ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት መቀየር ለምን አስፈለገ?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ በኢትዮጵያ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅ አጽድቋል።

በአዋጁ መሠረትም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ይሆናል። ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ የገለጸ ሲሆን፣ ምን አልባትም ይህ የትምህርት ተቋም በቀጣዩ በጀት ዓመት አስርት ዓመታትን ከዘለቀበት መዋቅር በተለየ ሥራ ሊጀምር ይችላል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝነትን በመተግበር ቀዳሚ ይሁን እንጂ፣ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይህንን አሰራር እንደሚተገብሩ ይጠበቃል።

ራስ ገዝ ዩነቨርሲቲ ምንድን ነው?

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ምንነትን በተመለከተ ቢቢሲ ሁለት ምሁራንን አነጋግሯል። እነሱም ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እና በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) ናቸው።

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት የሥራ ስምሪት እና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ማቋቋሚያ አዋጅ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ የቀረበው በእሳቸው አማካኝነት ነው።

በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር እና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው።

በላይ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ (autonomous) ሲሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣን እና ነጻነት እንደሚያገኙ ያመለክታሉ።

ይህም ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ያለመንግሥት ምደባ በራሱ የመግቢያ ፈተና የሚቀበል፣ የራሱን ሠራተኞች መቀጠር እና ማሰናበት የሚችል፣ ግዢን ጨምሮ የራሱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ በራሱ መምራትን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።

በራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ የሚገኘው ነጻነት ደግሞ በተቋማዊ፣ በአስተዳደራዊ እና በአካዳሚያዊ ነጻነት የሚገለጽ እንደሆነ ነገሪ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

ይህም ማለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር፣ የሰው ኃይል ምደባ፣ ቅጥር እና ደሞዝ የሲቪል ሰርቪስን ሕግ መከተል ሳይጠበቅባቸው ለራሳቸው በሚመች መልኩ እንዲያዘጋጁ አስተዳደራዊ ነጻነት እና ሥልጣንን ይሰጣል።

አካዳሚያዊ ነጻነት ደግሞ “የማሰብ ነጻነትን” የሚሰጥ ነው የሚሉት ነገሪ (ዶ/ር) “ምን ማስተማር እንዳለባቸው፤ የትኛውን ካሪኩለም መቅረጽ እንዳለባቸው፣ አዲስ የትምህርት ክፍል መክፈት ካስፈለጋቸው፣ የጥናት እና ምርምር ዘርፎችን መወሰን ካለባቸው ከየትኛውም ጫና እና ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው መሥራት መቻል ማለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችሉ ይደነግጋል።

በተጨማሪም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ገቢ ለማመንጨት በንግድ ሥራ ላይ መሰማራትን ይፈቅድላቸዋል።

በላይ (ዶ/ር) የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ገቢ ያመነጫሉ ማለት ከመንግሥት የሚመደብላቸው በጀት ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል ማለት እንዳለሆነ ያስረዳሉ።

“መንግሥት የሚመደበውን በጀት ይቀጥላል ብዬ ነው የምጠብቀው. . . ዓለም አቀፍ ልምዱም የሚያሳየው ትምህርት ቤቶች የመንግሥት ወይም የሕዝብ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት ነው 100% በጀቱን መመደብ ያለበት” በማለት ይህንን በጀት ዩኒቨርሲቲው በሚያወጣው ደንብ በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን እንደሚሰጠው አንስተዋል።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ምን ጥቅም ያስገኛል?

በላይ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ለትምህርት ጥራት ማደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያምናሉ።

የእንዲህ አይነት ዩኒቨርሲቲዎች መገለጫ ከሆኑት ነገሮች መካከል ተማሪዎችን በመግቢያ ፈተና መቀበል ነው። ይህ ደግሞ “የተሻለ አቅም ያላቸው እና ተወዳዳሪ” የሆኑ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

“ከመጀመሪያው አጥርቶ ሲቀበል ከጥራት ጋር በቀጥታ ይገናኛል ማለት ነው” ይላሉ።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ነገሪ (ዶ/ር) “ተማሪዎች ተወዳድረው ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ ስንል ተማሪዎችም ወላጆችም ከታች ጀምሮ ትኩረት ይሰጣሉ. . . ብቃትን መሠረት ስለሚያደርግም ወላጆችም ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢንቨስት ያደርጋሉ” ብለዋል።

