ቆሻሻ መጣያ የነበረን ቦታ ወደ ውብ የመናፈሻ ሥፍራነት የለወጠች ሴት

በአንድ ሰው ብርታት የሆነ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል። ግን ሆኗል።

በእርግጥ እንዲሁ በአንድ ጀምበር የሆነ አይደለም። ከጽንሰት እስከ ውልደት አስርት ዓመታትን ፈጅቷል።

ከተማዋ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ቦታ ዐይታ አታውቅም።

ሞቃታማ የአየር ጠባይ ላላት ከተማ አሁን ላይ ንጹህ አየር መቀበያ ሥፍራ ሆኗል።

የወዳጆች የልብ ለልብ መጫዎቻ፣ የሠርግ ማድመቂያ፣ የልደት እና የምርቃት ፕሮግራም ማሰናጃ፣ የልጆች መቦረቂያ፣ የሙዚቃ ቪዲዮዎች መሥሪያ፣ የተጣሉትን ማስታረቂያ፣ ከራስ ጋር መነጋገሪያ ቦታም ነው።

ለከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ከተሞች ነዋሪዎችም ‘አንድ አለን’ የሚሉት መዝናኛ ቦታ ሆኗል።

በእርግጥ እንዲህ የተዋቡ አረንጓዴ መናፈሻዎችን ማግኘት ለኢንደስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ብርቅ ነው።

ታዲያ የመናፈሻ ብርቅነትን ለማስታገስ ይመስላል አንዲት የከተማዋ ነዋሪ በአሁኑ ሰዓት በከተማው ‘ብርቅዬ’ ሊባል የሚችል መናፈሻን ለተገልጋዮች ክፍት ያደረገችው።

ይህች ሴት ሰናይት ጋሻው ትባላለች። ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት።

ሰናይት ከእፅዋት ጋር ያላት ትስስር በልጅነቷ ተጠንስሶ አብሯት ያደገ ነው። ለእፅዋት ልዩ ፍቅር ነው ያላት። የለመለመ አረንጓዴ መሬት ማየት ረሃቧንም፣ ጥማቷንም የምታረካበት ነው።

‘ሆድ ብቻ ሳይሆን ዐይንም ይበላል’ የሚል እምነት አላት።

ለዚህም ነው ሳትታክት እንደ ልጅ የምትንከባከባቸውን እፅዋቶች ከቤቷ እና ከግቢዋ ይዛ በመውጣት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲተርፍ ያደረገችው።

መኖሪያ ቤቷ በቤት ውስጥ እፅዋቶች የተሞላ ነው። ግቢዋም እንዲሁ። ለእነርሱ ያላት ፍቅር ይህ ነው ተብሎ የሚገለጽ አይደለም።

ሰናይት የግብርና ሙያ አልተማረችም። ስለእፅዋትም ቢሆን በቀለም ያገኘችው እውቀት የለም።

እፅዋት የመትከልና የመንከባከብን ሙያ ያዳበረችው በልምድ ነው።

“የእፅዋቱን ባህርይ ለማወቅ ሙከራ አካሂዳለሁ። እንደ ሐኪም እፅዋቱ ምን እንደሆኑ ማወቅ እችላለሁ። ይህንን ያገኘሁት ከልምድና ከፍቅር ነው። ልክ ሕጻን ልጅን ምን ይወዳል? ምን ይጠላል? ምን ያሳምመዋል? ምን ያድነዋል? ብሎ እንደ መንከባከብ ነው” ትላለች።

ይህ ልምድ ግን ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ከልጅነት እስከ እውቀት በዘለቀ የዳበረ ልምድ ነው።

በሹፍርና ሙያ ይተዳደሩ የነበሩት አባቷም ለዚህ ዋና መሠረቷ እና አርአያዋ ነበሩ።

ደሴ ከተማ ይኖሩ የነበሩት አባቷ አቶ ጋሻው፣ ቤታቸውና ግቢያቸውን በእፅዋት የማስዋብ ልምድ ነበራቸው።

በሥራ ባህርያቸው ምክንያት ብዙ ጊዜያቸውን ቤት ውስጥ አያሳልፉ እንጂ የትም ቦታ ተጉዘው ሲመለሱ ግን የተለያዩ የእፅዋት ችግኞች ከእጃቸው አይታጣም ነበር።

