የኤርትራ መንግሥት ከባሕር በር ጋር በተያያዘ በሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ እንደሌለበት ገለጸ

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት በተመለከተ ያቀረቡትን ሃሳብ በተመለከተ ኤርትራ ምላሽ ሰጠች።

የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ፣ የባሕር በር እና ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ወደሚደረግባቸው መድረኮች የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትን በተመለከተ መቼ እንደሰጡት ባልታወቀው እና በመንግሥት ቴሌቪዥኖች ባለፈው አርብ ምሽት በተላለፈው ማብራርያቸው ጉዳዩ ውይይት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሕዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሄደው እና ከቀይ ባሕር እና ከሕንድ ውቅያኖስ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ሃሳብ የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

“ቀይ ባሕር እና አባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ጥፋት መሠረት ናቸው” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ መሸሽ እንደማይስፈልግ በመጥቀስ፣ የተለያዩ አማራጮችን አቅርበዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በቀጥታ በኤርትራ ወደቦች ላይ ያነጣጠረ ባይሆንም በበርካቶች ዘንድ በሁለቱ አገራት መካከል ባለፉት ዓመታት የተሻሻለውን ግንኙነት ሊያበላሸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በዚህ ዙሪያ ከቀናት በኋላ የኤርትራ መንግሥት ባወጣው ግልጽ ባልሆነ አጭር መግለጫው ላይ “በውሃ፣ በባሕር በር እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ. . . የሚደረጉ ውይይቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ እና ከልክ ያለፉ ሆነዋል” በማለት ነገሩ ለታዛቢዎች እንቆቅልሽ መሆኑን ጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትን በተመለከተ ለ45 ደቂቃዎች ያህል በሰጡት ማብራሪያ ላይ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሶማሊላንድ አማራጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ በመዘርዘር፣ ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሊሳካባቸው ይችላል ያሏቸውን ከግጭት ውጪ ያሉ አማራጮችን አስረድተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ እንድታገኝ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በትልልቅ የአገሪቱ ተቋማት ውስጥ ድርሻ መስጠት እና የመሬት ልውውጥ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት ለእንዲህ አይነቱ ነገር እንግዳ መሆኑን በመግለጽ፣ ከባሕር በር ጋር በተያያዘ በሚካሄዱ ንግግሮች ውስጥ እንደሌለበት እና እንደማይሳተፍ አመልክቷል።

“የኤርትራ መንግሥት እንደ ሁልጊዜው ወደ እንደዚህ ያሉ መድረኮች ተስቦ እንደማይገባ በማረጋገጥ” ጉዳዩ የሚመለከታቸው ያላቸው ሁሉም የኤርትራ ተቆርቋሪዎች በዚህ ሁኔታ ቁጣቸው እንዳይቀሰቀስ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ግን የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ነው። ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የትንሿን ጎረቤት አገር ጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።

ከቅርብ ወራት በፊት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ስለማስገኘት በይፋ ሲባል ባይሰማም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ አገሪቱ የፈረሰውን የባሕር ኃይሏን መልሳ ማቋቋሟ ይታወቃል።

ይህን የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ በተመለከተ ባለፉት ወራት በተለያዩ መድረኮች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡበት በቴሌቪዥን ለሕዝብ የተላለፈው ስብሰባ ጉዳዩን ይፋ አውጥቶታል።