በሌላ በኩል በላይ (ዶ/ር) ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጣቸው ሠራተኞችን የመቅጠር እና የማሰናበት ስልጣን ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ እንዳለው ያስረዳሉ።

“እስካሁን የነበረው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ፣ [ሠራተኛው] ምርታማ ባይሆንም [ዩኒቨርሲቲው] ማሰናበት የሚቸገርበት አጋጣሚ ነበር። ውጤት የሚያመጣውን ማስቀጠል የሌለውን ማሰናበት እንዲችል ይሆናል። ይሄ ከትምህርት ጥራት ጋር በጣም ይገናኛል” ብለዋል።

ነገሪ (ዶ/ር) ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ማቋቋም ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሆነ ያነሳሉ።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያላቸው መምህራንን በተሻለ ደሞዝ እና የሥራ ሁኔታ ሊይዙ የሚችሉበት ዕድልን ይፈጥርላቸዋል።

“አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንድ ቦታ የሚሠራ መምህር ኑሮን ለማሸነፍ ሌላ ሁለት ሦስት ቦታ የሚሰራበት ሁኔታ አለ። ጥናት እና ምርምር ላይ ትኩረት አያደርግም” የሚሉት ነገሪ (ዶ/ር) ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እንደብቃታቸው ክፍያ እንዲፈጽሙ እና መምህራን ጥናት እና ምርምር እንዲሁም አካዳሚያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ዕድልን ይሰጣል ብለዋል።

ይህንን ሀሳብ በላይ (ዶ/ር) ይደግፉታል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ መምህራን ከሌሎች አገራት አንጻር ዝቅተኛ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው ጠቅሰው፣ አዲሱ አሰራር ለዚህ መፍትሄ እንደሆነ አመልክተዋል።

“መምህሩ ያለውን አቅም ሌላ ቦታ እያዋለ ነው ያለው” ካሉ በኋላ “የራስ ገዝ አስተዳደር ሲመጣ ለመምህራን ተመጣጣኝ ክፍያ ይከፈላል ተብሎ ይታሰባል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ መምህራን ብቃታቸውን፣ ክህሎታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን በሙሉ እዚህ ሥራው ላይ እንዲያውሉ የሚያስችል ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

በሌላ በኩል የአስተዳደር ሠራተኞችም “ብዛታቸው ሳይሆን ብቃታቸው ነው የሚፈለገው” የሚሉት ነገሪ (ዶ/ር) በአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ሕግ ሳይሆን በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ “ትልቅ ሥልጣን ያለው” ቦርድ በሚያጣው መመሪያ እንዲተዳደሩ መፍቀዱ የተማሪዎች አገልግሎት ጥራት እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉ አክለዋል።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ “እጅግ አስቸጋሪ” ነው የሚባለውን የግዢ ሥርዓት እንደሚቀይሩ ታምኖባቸዋል።

እንደ ነገሪ (ዶ/ር) ገለጻ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ዋና ኦዲተር ኦዲት ቢደረጉም የሚኖራቸው የግዢ ሥርዓት “ማነቆ የሆነባቸውን አሰራር የሚጥሱበት እና በጥራት እና በወቅቱ መፈጸም ያለባቸውን ግዢዎች ማካሄድ ይችላሉ።”

በላይ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባለቸው አሰራር በራሳቸው መወሰን ስለማይችሉ “ለእነሱ ተገቢ ባልሆነ መመሪያ” ግዢዎችን ለመፈጸም ይገደዳሉ።

“ለምሳሌ ኮምፒውተር ለመግዛት ዋጋው በጣም ርካሽ የሆነ አወዳድሮ፣ በጣም ዝቅተኛ ጥራት ያለው ኮምፒውተር ነው መግዛት የምንችለው። ...ጥራት ያለው ኮምፒውተር መግዛት ብንፈልግ በአገሪቱ የግዢ ማዕቀፍ ነው መሄድ ያለባችሁ ስለምንባል ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖረን ያንን ማድረግ አንችልም” ይላሉ።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ ከፍተኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተወሰኑት ብቻ ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ይሸጋገራሉ።