እነዚህን እፅዋቶች በግቢያቸው ከተከሉ በኋላ ግን አደራውን የሚሰጡት ለሰናይት ነበር። እነርሱን ውሃ ማጠጣት፣ ማስዋብና መንከባከብ ኃላፊነቷ ነበር።

ለዚህ ነው የልብ ጓደኞቿ ያህል ከእፅዋት ሥር የማትጠፋው።

ሰናይት እንደምትለው በቤታቸው ግቢ ውስጥ የሌለ የእፅዋት ዓይነት አልነበረም።

ለውበት የተተከሉ ብቻ ሳይሆን ለመዓዛም፣ ለምግብነትም የሚተርፉ ነበሩ። አደሱ፣ አርቲው፣ ጤና አዳሙ፣ የሥጋ መጥበሻው፣ ፕሪም፣ ኮክ፣ አፕል ሌላም ሌላም።

ሰናይት የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ግን ቤተሰቦቿን በሞት አጣች። ሁለት ታናናሽ እህቶቿን የማሳደግ ኃላፊነትም በእርሷ ላይ ወደቀ። በነበረባት ኃላፊነት ምክንያት ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም። ትዳር መስርታ፣ የራሷን ጎጆ ቀልሳ እህቶቿን ማሳደግ ያዘች።

ለእጽዋት ያላት ፍቅር ግን እንደ ትምህርቷ በአጭሩ አልተቀጨም። ቤቷ ውስጥ መትከልና ግቢዋን ማስዋብ ቤተሰቡን ከመንከባከብ እኩል የምታደርገው የዕለት ሥራዋ ሆነ።

ይህን የምታደርገው ራሷን ለማስደሰት ብቻ ነበር። የትዳር አጋሯ እጽዋትን መትከልና መንከባከብ መውደዱ ደግሞ ለሥራዋ ብርታት ሆናት።

ሰናይት መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ እፅዋቶች እንዳሉ ትናገራለች።

“በቤት ውስጥ ለሚተከሉ እፅዋቶች የተለየ ፍቅር አለኝ” የምትለው ሰናይት፣ እጽዋቶቹን ከተለያዩ አካባቢዎች ለመሰብሰብ፣ ከውጪ አገር የሚገቡ እጽዋትን ገዝቶ ለማባዛት ከ20 ዓመታት በላይ እንደወሰደባት ትገልጻለች።

ከጓሮዋ ወደ ሌሎች ግቢ መድረስ የጀመረችውም ያሏትን እጽዋቶች ለወዳጅ ዘመድ በማበርከት ነበር።

ከዚያም ይህንን በጎ ተግባር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለማጋባት ሳሎን ውስጥ፣ ቢሮ ውስጥ እና የሥራ ቦታዎች ውስጥ የሚተከሉ የእፅዋት ችግኞችን መሸጥ ጀመረች።

እርሷ እንደምትለው አተርፍበታለሁ፣ ሃብታም እሆንበታለሁ ብላ ግን አልነበረም። አካባቢው እንደርሷ እንዲዋብ እንጂ።

ሆኖም እጽዋቶቹን ለገበያ ማቅረብ ብቻ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ልብ አልሳበውም።

"የማቀርብላቸው እፅዋቶች ተተክለው የሚጸድቁ አይመስላቸውም ነበር" ትላለች።

ይህንን በተግባር ለማሳየትም እዚያው የምትሸጥበት ቦታ ላይ አነስተኛ ሰርቶ ማሳያ አዘጋጀች። ሰዎች ሊገዙ ሲመጡ የትኛው የቱ እንደሆነና እንዴት መንከባከብ እንደሚችሉ እያስጎበኘች ለማስረዳት ረዳት።

ይህ አንድም ገበያዋ እንዲደራ፣ በሌላም በኩል ነዋሪው ከእፅዋት ጋር እንዲወዳጅ ለማነሳሳት አግዟታል።

በአካባቢው አረንጓዴ የመዝናኛ ሥፍራ ባለመኖሩም ይህንኑ አነስተኛ ሰርቶ ማሳያ ፎቶ ለመነሳት የሚጎበኘው በርካታ ሰው ነበር።

ኅብረተሰቡን ለአረንጓዴ ሥፍራ ያለውን ፍቅር የተረዳችው ሰናይት ታዲያ አነስተኛ መናፈሻ መሥራት እንዳለባት አሰበች፤ እውን አደረገችውም።

