ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኡጋንዳ የአባትነት ምርመራ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተነገረ
በኡጋንዳ አባትነታቸውን ለማረጋገጥ ምርመራ የሚሹ ወንዶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተነገረ።
አሁን ባለው መረጃ መሰረት 70 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱንም ነው የአገሪቱ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ሲሞን ሙንዴይ የተናገሩት።
ከሶስት ዓመት በፊት በወር ሶስት የዲኤንኤ (ዘረመል) ምርመራዎች ይደረጉ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ወደ 100 የሚጠጉ የአባትነት ማረጋጋጫ የዲኤንኤ ምርመራዎች እንደሚደረጉም የኡጋንዳው ሞኒተር ጋዜጣ ቃለ አቀባዩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
መንግሥት የአባትነት ማረጋገጫ ምርመራዎች በዚህ ደረጃ ለምን እየጨመረ እንደመጣ እርግጠኛ አይደለም ተብሏል።
“አንዳንድ ወንዶች ያልወለዷቸውን ልጆች እያሳደጉና በመንከባከብ ላይ መሆኑን ተረድተዋል” ሲሉም ቃለ አቀባዩ ለኤንቲቪ ዩጋንዳ ተናግረዋል።
በርካታ የኡጋንዳ ወንዶች የአባትነት ጥያቄያቸውን ለመመለስ ዲኤንኤ (ዘረ መልን) አማራጭ ማድረጋቸውም ተነግሯል።
በዚህ ሳምንት የተደረገ ምርመራንም የጠቀሱት ቃለ አቀባዩ ከ12 የአባትነት ማረጋገጫ የዲኤንኤ ምርመራዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ወላጅ አባት ሆነው ተገኝተዋል ብለዋል።
በቡጋንዳ ግዛት የእናቶች ህብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆሴፊን ካሳቶ በበኩላቸው በእንደዚህ አይነት ምርመራዎች የሚያልፉ ቤተሰቦችን ለመደገፍ የምክር አገልግሎት ሊኖር ይገባል ሲሉ ለኤንቲቪ ኡጋንዳ ተናግረዋል።
የዲኤንኤ ምርመራዎቹ የሚካሄዱት በመዲናዋ ካምፓላ በሚገኘው የመንግሥት ላብራቶሪ ውስጥ ነው።
አንድ ጊዜ ለመመርመርም 100 ዶላር ያህል ያስወጣል።