ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከሰኞ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ
በሱዳን የሚካሄደው ውጊያ ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በአሁኑ ጊዜ ተቀናቃኝ ኃይሎቹ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
ከዚህ ቀደም በሱዳን መደበኛ ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ተኩስ ለማቆም ተደርሰው የነበሩት ስምምነቶች ተግባራዊ ሳይሆኑ ሲጣሱ እንደነበር ይታወሳል።
በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አማካይነት በወጣው መግለጫ መሠረት አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም “ተፈጻሚነቱን በሚቆጣጠር አካል” ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል።
ለሰባት ቀናት ይቆያል በተባለው በዚህ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም ስምምነት የሱዳን ባለሥልጣናት መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ የተቀሰቀሰው ውጊያ ሱዳንን ወደ ከባድ ቀውስ የተከተታት ሲሆን፣ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎችንም ለመፈናቀል እንደዳረገ ይታሰባል።
በአገሪቱ የምግብ፣ የገንዘብ እና የሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ክምችት በፍጥነት የተመናመነ ሲሆን፣ የእርዳታ ድርጅቶች አብዛኛው ግጭት ወደ ተካሄደባት ዋና ከተማ ካርቱም አስፈላጊ እርዳታ ለነዋሪዎች ማቅረብ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ቆይተዋል።
ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የእርዳታ አቅርቦት እንዲካሄድ እንዲፈቅዱ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እንዲያደርጉ እና ኃይሎቻቸውን ከሆስፒታሎች እንዲያስወጡ ሲጠየቁ ቆይተዋል።
በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ድርድር ሲመሩ የነበሩት አሜሪካ እና ሳዑዲ እንዳስታወቁት፣ አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ነው ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ቀደም ሲል የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተግባራዊ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ጠቅሶ፣ የአሁኑ ግን ከቀደሙት ወሳኝ ልዩነት እንዳለው አመልክቷል።
መግለጫው ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ “አሁን ጄዳ ላይ የተፈተመው ስምምነተ ከቀደሙት የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተለየ በአሜሪካ እና በሳዑዲ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ባለው የተኩስ አቁም ተቆጣጣሪ አካል ተግባራዊነቱ ክትትል የሚደረግበት ነው” ብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ላይ፣ ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን እንዲፈቅዱ ጥሪ አድርገዋል።
አክለውም “ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያከብሩ ጥሪ አቀርባለሁ። የዓለማችን ዐይኖችም እየተከታተሏችሁ ነው” ብለዋል ብሊንከን።
አሁን ሱዳንን ከባድ ቀውስ ውስጥ የከተታት ግጭት የተቀሰቀሰው በሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በቆዩት የአገሪቱን ሉዓላዊ የሽግግር መንግሥትን በዋናነት እና በምክትልነት ሲመሩ በቆዩት የጦር ኃይሎቹ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሚመሯቸው ወታደሮች መካከል ነው።
ለቀናት ከቆየ ውጥረት በኋላ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላቱን በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች ማሰማራቱን ተከትሎ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዦች ስጋት ውስጥ በመግባታቸው ነበር በሁለቱ ኃይሎች መካከል ካርቱም ውስጥ ግጭቱ ሚያዚያ 07/2015 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው።
አስካሁን በተካሄዱት ውጊያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። በአፍሪካ ሦስተኛ ትልቅ አገር በሆነችው ሱዳን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ሕዝብ ያለ ሲሆን፣ ሁኔታው ዕየተባባሰ ከሄደ ከባድ ችግርን ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አስጠንቅቋል።
የተፋላሚዎቹ ተወካዮች ድርድር ለማድረግ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካመሩ ሁለት ሳምንት ሆኗቸዋል። ከሳምንት በፊት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ እና የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን በስምምነት አረጋግጠው ነበር።
ነገር ግን ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ይህ የተኩስ አቁም ያልተካተተበት ስምምነት እየተጣሰ መሆኑን አመልክተዋል።
አስከ ትናንት ቅዳሜ ድረስ በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች ውጊያዎች፣ የከባድ መሳሪያ እና የአየር ጥቃቶች ሲካሄዱ እንደነበር የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል።