ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳዊው የአርሰናል ደጋፊ ከዩናይትድ ጋር ከነበረው ጨዋታ በኋላ በጥይት ተገደለ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊጉ ክለብ አርሰናል ደጋፊ የሆነው ኡጋንዳዊው ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድን ከረታ በኋላ ደስታውን ሲገልፅ በጥይት ተመትቶ መሞቱ ተሰምቷል።
የአርሰናል ደጋፊው በአንድ የጥበቃ ሠራተኛ ተመትቶ መሞቱ ነው የተሰማው።
የጥበቃ ሠራተኛው ደስታቸውን እየገለፁ ያሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ላይ በፈከተው እሩምታ ምክንያት አንድ ሌላ የአርሰናል ደጋፊ ቆስሏል።
ይህ የሆነው ሉካያ በተባለች ማዕከላዊ ኡጋንዳ በምትገኝ ከተማ ነው። ከተማዋ ከመዲናዋ ካምፓላ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
አርሰናል ዩናይትድን አስተናግዶ 2-0 ሲረታ ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ነው የተኩስ እሩምታ የተከፈተው።
አንድ የአካባቢው ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው የሕንፃው ባለቤት በደጋፊዎቹ ጫጫታ በመረበሹ ምክንያት የፀጥታ ሠራተኛው ፀጥ እንዲያስብላቸው ጠይቋል።
ነገር ግን ደስታቸውን እየገለፁ የነበሩት ደጋፊዎች ይህን ትዕዛዝ ሊቀበሉ አልወደዱም።
ፋሪሽ ማጌምቤ የተባለው ጋዜጠኛ ከዓይን እማኞቹ እንደሰማው ከሆነ የሕንፃው ባለቤት ሰዎች ኳስ እየተመለከቱ የነበሩበትን ምግብ ቤት መብራት ሲያጠፋ ደጋፊዎቹ ደግሞ የበለጠ ድምፃቸውን ጨምረው በመጨፈር ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ጊዜ የፀጥታ ሠራተኛው ጠመንጃውን አቀባብሎ በርካታ ጥይቶች የተኮሰው።
የ30 ዓመቱ ጆን ሴንዮንጋ እዚያ መሞቱ ተረጋግጧል። ሌላኛው የረዥም ጊዜ የአርሰናል ደጋፊ ሎውረንስ ሙጌጄራ ደግሞ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
የሕንፃው ባለቤት እና የጥበቃ ሠራተኛው አካባቢውን ጥለው የጠፉ ሲሆን ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ፍለጋ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ትዋሀ ካሲርዬ ክስተቱ የተፈጠረበት ሥፍራ ላይ የጦር መሣሪያ ተገኝቷል ብለዋል ሲል የዘገበው ዴይሊ ሚረር ነው።
ቃል አቀባዩ የተፈጠረውን ነገር አውግዘው ነዋሪዎቹ ስለሁለቱ ግለሰቦች የሚያውቁት መረጃ ካለ ለፖሊስ እንዲጠቁሙ አሳስበዋል።
አክለው ደጋፊዎቹ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ መክረዋል።
በተለይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እጅግ ተወዳጅ በሆነባት ኡጋንዳ በሊጉ ደጋፊዎች መካከል በሚፈጠር አተካራ ምክንያት ግርግር ሲነሳባት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ጥቅምት አርሰናል ከሊቨርፑል ካደረጉት ጨዋታ በኋላ በተነሳ ክርክር ምክንያት አንድ የአርሰናል ደጋፊ የማንቸስተር ዩናይትዱን ደጋፊ በስለት መውጋቱ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ጥር ደግሞ አርሰናል በሲቲ ከተሸነፈ በኋላ የተነሳ ግርግርን ለማስታረቅ የገባ አንድ ወጣት ግለሰብ በስለት ተወግቶ ሕይወቱ ማለፉ አይዘነጋም።