በእንግሊዝና እና ዌልስ ሙሃመድ ቀዳሚ የህጻናት ስም ሆነ

በእንግሊዝ እና ዌልስ ሙሃመድ ቀዳሚ የህጻናት ወንድ ልጆች ስም ሆነ።

በባለፈው ዓመት 4 ሺህ 600 ወንድ ህጻናት ሙሃመድ ተብለው መሰየማቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህም ወላጆች ስሙን ምርጫቸው እንዳደረጉት ማሳያ ነው ተብሏል።

ሙሃመድ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ከአስሩ የተመረጡ ስሞች አንዱ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም በአንደኝነት የነበረውን ኖህን በመብለጥ ተመራጭ መሆኑን የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ ገልጿል።

በእንግሊዝኛው የተለያዩ ሆሄያትን በመጠቀም የተጻፉ መሃመድ እንዲሁም ሞሃመድ በተጨማሪ በእንግሊዝ እና በዌልስ ከቀዳሚዎቹ 100 ስሞች ውስጥ ተካተዋል። የአገሪቱ ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ በተለያዩ ሆሄያትን የተጻፉትን የመሃመድ ስሞች እንደተለያዩ ስያሜዎች ነው የሚቆጥራቸው።

በሴት ህጻናት ደግሞ ኦሊቪያ ቀዳሚ ስያሜ የሆነ ሲሆን በመቀጠልም አሚሊያ እና ኢስላ ይከተላሉ።

እነዚህ ሶስት ስሞች የቀዳሚነት ስፍራውን ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ይዘዋል።

ሌላ የታየው በሰረዝ የተያያዙ ሁለት ስሞች ለሴት ህጻናት ተወዳጅ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው። በባለፈው ዓመት 19 ሺህ 140 በሰረዝ የተያያዙ ሁለት ስሞች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት 12 ሺህ 330 ተመዝግቧል።

በመቶ ተወዳጅነት እንደ አዲስ ከተካተቱት መካከል ሊላህ፣ ራያ እና ሃዜል ይገኙበታል። በወንዶች ደግሞ ጃክስ፣ ኤንዞ እን ቦድሂ ተወዳጅ አዳዲስ ስሞች ሆነዋል። የሙዚቃ ባህል እና ጥበብ ቤተሰቦች ስም በሚያወጡበት ወቅት ከፍተኛ ተጽእኖ እያደረገ መሆኑን የአገሪቱ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።

ከነዚህም መካከል ቢሊ ኢሊሽ፣ ላና ዴል ሬይ እንዲሁም የካርዲሽያን ጄነር ቤተሰቦች እና የፈልም ኮከቦች ማርጎት ሮቢ እና ሲሊያን መርፊን ዋቢ አድርጓል።

ሌሎች የታዋቂ ሙዚቀኞች ስም ማይሊ፣ ሪሃና፣ ኬንድሪክ እና ኤልተን ስሞችን ለህጻናት መሰጠት በባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ታይቷል። እንደ ሰንደይ (እሁድ) እና ወይንስደይ (ረቡዕ) የሚሉ ስሞች መውጣታቸውን ተከትሎ የሳምንቱ ቀናትም ለቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለመሰየም መነሳሻ ሆነዋል ተብሏል።