ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚከለክለው አዋጅ ምን ይላል? የትኞቹ ጎረቤት አገራት ተግባራዊ አደረጉ?
በኢትዮጵያ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም የሚያግደው ሕግ ከጥር 23/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
አዋጁ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ባለፈው ሐምሌ ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ ከስድስት ወራት በኋላ ነው።
በአዋጁ የማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው የአገሪቷ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሕጉን ጥሰው የሚገኙ አካላት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አሳስቧል።
በዚህም ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ሲጠቀሙ የተገኙ ሰዎች ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ባለሥልጣኑ ገልጿል።
አምራቾች፣ አከፋፋዮች እና የፕላስቲክ ከረጢቶችን ከውጭ የሚያስገቡ አስመጪዎች ደግሞ ከ50 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስር ይከተላቸዋል ብሏል።
አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።
ነዋሪዎችም በቂ የመዘጋጃ ጊዜ አለመሰጠቱን ለማሳየት ከተለመደው በተለየ መልኩ ቁሳቁሶችን ሲይዙ የሚያሳዩ ምሥሎች እና ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርተዋል።
እርምጃውን በበጎ የተቀበሉት ቢኖሩም አንዳንዶች የፕላስቲክ ከረጢቶቹ የሚያስከትሉት ብክለት ከአያያዝ እና ከአወጋገድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመጥቀስ " ከዋጋ እና ከአጠቃቀም አንፃር" አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
እገዳው በፕላስቲክ አምራቾች ማኅበራት ዘንድም ጠንካራ ተቃውሞውን አስነስቷል።
የፕላስቲክ አምራቾች ማኅበር እርምጃውን የነቀፈ ሲሆን፣ የፕላስቲክ ከረጢቶች ምርትን ማገድ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ሥራ አጥ ሊያደርግ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
ማኅበሩ ጨምሮም የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አማራጭ እስከሚያዘጋጁ እና ቴክኒካዊ አቅም እስከሚያጎለብቱ ድረስ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ሲልም እርምጃውን ተቃውሟል።
"መንግሥት ምንም አማራጭ መፍትሔ ሳያስቀምጥ ሕጉን ተግባራዊ አድርጓል" ሲል በመክሰስም ውሳኔውን መልሰው እንዲያጤኑ አሳስቧል።
ይሁን እንጂ ሕጉ ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በአምራቾች እና በተጠቃሚዎች ዘንድ ግንዛቤ ሲፈጥር መቆየቱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ባለሥልጣናትም እገዳው ብክለትን ለመከላከል እና አካባቢን ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።
አዋጁ ምን ይላል?
የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም እና ማመረት በወንጀል ተጠያቂ የሚያደረገው አዋጅ፤ "የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ" ሲሆን፣ ይህንን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል።
አዋጁ ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደኅንነት እና ጤና ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ በመምጣቱ ውጤታማ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተቋማትን እና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ኃላፊነት በሕግ ለመወሰን አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሆነው ይህ አዋጅ የኤሌክትሮኒክ እና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች አያያዝ እና አወጋገድን አይመለከትም።
ስድስት ክፍሎች እና 28 አንቀጾች ያሉት አዋጁ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክን ማምረት፣ ገበያ ላይ ማቅረብ፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀምን ይከለክላል።
ይህ ግን ድንጋጌው ከመውጣቱ በፊት በአገር ውስጥ በተመረተ ወይም ወደ አገር ውስጥ በገባ፣ በመግባት ሒደት ላይ ባለ የፕላስቲክ ምርት ላይ ተፈፃሚ አይሆንም። ተፈፃሚ የሚሆነው አዋጁ በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት ብቻ መሆኑን አዋጁ ጠቅሷል።
ይህንንም እንዲቆጣጠር እና ጥሰት ሲኖር ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ለአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ሥልጣን ሰጥቷል።
በመሆኑም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች በቀላሉ በሌላ ምርት የማይተኩ ከሆነ እንዲመረቱ ፣ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ባለሥልጣኑ በመመሪያ ሊወስን የሚችልበትን ልዩ ሁኔታ አስቀምጧል።
በዚህ ልዩ ሁኔታ መሠረት እነዚህን በሌላ የማይተኩ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን የሚያቀርብ ወይም የሚጠቀም ሰው ደረጃውን እንዲያረጋገጥ፣ በአግባቡ የሚያዝበትን እና የሚወገድበትን ሥርዓት እንዲዘረጋ አዋጁ ያስገድዳል።
ከዚህም በተጨማሪ ስለምርቱ ገላጭ ጽሑፍ ማስቀምጥም ይኖርበታል።
በመሆኑም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ በማምረት ላይ የተሰማሩ አምራቾች ወይም አስመጪዎች አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ አዋጁ የሚያዛቸውን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ግን በፕላስቲክ ከረጢቶች ላይ ተፈፃሚ አይሆኑም።
የጎረቤት አገራት ተሞክሮ ምን ያሳያል?
