በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አህዮች ለእርድ የሚቀርቡት ለምንድን ነው?

አንድ ሰሞን በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች፣ የአህያ ሥጋ ነገር ‘ሞቅ ያለ’ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። አንዳንዶች የከረረ ትችት ሲሰነዝሩ ሌሎች ደግሞ የቀልድ ምንጭ ሆኖላቸው ነበር።

ከቀልድ እና ትችት ያለፉት ደግሞ በዚያ ሰበብ ሥራቸው እንደተጎሳቆለ በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል። የነገሩ መነሻ የአህያ ሥጋ በልንኳንዳ ቤቶች ለሽያጭ ይቀርባል የሚል ነበር።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጎረቤት ኬንያ የአህያ ነገር መነጋጋሪያ ሆኗል። ርዕሱ ግን የአህያው ሥጋ ሳይሆን ቆዳው ነው። ለቆዳቸው ተብሎ የአህያ ስርቆት እንደተጧጧፈ ይሰማል።

ለአብነት የ24 ዓመቱ ስቲቭ የገጠመውን እንመልከት። የስቲቭ የገቢ ምንጭ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በአህዮቹ ላይ ነው። 20 ጄሪካኖችን ውሃ እየሞላ በአህዮቹ አማካኝነት ለደንበኞቹ ያደርስር ነበር። አንድ ቀን ሁሉም አህዮቹ ተዘረፉ። የገቢ ምንጩ ቀጥ አለ።

ስቲቭ ያንን ቀን አይረሳውም። እንደሌሎቹ የሥራ ቀናት ከናይሮቢ ማዕከል ርቆ ከሚገኘው ቤቱ አህዮቹ ወደ ሚገኝበት አመራ።

“አህዮቹን ላያቸው አልቻልኩም። ቀኑን ሙሉ፣ ለሌቱን ሙሉ ፈለኳቸው። በሚቀጥለው ቀንም እንዲሁ” የሚለው ስቲቭ ከሦስት ቀናት በኋላ አዲስ ነገር መስማቱን ይገልጻል።

በዚህ ቀን፣ ጓደኛው ስልክ ደውሎ የእንስሳት ቅሪት መመልከቱን ይነግረዋል። “ተገድለዋል፣ ታርደዋል ቆዳቸው ቦታው ላይ አልነበረም” ይላል።

ይህ ዓይነቱ የአህያ ዝርፊያ፣ በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የአህያ ቁጥር ባለባቸው ቦታዎች ላይ እየተስፋፋ መጥቷል። ጥያቄው አህዮች ለምን ይዘረፋሉ? ተዘርፈውስ ለም ለእርድ ይቀርባሉ? የሚል ነው።

የዚህ አጭሩ መልስ ደግሞ ለሥጋቸው ሲባል ሳይሆን በቆዳቸው ምክንያት ነው የሚል ነው።

ስቲቭ እና አህዮቹ እጅግ አወዛጋቢ የሆነው የዓለም አቀፍ የአህያ ቆዳ ንግድ ሰለባ ሆነዋል። መስሎቹም ብዙዎች ናቸው።

የስቲቭ አህዮች ኬንያ ውስጥ ተዘርፈው ለእርድ ይቀረቡ እንጂ ቆዳቸው የሚፈለገቡት ቦታ ለመድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ሊያቆራርጥ ይችላል።

በቻይና ከአህዮች ቆዳ የሚዘጋጀው እና ኢጂያዎ የሚሰኘው ባህላዊ መድኃኒት ፈላጊው ብዙ ነው። መድኃኒቱ ጤናን እንደሚያጎለበት እና ወጣት ሆኖ ለመቆየት እንደሚረዳ ይታመናል።

መድኃኒቱ ሚዘጋጀው የአህያ ቆዳው ተቀቅሎ ከሚወጣው ንጥረ ነገር ነው። ይህ ንጥረ ነገር በዱቄት፣ በእንክብል ወይም በፈሳሽ መልክ ይዘጋጃል። አሊያም ምግብ ውስጥ ሊጨመር ይችላል።

ሆኖም የአህያ ቆዳ ገበያን ክፉኛ የሚቃወሙ ሰዎች አሉ። እነዚህ የመብት ተሟጋቾች እንደ ስቲቭ ያሉ ሰዎች እና ሕይወታቸውን የመሠረቱባቸው አህዮች ኢጂያዎ የተሰኘው ቅመም ላይ የሚፈጠረው ያልተረጋጋ ፍላጎት ተጠቂ ናቸው ይላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2017 የተመሠረተው የአህዮች የቆዳ ሽያጭን አጥብቆ የሚቃወመው ‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5.9 ሚሊዮን በላይ አህዮች ለእርድ ይቀርባሉ የሚል ግምቱን አስቀምጧል።

