቀየር ዝሆኖቹ በጫዋታው ህይወት እንዲዘሩ አድርጓል።
ይህ ጎል ከተቆጠረ 18 ደቂቃ በኋላ፣ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ሳባስቲያን አለር ያስቆጠራት ጎል አዘጋጇን ሻምፒዮን አደርጓል።
አይቮሪ ኮስት በምደብ ጨዋታዎች ዝቅ ያለ አቋም ያሳየች ሲሆን ከአራት ጨዋታዎች በሁለቱ ተረታለች። በዚህም ሳቢያ አሳልጣኟን አሰናብታለች።
በተለይ በመጨረሻው የምደብ ጨዋታ በዘጋጀችው ውድድር በደጋፊዎቿ ፊት በኢኳቶሪያል ጊኒ አራት ለምንም የተረታችበት ጨዋታ አስደንጋጭ ነበር።
ሆኖም፣ በሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች ውጤት ተመርኩዛ ምርጥ ሶስተኛ ሆና አልፋለች። ኪዘያ በኋላ የነበሩ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን በመርታት የዋንጫው አሸናፊ ሆናለች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪ ኮስት በአሮፓውያኑ 1992 እና 2015 የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች። አይቮሪ ኮስት ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳች ብቸኛዋ ሀገር ሆናለች።
አይቮሪ ኮስት ይህንን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አውጥታለች። የትላንቱ የፍጻሜ ጨዋታ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልሳኔ ኦታሪ ታድመውታል።
ዝሆኖቹ ይህንን ጨዋታ በማሸነፋቸው 7 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው ሲሆን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ናይጄሪያ ደግሞ 4 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላታል።
ናይጄሪያ ለፍጻሜ ቀርባ ሽንፈት ገጥሟት አያወቅም። ንስሮቹ እና ዝሆኖቹ በዚህ ወድድር የምድብ ጨዋታ የተጋጠሙ ሲሆን ናይጄሪያ አዘጋጇን አንድ ለምንም ረትታለች።