ኬንያ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የከለከለችው ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር። በወቅቱ እርምጃው ወሳኝ ተብሏል።
በሕጉ መሠረትም የፕላስቲክ ከረጢቶችን ከውጭ ሲያስገባ፣ ሲሸጥ ወይም ሲያመርት የተገኘ እስከ 40 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት አሊያም እስከ አራት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጣልበታል።
የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም ደግሞ 500 ዶላር ወይም እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስር ያስቀጣል።
ይህንን ካገደች ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ በፓርኮች እና ጫካዎች ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ከልክላለች።
እገዳው ከተጣለ ጀምሮ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም እንዳቆመ መንግሥት በወቅቱ ገልጿል። ሆኖም ከረጢቶቹን የተኩ ሌሎች ምርቶች አሁንም አካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው።
ኡጋንዳ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የከለከለችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 ሲሆን ሕጉን ጥሶ የተገኘ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስር ወይም እስከ 20 ሺህ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል።
ታንዛኒያም እንደ አውሮፓውያኑ 2019 የፕላስቲክ ከረጢቶችን አግዳለች። በዚህም የፕላስቲክ ከረጢቶችን ይዘው የተገኙ እስከ 87 ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም የሰባት ቀን እስር ይጠብቃቸዋል።
እነዚህን የፕላስቲክ ምርቶች ማምረት ወይም ከውጪ ማስገባት ደግሞ እስከ 430 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና የሁለት ዓመት እስር ያስከትላል።
እግዱን ተከትሎ የወቅቱ አገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት ጆን ማጉፉሊ ተግባራዊነቱን ለማበረታታት ዘንቢል ይዘው ታይተው ነበር።
ኢትዮጵያም ሕጉን ተግባራዊ በማድረግ ቀደም ብለው የፕላስቲክ ከረጢቶችን ያገዱትን ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ቤኒን፣ ሴኔጋል፣ ኮትዲቯር እና ማዳጋስካርን ጨምሮ ከ34 በላይ የአፍሪካ አገራትን ተቀላቅላለች።
ኤርትራ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ ከ21 ዓመታት በፊት ምርቶቹን በማገድ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
የአገራቱ እርምጃ በዘርፉ ላይ በተሰማሩ ፋብሪካዎች እና የንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ ሲሆን በርካቶችን ሥራ አጥ እንዲሆኑ በማድረግ ይተቻል።
ነገር ግን እነዚህን የፕላስቲክ ምርቶች ለመተካት የተከፈቱ ኢንደስትሪዎች ደግሞ ሌሎች የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
አገራት አካባቢን ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ቢሆንም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ለመተካት በተመረቱ ከረጢቶች፣ የውሃ ኮዳን ጨምሮ በሌሎች የፕላስቲክ ምርቶች እና በሕግ አፈጻጸም ጉድለት ምክንያት አሁንም አካባቢ ከብክለት እንዳልዳነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።