የአፍሪካ ኅብረት የአህያ ቆዳ ንግድን በመላው አህጉሪቱ እንዳይካሄድ አገደ

የአፍሪካ ኅብረት አዲስ አባባ ላይ ያካሄደውን የመሪዎች ጉባዔን ተከትሎ በመላው አፍሪካ አወዛጋቢ የሆነው የአህዮች ቆዳ ንግድ እንዳይካሄድ እገዳ ጣለ።

ይህ የኅብረቱ ውሳኔ በመላው አፍሪካ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡትን አህዮች ለቆዳቸው ሲባል በሕገወጥ መንገድ ከመታረድ ይታደጋቸዋል የሚል ተስፋን ፈጥሯል።

በአሁኑ ወቅት ከአህያ ቆዳ በሚሠራው እና ተፈላጊ በሆነው የቻይናውያውን ባህላዊ መድኃኒት ምክንያት የአህዮች ቆዳ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የአፍሪካ መሪዎች የአህዮች ቆዳ ንግድ እንዲታገድ የወሰኑት እሁድ ዕለት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ ይህም መላውን የአፍሪካ አገራትን የሚመለከት ውሳኔ ነው።

የአህዮች ደኅንነት ተቆርቋሪው ዶንኪ ሳንክቹዌሪ የአህዮች ቆዳ ንግድ በተለይ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ያለውን የአህዮች ቁጥርን በመቀነስ የሚያጠፋ “ጭካኔ የሞላበት እና ዘላቂ ያልሆነ” ብሎታል።

ከአህያ ቆዳ የሚሠራው ኢጂያዎ የተባለው መድኃኒት ውጤታማነቱ ባይረጋገጥም ለእርጅና እና ለተለያዩ የጤና አገልግሎቶች ይውላል። መድኃኒቱን የሚያዘጋጁት የቻይና ተቋማት በአገራቸው ያሉት አህዮች አሃዝ በመቀነሱ ፊታቸውን ወደ ሌሎች አገራት ለማዞር ተገደዋል።

በዓለም ላይ ለከባድ የጉልበት ሥራዎች ከፍተኛ አገልግሎት ከሚሰጡት አህዮች መካከል ሁለት ሦስተኛው የሚሆኑት በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከአህጉሪቱ አገራት መካከል በአህዮች ብዛት ቀዳሚዋ ናት።

አህዮች ምን ያህል ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንደሚሰጡ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተደረገ ጥናት፣ የአንድ አህያ ባለቤት መሆን በኑሮ ላይ ጉልህ የሆነ ልዩነትን የሚያሳይ መሆኑን አመልክቷል።

ዘ ብሩክ የተባለው የእንስሳት ደኅንነት በጎ አድራጎት ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ራፋኤል ኪኖቲ “አህዮች ለቆዳቸው ሲባል መታረዳቸው በአፍሪካ የሰዎችን የኑሮ ሁኔታን ክፉኛ ከመሸርሸሩ ባሻገር፣ የአህጉሪቱን ባህል፣ ብዘሃ ሕይወት እና ማንነትን የሚያጠፋ ነው” ብለዋል።

የእንስሳት ደኅንነት ተቆርቋሪዎች የአፍሪካ መሪዎች በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የአህያ ቆዳ ሽያጭን ማገዳቸውን አወድሰው፣ ሁሉም አባል አገራት ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።