የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና የፈጠረው ስጋት

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ሰብስበው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ተናገሩ።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከተላለፈ በኋላ ኤርትራ በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዙሪያ የሚንሸራሸረው ውይይት “ከልክ ያለፈ” እና “ለታዛቢዎች እንቆቅልሽ” መሆኑን በመጥቀስ በተዘዋዋሪ ምላሽ ሰጥታለች።

ከኤርትራ ምላሽ በኋላ ባሉት ቀናት ደግሞ ስማቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሳው ሶማሊያ እና ጅቡቲ ለኢትዮጵያን መሪ የባሕር በር ፍላጎት ሃሳብ አውንታዊ ምላሽ አልሰጡም።

በአፍሪካ ትልቅ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻነቷን ማወጇን ተከትሎ ነው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግደ የጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳባቸው የሚሳካው ከግጭት ውጪ በሆነ መንገድ ብቻ ነው ኣሉ ቢሆንም፣ የባሕር በር ጥያቄው ከትብብር ይልቅ የስጋት ምንጭ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።

ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት በቀጥታ በኤርትራ ላይ ያነጣጠረ ባይሆንም በርካቶች በሁለቱ አገራት መካከል ባለፉት ዓመታት የተሻሻለውን ግንኙነት ሊያበላሸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለቸው እየገለጹ ነው።

የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱልራህማን ሰይድ አቡ ሃሺም “ጥያቄው የሚነሳው በዚህ ወቅት የአገሪቱን [የኢትዮጵያን] የውስጥ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማዛባት ነው” ይላሉ።

አብዱልራህማን ምክንያታቸውን ሲየስቀምጡ “ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር ምንም አይነት ምላሽ ስለሌላቸው በአያያዝ ላይም ግልፅ ድክመቶችን ስላሳዩ ጉዳዩን ወደ ሌላ ጉዳይ ማሸጋገር ይፈልጋሉ።”

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ እየሰሩ የሚገኙት ነገራ ጉደታ በበኩላቸው በአቡ ሃሺም ሃሳብ በተወሰነ መልኩ ይስማማሉ።

ይህ የባሕር በር ጥያቄ አሁን የተነሳው ሰዎች ስለ ጦርነት ማሰብ አቁመው ውጪያዊ የሆነ ነገር እና አገሪቱን አንድነት የሚያመጣ ጉዳይ እንዲያስቡ ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ሌላናው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ አሁንም ካለችበት ችግር የመውጣት አቅም አላት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይሆናል።

በሦስተኝነት ግን ደግሞ አገራዊ ከሆኑ ጉዳዮች ወደ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ አቅጣጫ ለማስቀየር ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

የጎረቤቶች ስጋት

አቡሃሺም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት በመግለጽ “ከሞምባሳ፣ ከሞቃዲሾ፣ ከበርበራ፣ ከጂቡቲ፣ ከአሰብ እና ከምጽዋ እስከ ፖርት ሱዳን ድረስ ስድስት አማራጮችን አየመጠቀም ዕድል አላት” ይላሉ።

ስለዚህ እነዚህ የወደብ ዕድሎች ኢትዮጵያ እያሏት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአገራቱ ጦርነት እንደ ማወጅ ሊወሰድ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

አቶ ነገራ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ያንን ሁሉ ሕዝብ፣ ትልቅ ጦር፣ በዲፕሎማሲ ተጽዕኖዋ ከፍተኛ ሆኖ ባሕር በር እፈልጋለሁ ስትል ለእነዚህ አካላት ትልቅ ስጋት እንደሚሆን ያምናሉ።

እነዚህ የጎረቤት አገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ከድንበር ማስፋፋት ጋር አያይዘው ስለሚያዩት ካለመቀበላቸው በተጨማሪ እንደ ስጋት ሊመለከቱት እንደሚችሉም ጨምረው ገልጸዋል።

“ነገር ግን ይሄን የኢትዮጵያን ፍላጎት እነርሱም ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ወደፊት ይህንን ጥያቄ ማንሳት አንደምትችልም ይረዳሉ” በማለት ጥያቄው ለአገራቱ እንግዳ እንደማይሆን ጠቅሰዋለ።

አቶ ነገራ ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የኢኮኖሚ ትስስር በጣም ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት፣ የባሕር በር መፈለጓ ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥርባት ግን ያብራራሉ።

“ከብሔራዊ ገቢያቸው ውስጥ 70 በመቶ ኢትዮጵያ የምትከፍለው የወደብ አገልግሎት ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ማንሳቷ የጂቡቲ ምጣኔ ሃብት ፍላጎት ስጋት ነው።”

ለሶማሌላንድ ግን ይላሉ አቶ ነገረቃ፣ “ይህንን ተጠቅመው ነጻነታቸውን ለማግኘት ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ፣ ለእነርሱ መልካም አጋጣሚ ሊያመጣ ይችላል።

“በሌላ በኩል ለሶማሊያ የስጋት መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው። ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ኢትዮጵያን እንደ ‘ኢምፓየር’ የመመልከት ሁኔታ አለ።”

ስለዚህም ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት በአግባቡ ካልተያዘ፤ “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ልትጋጭ ትችላለች። አካባቢውንም ወደ ጦርነት ሊወስደው ይችላል። ለአሁኑ ግን ውጥረት ነው ሊፈጥር የሚችለው” በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የአንድ ወገን ፍላጎት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ውስጥ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን “ሰጥቶ የመቀበል” መርኅን አንደምትከተል በመግለጽ፣ ኢትዮጵያም ታቀርባቸዋለች ያሏቸውን ነገሮችም ዘርዝረዋል።

አብዱራህማን ሰይድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ትልቅ አገር በመሆኗን “የግድ ወደብ ሊኖራት ይገባል” ሲሉ አሉታዊ መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው።

“ሃሳቡ ተባብሮ በጋራ መጠቀምን ሳይሆን የአንድ ወገን ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ነው። ይሄ ደግሞ አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል” ብለዋል።

አቶ ነገራም የተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር ያላቸው አገራት ለሌላቸው አገራት በር ወይንም መንገድ መክፈት አለባቸው አንደሚል በመጥቀስ፣ ነገር ግን ይህ መፈጸም ያለበት በአገራቱ ይሁንታ ላይ አንደሆነ ያስረዳሉ።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት አካሄድ የተለመደ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ነገራ “ሁለቱ አገራት ፍላጎት ካላቸው ኢትዮጵያ ልትጠቀም ትችላለች። ፍላጎት ግን ከሌለ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።”

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ 2 ቢሊዮን ዶላር እየከፈለች መሆኑን የሚያነሱት አቶ ነገራ፣ በዚህ ሁኔታ “መቀጠል አትችልም። ሕዝቡ ይጨምራል ስለዚህ ትልቅ ስጋት ነው” ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ሃሳብ ብዙ አገራት ይፈሩታል የሚሉት አቶ ነገራ፣ “ኢትዮጵያ ለመስጠት ያቀረበችው ላይፈጸም ይችላል ብለው ይጠረጥራሉ። ሁለተኛ ከኢትዮቴሌኮም፣ ከሕዳሴ ግድብ ወይንም ከሌላው 20 በመቶ ድርሻ መያዝ ለእነርሱ አይጠቅምም። ከዚያ የሚያገኙት ጥቂት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የባሕር በር አገኘች ማለት ትልቅ ነገር ነው የምታተርፈው።”

በተጨማሪም ቀይ ባሕር ወይም ሕንድ ውቅያኖስ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ትልቅ ስለሆነ ለኢትዮጵያ የሚኖረው ጠቀሜታ የገንዘብ ጉዳይ ብቻ እንደማይሆን ነገራ ይጠቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ታላላቅ አገራት ወደ አፍሪካ ቀንደ መጥተው የጦር ሠፈር እንደሚያቋቁሙ በመጥቀስ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ይዛ ጥያቄ ማንሳት የማትችልበት ምክንያት የለም በሚል ተጠየቅ “የአገራቸውን እድገት” እንደ መነሻ አስቀምጠዋል።

“ታላላቆቹ አገራት የቀጣናውን ሀገራት ሉዓላዊነት አክብረዋል። በተጨማሪም የሚጠቀሙበት እና የሚሰጡት ነገር አላቸው። ነገር ግን ‘ይገባናል፣ የተፈጥሮ ድንበራችን እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ነው’ የሚሉ ጠንካራ አነጋገር ይዘህ በመነሳት መግባባት ላይ የሚያደርስ አይደለም” የሚሉት ደግሞ አቡሃሺም ናቸው።

በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ በተለይ በኤርትራውያን ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነው በማለት ለዚህ ምክንያቱ ጥያቄው እና ፍላጎቱ በኤርትራ ላይ በተለይ ያተኮረ ይመስላል በማለት “ይህም ኤርትራውያን በትኩረት ምላሽ እንዲሰጡበት እያደረገ ነው” ይላሉ።

በአግባቡ ያልተመለሰ ጉዳይ

የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሑሩ አቶ ነገራ ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ተገቢውን ምላሽ አለማግኘቱን ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ትችላለች? ኤርትራስ በምላሹ ምን ታገኛለች? የሚል ስምምነት አልነበረም። ስምምነቱ በትጥቅ ትግል ውስጥ ባሉ ሁለት አካላት እንጂ ተቋማዊ አልነበረም። ሁለተኛው ኤርትራ ሁሌም ኢትዮጵያን እንደ ስጋት ነው የምታያት። ምክንያቱም የድንበር ውዝግብ ነበራቸው” በማለት ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ በሕግ ያላለቀ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ነገራ ጉደታ፣ “...ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት ስምምነት የፈጸሙት ሕግ እና ተቋም ላይ ተመሥርተው አይደለም” ሲሉ ያክላሉ።

ስለዚህም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የድንበር፣ የባሕር በር እና ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ ተገቢውን ምላሽ ስላላገኙ ቆይቶም ቢሆን ስጋት መፍጠሩ አይቀርም ብለዋል አቶ ነገራ።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት ለዓለም አቀፍ ንግድ ዋና መስመር በመሆኑ የኃያላን አገራት ትኩረት ተለይቶት አያውቅም።

በዚህ ረገድ አቡሃሺም የምዕራባውያን አገራት ሚና ወይም አመለካከት ምን ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

ሁለቱ አገራት ያላቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነት የተለያየ ነው። ኤርትራ ከሩሲያ እና ከቻይና ጎን በመቆም ምዕራባውያንን ስታወግዝ፣ ኢትዮጵያ ግን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት እና ጥቅም ማስቀጠል ትፈልጋለች።

በምዕራቡ በኩል [ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ፍላጎታቸውን እንዲሟሉ ሊከተሏቸው የሚገቡ ፖሊሲዎችን ሊያስቀምጡ ይችላሉ። ከእነዚህ አንዱ ኤርትራን ማስቆም ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ - አቡ ሃሽም።

በዚህ መሠረትም ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ለእድገቷ ወደብ ሊኖራት ይገባል የሚለውን አጀንዳቸውን ለመተግበር “አበረታተዋቸው” ሊሆን እንደሚችል፤ ለምሳሌ አሰብን በኃይል እንዲቆጣጠሩ እንደሚያግዟቸው ቃል ሊገቡላቸው እንደሚችሉ “አይዝዎት” ብለዋቸው ሊሆን እንሚችል እንደ አንድ ክስተት ሊታይ እንደሚገባ ይገምታሉ።

አቶ ነገራ በበኩላቸው ምዕራባውያን እጃቸውም ባይኖር ሳይደሰቱ አይቀሩም ይላሉ።

“ኢትዮጵያ ይህንን የባሕር በር አገኘች ማለት በቀጠናው ፖለቲካ ኃያል ሆና ትወጣለች ማለት ነው። ምክንያቱም አሁን ተከብባ ነው ያለችው። ቀይ ባሕር ላይ ወታደራዊ ቤዝ የመሠረቱ አገራት ኢትዮጵያ ላይ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ጫና ያሳድራሉ። አገሪቱን የሚያስተዳድረው የትኛውም አካል ይህንን ጥቅማቸውን ሊጠብቅላቸው ደግሞ ይገባል” ይላሉ።

አክለውም “ኢትዮጵያ በአካባቢው ከጠነከረች የባሕር ላይ ንግድ ደኅንነትን በማስከበር ውስጥ ልታግዛቸው ትችላለች። በተመሳሳይ ስጋት ሊፈጥርባቸውም ይችላል። ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ግጭት የሚፈጥር ከሆነ በቀጠናው ሌላ ችግር ሊቀሰቅስ ይችላል።”