የተወካዮች ምክር ቤት ዋና እንባ ጠባቂ፣ ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ እና የዘርፍ እንባ ጠባቂ ሾመ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ዋና እንባ ጠባቂ፣ ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ እና የዘርፍ እንባ ጠባቂን ሹመቶች በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።
የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው እያገለገሉ የነበሩት ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው ተሹመዋል። የቀድሞው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር የኔነህ ስመኝ ደግሞ ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ ሆነዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ አቶ አባይነህ አዴቶ የዘርፍ እንባ ጠባቂ ሆነው እንዲሠሩ ሹሟቸዋል።
ፓርላማው የሶስቱን ግለሰቦች ሹመት ከማጽደቁ በፊት አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ የምልመላ ሂደቱን እና የተሿሚዎቹን የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ለአባላት በንባብ አሰምተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣን እና ተግባር የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ ክፍል፤ "[ምክር ቤቱ] የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ያቋቁማል፣ ተቋሙን የሚመሩ አባላትን ይመርጣል፣ ይሰይማል። ሥልጣን እና ተግባሩን በሕግ ይወስናል" ሲል ይደነግጋል።
ፓርላማው ከሦስት ወራት በፊት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የሚመሩ ዕጩዎችን እንዲያቀርብ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወሳል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ በተለያዩ የጥቆማ መቀበያ ዘዴዎች ዋና እንባ ጠባቂ ዕጩዎች ሲጠቆሙ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም መሠረት ለዋና እንባ ጠባቂነት 54 ወንድ እና 6 ሴት ዕጩዎች፣ ለምክትል ዋና እንባ ጠባቂነት 185 ወንድ እና 15 ሴት ዕጩዎች መጠቆማቸውን ገልጸዋል።
"ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ዝርዝር መመዘኛ" የማጣራት ሥራ ማከናወኑን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል። ከእነዚህ መመዘኛዎች መካከል የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ እና ታታሪነት እንደሚገኙበት በአቶ ታገሰ ተገልጿል።
በእነዚህ መመዘኛዎች "የተሻለ ነጥብ ያላቸው ዕጩዎች" ተለይተው በተቋሙ ቢሾሙ "ሊያሳኩ የሚፈልጉትን ራዕይ እና ተግባራትን አስመልክቶ አጭር መግለጫ እንዲሰጡ እና ከኮሚቴ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያዎች እንዲሰጡ" መደረጉን አፈ ጉባኤው አብራርተዋል።
ይህን የምልመላ ሂደት ተከትሎ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ "በቂ የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ያላቸው በመሆኑ" ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው ተሹመዋል።
በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወይዘሮ ስመኝ በሥርዓተ ፆታ የማስተርስ ምሩቅ ናቸው። እስከ ዛሬ ድረስ የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው እያገለገሉ የነበሩት ተሿሚዋ፣ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚኒስትር ዲኤታነት ሠርተዋል።
ወይዘሮ ስመኝ የማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ። በተጨማሪም በቀድሞው የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታው ሆነው አገልግለዋል።
ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር የኔነህ ስመኘዕ በበኩላቸው በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው። ዶ/ር የኔነህ አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዋና የሕግ አማካሪ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ዳኛ ሆነው አገልግለዋል።
ዶ/ር የኔነህ "ካላቸው በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ እና ሥነ ምግባር አንጻር"" ምክትል ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው መሾማቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው የሚሾሙት ኃላፊ ተጠሪነታቸው ለሾማቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ አስተዳደራዊ በደሎችን እና የተቋሙን የሥራ አካሂድ አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት የማቅረብ ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቷቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም "ለተቋሙ የቀረበ አቤቱታ በአቤቱታ አቅራቢ ላይ የማይመለስ ወይም የማይተካ ጉዳት ያደርሳል ብሎ ዋና ዕንባ ጠባቂ ካመነ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዕግድ ትዕዛዝ የመስጠት" ሥልጣን አለው።
ለዋና እንባ ጠባቂ ተጠሪ የሆኑት ምክትል ዋና እንባ ጠባቂው በበኩላቸው፤ "ዋና ዕንባ ጠባቂው በማይኖርበት ጊዜ ለዋና ዕንባ ጠባቂው የተሰጡትን ሥራዎች የማከናወን" እና "በዋና ዕንባ ጠባቂው የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት የማከናወን" ኃላፊነት በአዋጁ ተሰጥቷቸዋል።
የእንባ ጠባቂ ተቋም፤ "በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት እና በግል ድርጅቶች መከበራቸውን በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ" ዓላማው መሆኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።