ቢቢሲ የዚህ ቁጥር እውነታነትን ማረጋገጥ ባይችልም፣ ተቋሙ ይህ ቁጥር በየዓመቱ እንደሚያሻቅብ ጠቁሟል።

ምን ያህል አህዮች ለእርድ ቀርብው ለኢጂያዎ ምርት ግብአት እንደሚሆኑ መረጃ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው።

በዓለም ላይ 53 ሚሊዮን አህዮች አሉ። ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አህዮች መገኛው አፍሪካ ናት። በአፍሪካ የአህያ ሥጋ እና ቆዳ የውጭ ንግድ ላይ ወጥ የሆነ ሕግ የለም።

አንዳንድ አገራት የአህያ ቆዳን ለውጭ ገበያ ማቅረብን ሲከለክሉ ሌሎች ሕጋዊ አድርገው ፈቅደዋል።

የአህያ ቆዳ ያለው ከፍተኛ ፍላጎት እና ዋጋ የአህያ ስርቆት እንዲጧጧፍ ሰበብ ሆኗል።

‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ የእንስሳቱን ቆዳ መሸጥ ከሚከለክሉ አገራት ወደ ወደሚፈቅዱት አህዮች በገፍ እንደሚነዱ ደርሼበታለሁ ይላል።

ሆኖም የአህያ ቀጥር መመናመን ያሳሰባቸው ሁሉም የአፍሪካ አገራት መንግሥታት እና የብራዚል መንግሥት የእንስሳቱን እርድ እና የውጭ ንግድ ለመከለከል ማቀዳቸው ምን አልባት ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2019 ባሉት ሦስት ዓመታት ግማሽ የሚሆኑት የኬንያ አህዮች ለቆዳቸው ተብሎ ለእርድ መቅረባቸውን ናይሮቢ በሚገኘው የ‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ ቢሮ ባልደረባ የሆነው ሶሎሞን ኦንያንጎ ይናገራሉ።

እነዚህ አህዮች በተለይ በገጠር የድሃውን ሕብረተሰብ ሽክም የሚሸከሙ ናቸው። ሰዎችን፣ ቁሶችን፣ ውሃ እና ምግብ በማመላለስ ሥራቸውን ያቀላሉ።

ታዲያ በፍጥነት እየተመነደገ ያለው የአህያ ቆዳ ንግድ ለበርካታ የአህያ መብት ተሟጋቾች የማንቂያ ደውል ሆኗል። በዚህም ምክንያት በኬንያ በርካቶች የአህያ ቆዳ ንግድን የሚቃወመውን እንቅስቃሴን ተቀላቅለዋል።

ይህ ጉዳይ የካቲት 9 እና 10/2016 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ሰብሰባ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከአጀንዳም አልፎ ይህ በአፍሪካ የአህያ እርድ እና ቆዳ ንግድ እንዲታገድ ከስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ ተጥሏል።

ይህንን በተመለከተ ስቲቭ ሲናገር እንስሳቱን መንግሥታቱ እንደሚታደጉ ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል። “ያ ካልሆነ ግን መጪው ትውልድ አህዮች አይኖሩትም” ይላል።

የሆነው ሆኖ፣ በአፍሪካ እና በብራዚል የአህያ እርድ እና የቆዳ ንግድን ማገድ በቀላሉ ለውጥ ያመጣል?

በቻይና የኢጂያዎ አምራቾች የአህያ ሥጋን እንደግብዓት ይጠቀማሉ።

በቻይና በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1990፣ 11 ሚሊዮን የነበረው የአህዮች ቁጥር አሽቆልቁሉ በ2021 ከ2 ሚሊዮን በላይ በታች መሆኑን የአገሪቱ ግብር እና የገጠር ጉዳዮች ሚኒስቴር ገልጿል። በተቃራኒው እጅግ ቅንጡ የነበረው የኢጂያዎ ምርት በስፋት የሚገኝ እና ማንም የሚሸምተው ሆኗል።

ታዲያ የኢጂያዎ አምራቾች ባሕር አቋርጠው የአህያ ቆዳ አቅራቢዎችን ያስሳሉ። የአህያ ቄራዎች በአፍሪካ፣ በደቡ አሜሪካ እና በዚያው በእስያ ከፍተዋል።

