ኬንያ የሁሉም የአፍሪካ አገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው

ፓስፖርት የያዘ ሰው እጅ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

ኢትዮጵያውያንን ቪዛ የማትጠይቀው ኬንያ የቪዛ ገደቦችን በማንሳት ሁሉም አፍሪካውያን ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ ግዛቷ መግባት እንዲችሉ በሯን ለመክፈት መዘጋጀቷን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ።

“አሁን የቪዛ ክልከላዎች አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩብን መሆኑን የተገነዘብንበት ወቅት ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል።

ይህ ለአፍሪካውያን የቪዛ ጥያቄን ለማስቀረት የሚያስችለው የኬንያ ሃሳብ ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ፣ ማለትም በመጪዎቹ ሁለት ወራት ተግባራዊ እንደሚሆን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ገልጸዋል።

በአህጉሪቱ አገራት መካከል ከቪዛ ነጻ ጉዞ እንዲኖር ማድረግ ከአፍሪካ ኅብረት ያለፉት ዓመታት ግቦች አንዱ ነበር።

በቀጠናዊ አገራት እና በአገራት መካከል በሚደረጉ ስምምነቶች መሠረት ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴን የፈቀዱ ቢኖሩም የኅብረቱ ግብ ተግባራዊነት ግን አሁንም አዝጋሚ ነው።

በ2022 (እአአ) በወጣ አንድ ሪፖርት መሠረት ሲሸልስ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን ብቻ ናቸው እስካሁን ለአህጉሪቱ ዜጎች ከቪዛ ነጻ ጉዞን የፈቀዱት።

የአፍሪካ አገራት ምን ያህል ለአህጉሪቱ ጎብኚዎች ክፍት ናቸው የሚለውን የሚያጠናው አፍሪካ ቪዛ ኦፕነስ ኢንዴክስ እንዳመለከተው፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት የመግቢያ ቪዛ ከማላላት ባለፈ ገደቦችንም እያነሱ መሆኑን አስታውቋል።

እአአ በ2022 ኬንያ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት 31ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በኮንጎ-ብራዛቪል ተገኝተው እንደተናገሩት ይህ የቪዛ ክልከላ ለአፍሪካውያን ሥራ እና ንግድ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።

“ሰዎች ካልተንቀሳቀሱ የቢዝነስ ሰዎችም መንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህ ደግሞ ሁላችንም እንከስራለን” ብለዋል።

“ይህንን ልናገር፣ እንደኬንያ ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ማንኛውም አፍሪካዊ ኬንያን ለመጎብኘት ቪዛ አያስፈልገውም” ሲሉ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል።

“ልጆቻችን አውሮፓ እንዳይገቡም ተደርገው፤ አፍሪካ ውስጥም እንዳይንቀሳቁ መደረግ የለባቸውም።”

አፍሪካ ኅብረት በ2016 ነበር የአፍሪካን ፓስፖርት ይፋ ያደረገው። ዓላማው ሁሉም አፍሪካውያን በአህጉሪቱ ውስጥ ያለምንም ቪዛ በቀላሉ እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ቢሆንም በስፋት አልተሰራጨም።

ለዚህ ማነቆ ከሆኑት መካከል ደህንነት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሥራ ዕድል ጫና ይገኙባቸዋል።

የቪዛ ጥያቄን ማስቀረት ባይቻል እንኳን የቪዛ ዋጋን በመቀነስ፤ በደረሱበት አገር ቪዛ በመስጠት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢ-ቪዛ ሥራ ላይ በማዋል ማሻሻል እንደሚቻል ቪዛ ኦፕነስ ኢንዴክስ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።