ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርቴታ ለክለቡ ሽንፈት 'አስቸጋሪ እና በጣም ይበራል' ሲል ኳሱን ተጠያቂ አደረገ
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው ለካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ መድረስ እንደሚችል ቢያምንም ተጫዋቾቹ የውድድሩን "አስቸጋሪ" ኳስ መላመድ እንዳለባቸው አሳስቧል።
አሌክሳንደር ኢዛክ እና አንቶኒ ጎርደን ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች በመጀመሪያው ዙር የውድድሩ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ኒውካስል መድፈኞቹን ማሸነፍ ችሏል።
አርሰናል በጨዋታው 23 ኳሶችን ወደ ጎል ቢሞክርም ዒላማቸውን የመቱት ሦስቱ ብቻ ነበሩ። ጋብርኤል ማርቲኔሊ የጎሉን አግዳሚ ሲገጭ ካይ ሃቨርትዝ ደግሞ ቀላል የጭንቅላት ኳስ አምክኗል።
ከጨዋታው በኋላ ስለባከኑት ኳሶች የተጠየቀው አርቴታ ተጫዋቾቹ ምንም መቀየር ያለባቸው ነገር እንደሌለ ጠቅሶ ኳሱ በጨዋታው ላይ ስላደረሰው ተጽዕኖ ተናግሯል።
"ብዙ ኳሶቻችን በግቡ አናት ላይ አልፈዋል። ኳሶቹ በጣም ስለሚበሩ እና አስቸጋሪ በመሆናቸው ማሻሻል ያሉብን ጥቃቅን ነገሮች አሉ" ብሏል።
"አሁን ጨዋታው አብቅቷል፤ ምንም መቀየር አንችልም። ትኩረት ማድረግ እና ማስተካከል የምንችለው በቀጣዩ ጨዋታ ነው።"
"[የተከናወነው] ግማሹ ጨዋታ ነው። እንደተመለከትኩት አጨዋወት እና ከጥሩ ቡድን ጋር እንዳሳየነው ፍልሚያ ከሆነ በቀጣዩ ጨዋታ ውጤቱን እንቀለብሰዋለን" ብሏል።
ከዚህ ጨዋታ በፊት መድፈኞቹ ባደረጓቸው ሦስት የካራባኦ ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ከመረብ አሳርፈዋል።
በውድድሩ ጥቅም ላይ የሚውለው ኳስ በፑማ የሚመረት ሲሆን የፕሪሚየር ሊጉ ኳሶች ደግሞ በናይኪ የሚመረቱ ናቸው።
ስለኳሱ በዝርዝር እንዲያስረዳ የተጠየቀው አርቴታ "የተለየ ነው" ሲል መልሷል።
"ከፕሪሚየር ሊጉ ኳስ ይለያል። የሚጓዝበት መንገድም የተለየ በመሆኑ መላመድን ይጠይቃል" ሲል አክሏል።
"ስትይዘውም የተለየ በመሆኑ መላመድ ይኖርብሃል" ብሏል።
አርቴታ ምክንያት አለውን?
አርሰናል በአጨራረስ ምክንያት በኒውካስል ቢቀጣም መድፈኞቹ ግን በዘንድሮው የካራባኦ ዋንጫ ላይ ኳሱ ሲያስቸግራቸው አልተስተዋለም።
በመጀመሪያው የካራባኦ ዋንጫ ጨዋታ ቦልተንን 5 ለ 1 አሸንፈዋል።
ፕሪስተንን 3 ለምንም ከረቱ በኋላ ደግሞ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 2 በማሸፍ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል።
በውድድሩ ያላቸው የሙከራ ብዛትም በፕሪሚየር ሊጉ እና በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሚያደርጉት ጋር ተመሳሳይ የሚባል ነው። በአውሮፓ መድረክ ለሚዘጋጁ ውድድሮች ኳሶችን የሚያመርተው አዲዳስ ነው።
ከትላንቱ ጨዋታ በፊት አርሰናል በካራባኦ ዋንጫ ካደረጋቸው 51 ሙከራዎች 27ቱ ዒላማቸውን የጠበቁ ናቸው። ይህም 53 በመቶ ነው።
በፕሪሚየር ሊጉ 102 ሙከራዎችን አድርገው 197 ወይም 52 በመቶ የሚሆኑት ኳሶች ዒላማቸው ጠብቀዋል።
በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ መድፈኞቹ ካደረጓቸው 57 ሙከራዎች ውስጥ 33 ወይም 58 በመቶ የሚሆኑት ዒላማቸውን ጠብቀዋል።