አብን እና ኢዜማ ህወሓት ስላቀረበው የሠላም ድርድር ሃሳብ ምን አሉ?

ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሠላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንና በዚህም የሚሳተፉ ተወካዮችን መሰየሙን አስታወቋል።

መስከረም 1 2015ዓ.ም ከትግራይ አመራሮች በኩል የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ተኩስ የማይሰማበት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችና የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ የሚያበቃበት ቢሆን ፍላጎታቸው መሆኑን ያትታል።

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገው ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠርም አስቸኳይና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆም እንደሚስማሙና ይህንንም ተከትሎ በሚካሄድ ድርድር ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተደጋጋሚ ግጭቱ ለማስቆም በድርድር ለመሳተፍ ሲገልጽ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ አሁን ከትግራይ አመራሮች በኩል ለቀረበው ሐሳብ ያለው ነገር የለም።

ይህ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ፓርቲዎች አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መስከረም 03 ቀን 2015 ዓ.ም. “ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ የሚቻለው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ሊሆን ይገባል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

“ህወሓት ለሠላማዊ ድርድር ተስማምቼያለሁ ብሎ ጥያቄ ማቅረቡ መጥፎ ባይሆንም በተለመደ ባህሪው የሠላም ድርድሩን እንደ ጊዜ መግዣ ወስዶ ቀጣይ ጥቃት ለመክፈትና ለጥፋት ዝግጅት እንዳይጠቀምበት እንሰጋለን” ብሏል ኢዜማ በመግለጫው።

መንግሥት እና ሕዝቡም ይህንኑ በመረዳት “አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ” አሳስቧል፡፡

ህወሓት በተለያዩ ጊዜዎች አደረሳቸው ያላቸውን ጉዳቶች የጠቀሰው ኢዜማ “ለእውነተኛ ሠላም የሚረፍድ ጊዜ የለም” ብሏል፡፡

“በተደጋጋሚ አውዳሚ ጦርነትን ከለኮሰ በኋላም ለሠላም ዝግጁ ነኝ ማለቱ መጥፎ አይሆንም። የሠላም ድርድር ጥያቄው በተራዘመ ጦርነት የሃገርን ኢኮኖሚ በማዳከም፣ ማህበረሰቡን የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ በመክተት፣ ሕዝባዊ ስልቹነት ውስጥ ለማስገባት ታስቦ የሚደረግ ደባ እንዳይሆን በጥንቃቄ ልናየው ይገባል” ብሏል።

“የሃገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀስን ኃይል የማዘዝ ሥልጣን ሊኖረው የሚገባው የፌደራል መንግሥት ብቻ በመሆኑ ሃገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን አስረግጦ በማስገንዘብ ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ሊደረግ ይገባል” ብሏል ኢዜማ በመግለጫው።

“ከጀርባ ያለው ምክንያት መጠናት ያለበት” ቢሆንም ህወሓት ሠላምን እመርጣለሁ ማለቱን መልካም ጅምር አድርጎ መውሰድም ይገባል ሲል ገልጿል፡፡

“የሠላም ውይይት እና ድርድር ቢኖር እንኳን የሃገር ህልውና አደጋ ላይ በወደቀ ቁጥር ከፊት ተሰልፎ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚዋደቀውን ኃይል ለሁለተኛ ዙር መስዋዕትነት በማይዳርገው መልኩ መከወን ይገባዋል” ብሏል።

"የፖለቲካ ልዩነቶች ሁሉ ከጠረጴዛ ዙሪያ ውጪ ሊሆኑ አይገባም" የሚል ጽኑ እምነት እንዳለውም ኢዜማ አስታውቋል።

 በተመሳሳይም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ህወሓት ድርድር እና ሰላማዊ የግጭት መፍቻ አማራጮችን በድጋሚ የጦርነት ማራመጃ እና የሽብር ማሳለጫ መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀም ሊፈቀድለት አይገባም” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

አብን ለድርድር እና ለሠላም አማራጮች ቅድሚያ የሚሰጥ እና ያልተቆጠበ ድጋፍ የሚያደርግ ንቅናቄ ሲሆን አለመግባባቶች ሁሉ በሠላም መፈታት አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም እንዳለው አስታውቋል።

ሆኖም “ህወሓት የድርድር እና የሠላም አማራጮችን የጦርነት ማራመጃ እና የሽብር ማሳለጫ መሳሪያ የሚያደርግበትን አግባብ በጽኑ ያወግዛል” ብሏል አብን በመግለጫው።

ፓርቲው “ኢትዮጵያ እና የመላው ኢትዮጵያውያንን ዘላቂ ሰላም፣ ጥቅም እና ኅልውና ማረጋገጥ የሚቻለው የሽብር ቡድኑ ኅልውና የሚከስምበትን የጦር ፣ የኮሚኒኬሽን፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ስልቶች በተሟላ ሁኔታ ሥራ ላይ በማዋል ብቻ” መሆኑን እንደሚያምን አስታውቋል።

“የፌዴራሉ መንግሥት ከሽብር ቡድኑ (ህወሓት) ጋር ሰላም ለማውረድ በሚያደርገው ጥረት፣ የሽብር ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ከማስፈታት ያነሰ ግብ እንዳይዝ እና የሽብር ቡድኑን ኅልውና ለማክሰም የሚያስችሉ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ እንዲጠቀም” አብን ጥሪውን አስተላልፏል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት ዙሪያ የተለያዩ ወገኖች ተፋላሚ ወገኖቹን ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም፣ እስካሁን ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል። 

ከአደራዳሪዎች አንጻርም የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ህብረት የሽምግልና ሚናውን እንዲጫወት ሲፈልግ፣ የትግራይ ክልል አመራሮች ደግሞ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት አደራዳሪ እንዲሁኑ እንደሚፈልጉ አሳውቀው ነበር።

የትግራይ አመራሮች ለወራት መቀሌ እና አዲስ አበባ በመመላለስ ጥረት ሲያደርጉ በነበሩት የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ በሆኑት በኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ላይ እምነት እንደሌላቸው ሲገልጹ ነበር።

የአፍሪካ ህብረት ግን ባለፈው አንድ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካዩ ሆነው ያገለገሉትን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆን የውክልና ጊዜያቸው ማራዘሙን አመልክቷል።

የህብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በትዊተር ገጻቸው ላይ ቅዳሜ ዕለት እንዳሰፈሩት፣ በኦባሳንጆ ላይ እምነት እንዳላቸውና “በኢትዮጵያና በአካባቢው ሰላምና እርቅ ለማምጣት” ከሁሉም ወገኖች ጋር እንዲሰሩ እንዳበረታቷቸው ገልጸዋል።