የሶሪያ አማጽያን ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ ተቆጣጠሩ

የሶሪያ አማጽያን ሃማ የተሰኘችውን ትልቅ ከተማ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማድረጋቸውን ገለጹ።

አማጽያኑ ከተማዋን የተቆጣጠሩት የአገሪቱ ጦር ከከተማዋ መውጣቷን ተከትሎ ሲሆን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ሌላ ውድቀት ነው ተብሏል።

የታጣቂው ቡድን ሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) መሪ አቤ መሃመድ አል ጃውላኒ ድል ካወጁ በኋላ "ምንም የበቀል እርምጃ እንደማይወስዱ" ቃል ገብተዋል።

ቀደም ሲል የኤችቲኤስ ተዋጊዎች እና አጋሮቻቸው በከባድ ውጊያዎች የሐማ ማዕከላዊ እስር ቤትን ተቆጣጥረው እስረኞችን አስፈትተዋል።

ጦሩ በበኩሉ ወታደሮቹን ከከተማው ውጭ ማሰማራቱን አስታውቋል።

ከአሌፖ በስተደቡብ 110 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሃማ የአንድ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ናት። አማጽያኑ ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምዕራብ ከሚገኘው ጠንካራ ይዞታቸው ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ አሌፖን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

የአማጽያኑ አዛዥ ከአሌፖ ወደ ደማስቆ በሚወስደው አውራ ጎዳና በስተደቡብ ለምትገኘው የሆምስ ከተማ ነዋሪዎች "ጊዜው የናንተ ነው" ሲል ተናግሯል።

ከዚህ ቀደም አሳድ ተፋላሚ አካላትን ለመርታት በሩሲያ እና ኢራን ድጋፍ ይተማመኑ ነበር።

ነገር ግን ሁለቱም አጋሮቻቸው በራሳቸው ጉዳይ መጠመዳቸውን ተከትሎ የመንግሥታቸውን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችለውን ይህንን ግስጋሴ እንዴት ሊገቱት እንደሚችሉ ግልጽ አይደለም።

የአሳድ መንግሥት በዲሞክራሲ ደጋፊ ተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2011 በተነሳው የርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

አማጽያኑ የሃማ ከተማን መቆጣጠር የቻሉት ከመንግሥት የመከላከያ ስራዊት ጋር ጠንከር ያለ የቀናት ፍልሚያ ካደረጉ በኋላ ነው።

ጦሩ አሌፖ በአማጽያን እጅ ከወደቀች በኋላ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አሌፖ ልኮ ነበር።

ነገር ግን የሩሲያ አየር ጥቃቶች እንዲሁም በኢራን ተዋጊ ሚሊሻዎች ድጋፍ ቢደረግለትም የአገሪቱ ጦር ሃማ በአማጽያን እጅ ከመውደቅ አላተረፋትም።

የአማጽያኑ የጦር አዛዥ ሃሰን አብዱል ጋኒ ተዋጊዎቻቸው በተለያዩ ወረዳዎች ጦርነት ገጥሟቸው እንደነበር ትናንት ጥዋት አስታውቀው ነበር።

ከሰዓት ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከሐማ ማዕከላዊ እስር ቤት አስፈትተናል አሉ። ከደቂቃዎች በኋላ "የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ እና የከተማ ውጊያን ለመከላከል" ጦሩ ወታደሮቹን ከሐማ ውጭ አሰማርቻለሁ ብሎ ነበር።

ከስፍራው የወጡ እንዲሁም ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች በሰሜን ምስራቅ ስፍራዎች ተዋጊዎችን አሳይተዋል። የተፈቱት እስረኞችም ከማዕከላዊ ማረሚያ ቤት ውጭ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

"ኃይላችን ወታደራዊ ውጊያውን አጠናቋል። ሃማ ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣቷን ስነግራችሁ በደስታ ነው" ሲል አብዱል ጋኒ ገልጿል።