ይህ ሁኔታ በአፍሪካ በዚህ ንግድ ላይ “ጦርነት” የቀሰቀሰባቸው አገራት አሉ።

በኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም. በነበረ የሕዝብ ተቃውሞ እና በማኅበራዊ ሚዲያ በተቀጣጠለ ቅሬታ በአገሪቱ ከነበሩ ሁለት የአህያ ቄራዎች አንዱ እንዲዘጋ ሰበብ ሆኗል።

እንደ ታንዛኒያ እና አይቮሪ ኮስት ያሉ አገራት ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት የአህያ እርድ እና ንግድን ሙሉ ለሙሉ አግደዋል። ሆኖም የቻይና ጎረቤት ፓኪስታን የውጭ ንግዱን ከፍ አድርጋለች።

ከወራት በፊት አገሪቱ “ምርጥ የተባለውን” የአህዮች ማራቢያ መክፈቷን ሪፖርቶች አመልክተዋል። ገበያው የመንግሥትን ካዝና የሚያሞቅ አይነት ነው።

በሲድኒ ዩኒቨርስቲ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ተመራማሪዋ ፕሮፈሰር ላውራ ጆንስተን እንደሚሉት የኢጂያዎ ምርት አጠቃላይ ገበያ በአውሮፓውያኑ 2013 ከነበረው የ3.2 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ በ2022 ወደ 7.8 ቢሊዮን ዶላር ተመንድጓል።ይህ ንግድ ለሕብረተሰብ ጤና ሹማምንት እና ለእንስሳት ደኅንነት ተሟጋቾች ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ወንጀል መሪማሪዎችም ስጋትን ጨምሯል።

አንድ የሥነ ምኅዳር ጥናት ተቋም ያወጣው ጥናት የአህያ ቆዳ ሽያጭ ሌሎች የዱር እንስሳትን ምርት ለማጓጓዝ እንደሽፋን እየዋለ እንደሆነ ጠቁሟል።

ታዲያ የሚጠበቀው የአህያ ቆዳ ንግድን የማገድ እርምጃ ከዚህም የባሰ ሕገ ወጥነትን እንዳያስፋፋ በርካቶችን አስግቷል።

ለአገራት መሪዎች እጅግ ወሳኝ አንድ ጥያቄ አለ፡ አህዮች እያደገ ላለ ኢኮኖሚ የሚጠቅሙት ሲሞቱ ወይስ ሲኖሩ?

“በእኛ ሕብረተሰብ ውስጥ በርካታ ሰዎች አነስተኛ አምራች ገበሬ ናቸው። እነዚህ ገበሬዎች ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡት በአህያ ነው” የሚለው ስቲቭ ራሱ በአህያዎቹ አማካኝነት ውሃ እየሸጠ የህክምና ትምህርት ለመማር ገንዘብ እያጠረቀመ እንደነበር ይናገራል።

በ‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ ዋና የእንስሳት ሐኪም የሆነችው ፌዝ በርደን በበርካታ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ባሉ የገጠር አካባቢዎች እነዚህ እንስሳት እጅግ ወሳኝ እንደሆኑ ትናገራለች።

አህዮች በጣም ጠንካራ እና ለማዳ እንደሆኑ አስታውሳ “አንድ አህያ ምናልባት ውሃ ሳይጠጣ ለ24 ሰዓታት ሊጓዝ እንደሚችል እና ውሃም ሲያገኝ የለምንም ችግር አካሉን በጣም በፍጥነት በእርጥበት ሊሞሉ እንደሚችሉ” ትናገራለች።

አህዮች ይህንን የመሰለ አገልግሎት ይሰጡ እንጂ በቀላሉ ወይም በፍጥነት አይራቡም። ለዚህ ነው የአህያ መበት ተሟጋቾች አሁን ባለው ንግድ ላይ ቁጥጥር ካልተደረገ የአህዮች ቁጥር እየሽቆለቆለ ሄዶ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሕብረተሰብ ሕይወቱ አሁን ካለው በላይ ፈተና ላይ ይወድቃል ብለው የሚሰጉት።

ኦንያንጎ “አህዮቻችንን ለእርድ ብለን አርበተን አናውቅም” ይላል።

ፕሮፌሰር ጆንስተን ደግሞ፣ አህዮች ከጥንታዊው ዘመን ጀምረው “ደሃውን ተሸክመዋል” ሲሉ ይገልጻሉ።

ቀጥለው “ህጻናትን እና ሴቶችን ይሸከማሉ። የኢየሱስ እናት፣ ቅድስት ማሪያም አህዮች ተሸክመዋታል” ሲሉ አክለዋል።

እንስሳቱ ሲወሰዱ ህጻናት እና ሴቶች የአህዮቹን ሸክም ለመሸከም ይገደዳሉ በማለት “አንድ ጊዜ አህያው ከሄደ በመሠረቱ የአህያውን ሥራ የሚሠሩት ሴቶች ይሆናሉ” ሲሉ ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።