ነገሪ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ያሉበት እና ወደፊት ሊኖራቸው የሚችለው የፋይናንስ አቅም እንዲሁም ከአመራር ጀምሮ እስከ ትምህርት ክፍል ያለው የሰው ኃይል አደረጃጀታቸው ተፈትሾ እንጂ “እንዲሁ ስለፈለጉ” ራስ ገዝ አይሆኑም ብለዋል።

በቀጣዩ በጀት ዓመት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን የሚጠበቀውና ሰባት አስርት ዓመታትን ያቆጠረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞም ራስ ገዝ እንደነበር ነገሪ (ዶ/ር) ያስታውሳሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ዩኒቨርሲተው ከተቋቋመበት ከ1942 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ደርግ መምጣት ድረስ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ነበር።

በዚህ ምክንያት እና ተቋሙ ባለው ልምድ እንዲሁም ግዝፈት፣ ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደርነትን ከሚይዙ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያው ይሆናል።

“በአገራችን አንጋፋ እና ትልቁ፣ በሰው ሃብት እና በአስፈላጊ መሠረተ ልማቶች በጣም የተደራጀ በመሆኑ [ራስ ገዝ ለመሆን] የተቀመጡ መስፈርቶችን በቅድሚያ ያሟላል ተብሎ የተቀመጠው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው” ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ “የመጀመሪያ ትውልድ” የሚሰኙት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት ይሸጋገራሉ።

ሃሮማያ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ሁለት ዓመት “እንደየዝግጅታቸው” ወደ ራስገዝነት እንደሚያድጉ ተናግረዋል።

“የሃብታሞች ዩኒቨርሲቲ”

በላይ (ዶ/ር) ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው ገቢ እያመነጩ ቢቀጥሉም ከመንግሥት የሚቀርብላቸው በጀት ሊቋረጥ እንደማይገባው ይገልጻሉ።

መንግሥት የሚሰጠውን በጀት እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ ዩኒቨርሲቲዎች ያንን ለመተካት ጥረት ሲያደርጉ የሚያመጣው ውጤት ሊቀየር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

“ውጤቱ ምንድን ነው? ሊሆን የሚችለው ገንዘብ ያላቸው ሰዎች እዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገባሉ፣ የሌላቸው ደግሞ መግባት አይችሉም...ይህንን ደግሞ መንግሥትም የሚፈልገው አይመስለኝም” ካሉ በኋላ መንግሥት “ሙሉ በጀት” ማቅረቡን መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ያ ካልሆነ ዩኒቨርሲቲዎች የጎደለውን ገንዘብ ለማካካስ በሚያደርጉት ጥረት ገንዘብ ላላቸው ቅድሚያ ሊሰጡ እና ይህም ፍትሃዊነትን ሊያዛባ ይችላል ብለዋል።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ለማቋቋም የሚያስችለው አዋጅ በጸደቀበት ወቅት ተመሳሳይ ስጋታቸውን ያንጸባረቁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነበሩ።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች መክፈል የማይችሉ ተማሪዎችን በማግለል “የመደብ ልዩነት ይፈጥራሉ” እና “የሃብታሞች ዩኒቨርሲቲ” ይሆናሉ የሚል ስጋት ተንጸባርቆ ነበር።

ነገሪ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ አስተያየት ሲሰጡ፣ በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች “ብቃት እንጂ ሃብት ቦታ የለውም” ብለዋል።

“የሃብታም ልጆች ስለሆኑ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ የሚል ድምዳሜ የለም። ቅድሚያ የሚሰጠው ለጥራት” ነው ካሉ በኋላ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ዓላማ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ብቃት ላላቸውን ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት ዕድል መስጠት ነው ሲሉ አክለዋል።

ጨምረውም በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል ውድድር በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ያላቸውን ዩኒቨርሲቲዎች የመፍጠር ዓላማ መሆኑን ገልጸው፣ የሁሉም ነገር ማዕከል የተማሪዎች ብቃት እንደሆነ አንስተዋል።

አዋጁ ከፍለው መማር የማይችሉ ግን ለእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ የሆኑ ተማሪዎችን ለማስተማር “መንግሥት በጀት እንዲሰጥ የሚያስገድድ” አንቀጽ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

አዋጁ “አካታችነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን” የማረጋገጥ ግዴታን መንግሥት ላይ እንደጣለም ተናግረዋል።