“አነስተኛው መናፈሻም ከአቅሙ በላይ ሥራ በዛበት። ሠርገኞች ሁሉ ይመጡ ያዙ። የሕዝቡ ፍላጎት ከፍተኛ ሆነ” የምትለው ሰናይት፣ እንደገና በሰፊው ማለም ጀመረች።

በእፅዋት ዘርፍ ምንም ዓይነት የቀለም እውቀት የሌላትና ከኢትዮጵያ ውጭ የትም ሄዳ የማታውቀው ሠናይት፣ አዕምሮዋ ውስጥ ተስሎ እዚያው ያደገውን የመናፈሻ ዲዛይን መሬት ላይ ማውረድ ፈለገች።

ከዚያም የከተማ አስተዳደሩ መሬት እንዲሰጣት ደጋግማ ጠየቀች። ውትወታዋ መልስ አገኘ። ለከተማው ቆሻሻ መድፊያ ተመርጦ የነበረ ቦታ ተሰጣት። ቦርከና ወንዝ ዳርቻ - ሸህ ሿቢር የሚባል አካባቢ። 

ቦታው ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ያልነበረው የቆሻሻ መድፊያ ቦታ መሆኑ ልቧን አላዛለውም።

ጉልበቷም አልደከመም። በእጇ ላይ ግን ምንም ገንዘብ አልነበራትም። ይህም አላስፈራት።

“እጅ እና እግሬን ይዤ ነው ሥራውን የጀመርኩት” ትላለች ሠናይት። ፍቅር እና ትጋት ብቻ ነበር ጉልበቷ።

አካባቢውን አጽድታ፣ ከቦርከና ወንዝ ውሃ በመጥለፍ ላለፉት 20 ዓመታት በግቢዋ ያሰባሰበቻቸውን እፅዋቶችን ራሷ ዲዛይኑን በማውጣት ቦታ ቦታ አስያዘቻቸው። ልፋቱ ግን ቀላል አልነበረም።

በዙሪያዋ ያሉ ቤተሰቦቿ በሥራዋ ቢደሰቱም የእርሷን መጎዳት ባለመፈለግ በልፋቷ ትንሽ ቅሬታ ነበራቸው።

ከአካባቢው ማኅበረሰብም አትድከሚ፣ አይለወጥም የሚሉ አስተያያቶች ይደርሷት ነበር። በእርግጥ “አይዞሽ፣ በርቺ” የሚሏትም ጥቂት አልነበሩም። እርሷ ግን ተነሳሽነቷ ከፍቅር የመነጨ ስለሆነ አልተበገረችም።

ይሁን እንጂ ቦታው ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ ሰው ይመጣል የሚል እምነት አልነበራትም።

ወደ መናፈሻው ሰው ሲጎርፍ ግን አንድ ዓመት አልወሰደም። በፍቅር የጀመረችው ሥራዋ እንጀራዋም ሆነ። የመናፈሻ ሥራውን አጠናክራ ቀጠለች።

ሰናይት መናፈሻ በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው። 10 ሺህ ካሬ ሜትሩ በውሃ ተሸርሽሮ ገደል የነበረና በእርሷ ጥረት እንደገና ያገገመ መሬት እንደሆነም ትናገራለች።

ሰናይት እንደምትለው መናፈሻው በአንድ ጊዜ 15 ሠርጎችን የማስተናገድ አቅም አለው።

በአንዲት ብርቱ ሴት የተጀመረው መናፈሻ አሁን ላይ 50 ቋሚ ሠራተኞች አሉት። በጊዜያዊነት ለሚሰሩ ሠራተኞችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

“ብዙ ወጣት ባለሙያዎችን አፍርተንበታል። የሰዎችን አስተሳሰብ ቀይረንበታል። ቆሻሻ እንዲፀዳ፣ ሆቴሎች አረንጓዴ እንዲሆኑ ምሳሌ ሆኗል” ትላለች።

መሬት የማግኘት ዕድል ካገኘችም ይህንን ሥራዋን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ዕቅድ አላት። ነገር ግን ለጊዜው የመሬት ጉዳይ አስቸጋሪ በመሆኑ ይህንኑ ቦታ ለተገልጋዮች ምቹና እጅግ ውብ የማድረግ ሀሳብ ነው ያለኝ” ብላለች።

በሥራዋ ከሰዎች ከምታገኘው አክብሮትና ፍቅር ባሻገር የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳዳር ዋንጫ እና የምስክር ወረቀቶችን አበርክቶላታል።