አክለውም የሚያስገርመው ደግሞ ከደሃ ሴቶች የሚቀሙት አህዮች ቆዳ በቻይና ባለጸጋ ሴቶች የሚጠቀሙበትን ኢጂያዎን ለመቀመም ይውላል።

በሺዎች የሚቆጠር ዓመታትን ያሳለፈው ኢጂያዎ የደምን ጥንካሬ ማሳደግ እና ወላድነት ማጎልበትን ጨምሮ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ይታመናል።

ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 በቻይና አንድ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የታየችው ሴት ኢጂያዎን በብዙዎች ተፈላጊ እና በዋጋ የማይቀመስ አድርጋዋለች።

በዚያ ፕሮግራም ላይ የታየችው ሴት ኢጂያዎ የውበቷ ምሥጢር እንደሆነ ይታያል። ጉድ ተባለ። የኢጂያዎን የሚያሳድደው በዛ። የኋላ ኋላ ያቺ ሴት ገጸባህሪ ለአፍሪካ አህዮች ጠንቅ ሆና ይሆን?

የሆነው ሆኖ ፕፌሰር ጆንስተን ሲያስረዱ በዚያ ፕሮግራም ላይ “የታየችው ሴት ኢጂያዎ በየቀኑ እንደምትጠቀም እና ውበቷን እና ጤንነቷን እንደጠበቀው ተናገራለች። ቀጥላም ለቆዳ እና ወላድነት እንደሚጠቅም ታብራራለች። በዚህ ምክንያት ምርቱ የሴቶች ውበት ምንጭ ተደርጎ ተቆጠሯል። በተጻራሪው፣ ያ ምርት የአፍሪካ ሴቶችን ሕይወት እያመሳቀለ ነው” ብለዋል።

የ24 ዓመቱ ስቲቭ አህዮቹን ሲዘረፍ ሁለንም ነገር አጥቷል፤ ኑሮው ተመሰቃቅሏል። “ሕይወትን አሁን ገና እየጀመርኩ ነው” ይላል።

ብሩክ የተሰኘው እና በናይሮቢ የሚገኘው የአህዮች መብት ላይ የሚያተኩር ድርጅት እንደ ስቲቭ ላሉ ወጣቶች አህያ በማፈላለግ በእርዳታ ይሰጣል። እርዳታው የሚቀርበው ለሥራ እና ለትምህርት ዓላማ ብቻ ነው።

‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ ባልደረባ የሆነው ጃኔክ ሜሪክስ አገራት አህዮቻቸውን ለመጠበቅ ሕግ እያወጡ እና እየተገበሩ በሄዱ ቁጥር አህዮችን ለማግኘት ፈተናው እየጨመረ ይሄዳል ይላል።

“የአህዮችን ቆዳ ንግድ ለማስቀረት ህዋሳቸውን በግብርና የማሳደግን እና የመጠቅም አይነት ሥራ አማራጭ ነው” የሚለው ሜሪክስ ይህንን ለማድረግ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ መንገድ መኖሩን ያስረዳል።

የ‘ዶንኪ ሳንክቸሪ’ ኃላፊ እና የእንስሳት ሐኪሟ ፌዝ ደግሞ የአህያ ቆዳ ንግድ “ያልተገባ እና ኢሰብአዊ ድርጊት ተብሎ እንዲፈረጅ” ጥሪ አቅርባለች።

“ተሰርቀው በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛሉ። ከዚያም በአሰቃቂ ህምም አልፈው ለእርድ ይቀርባሉ” የምትለው ፌዝ “ስለእነሱ እንድንናገር ይፈልጉናል” ስትል ትገልጻለች።

የስቲቭ ሥራ ዳግም ሕይወት ዘርቷል። የአህያ መበት ተሟጋቹ ብሩክ ጆይ ላኪ የተሰኘች አህያ አበርክቶለታል። ስያሜዋ የስቲቭን ደስታ እና ዕድል ለመገለጽ የዋለ ነው።

ህክምና የመማር ዕቅድ ያለው ወጣቱ “ህልሜን ለማሳካት እንደምታግዘኝ አውቃለሁ። ደግሞም በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እችላለህ በደምብ እጠብቃታለሁ” ብሏል።