ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶክ ተጠቃሚዎቹን ሱስ የሚያስይዝ ገጽታውን ባለመለወጡ ተከሰሰ
ቲክቶክ ተጠቃሚዎቹን ሱስ በሚያስይዝ ገጽታው ምክንያት የአውሮፓ ኅብረትን የበይነ መረብ ሕግ ተላልፏል ተብሎ ተከሰሰ።
መተግበሪያው ሱስ የሚያስይዝ ገጽታውን እንዲያስተካክል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም እንዳላሻሻለ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ቲክቶክ ሱስ አስያዥ ገጽታውን ካልለወጠ የማኅበራዊ ሚዲያው አስተዳዳሪ ባይትዳንስ ከዓለም አቀፍ ገቢው ላይ የ6% ቅጣት እንደሚጣልበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት የበይነ መብት ተቆጣጣሪ ካቀረባቸው ክሶች መካከል ቲክቶክ ተጠቃሚዎቹ ያለማቋረጥ 'ስክሮል' እንዲያደርጉ የዘረጋው መዋቅር ይገኝበታል።
ለተጠቃሚዎች መረጃ የሚጠቁምበት ወይም 'ኖቲፊኬሽን' የሚሰጥበት መንገድ እና የእያንዳንዱን ተጠቃሚ ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ ይዘቶችን መግፋቱም በክሱ ተካቷል።
ቲክቶክ በመላው ዓለም ታዋቂ መተግበሪያ የሆነው ተጠቃሚዎቹን በተሻለ መንገድ በመገንዘቡ እንደሆነ ተገልጿል።
የአሜሪካ መንግሥት ቲክቶክ ሳንሱር ያደርጋል በሚል ታሪፍ ለመጣል መዛቱን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።
የአውሮፓ ኅብረት የበይነ መረብ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ለአንድ ዓመት ያህል 'Digital Services Act ወይም DSA' በተባለ ድንጋጌ ሥር ቲክቶክ ላይ ምርመራ ሲያካሂድ እንደቆየ የሮይተርስ ዘገባ ይጠቁማል።
ምርመራው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሕገ ወጥ እና ጎጂ ይዘቶችን ለመግታት ያለመ ነበር።
የቲክቶክ ቃል አቀባይ "የኮሚሽኑ ምርመራ የመጀመሪያ ዙር ውጤት ሐሰተኛ ነው፤ ተቋሙን አይወክልም። የምርመራውን ውጤት ለመገዳደር አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የበይነ መረብ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን እንዳለው፤ ቲክቶክ ተጠቃሚዎቹ ከመተግበሪያው እንዳይርቁ በሚያበረታታ መንገድ አዳዲስ ይዘቶችን አከታትሎ ይለቅቃል።
ሰዎች ምን ያህል መተግበሪያውን እየተጠቀሙ እንደሆነ በማያስተውሉበት ሁኔታ ሱስ አስያዥ ገጽታ እንዳለውም ገልጿል።
የቲክቶክ ሱስ አስያዥ ገጽታ ሕጻናትን ጨምሮ በአዋቂ ተጠቃሚዎቹ አካላዊ እና አእምሯዊ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ችላ እንደተባለ ኮሚሽኑ ሳይጠቅስ አላለፈም።
በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር የሚችሉበት አሠራር ቲክቶክ ሳይዘረጋ መቅረቱን የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ሄና ቪርከኑን "ታዳጊዎችን ለመጠበቅ ሲባል ቲክቶክ አሠራሩን ይለውጣል ብለን እንጠብቃለን" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ቲክቶክ ማብቂያ የሌለው 'ስክሮል' ማድረግን ለመቆጣጠር እና ወላጆች ለልጆቻቸው የስክሪን ዕይታ ገደብ የሚያስቀምጡበትን መንገድ ለማመቻቸት እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።
አምና የፌስቡክ እና ኢንስታግራም አስተዳዳሪው ሜታ የአውሮፓ ኅብረትን የበይነ መረብ ሕግ ተላልፏል ተብሎ ተከስሶ እንደነበር ይታወሳል።
የኅብረቱ ኮሚሽን ስናፕቻት፣ ዩትዩብ፣ አፕል እና ጉግል ታዳጊዎች ሕገ ወጥ እና ጎጂ ይዘት እንዳይመለከቱ የሚወስዱትን እርምጃ ይፋ እንዲያደርጉ እንደሚጠይቅ ሮይተርስ ዘግቧል።
ፈረንሳይ እና ስፔንን ጨምሮ የአውሮፓ አገራት ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማገድ ዕቅድ አውጥተዋል።
አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ በማገድ የመጀመሪያዋ አገር መሆኗ አይዘነጋም።
የአውሮፓ ኅብረት ሕግ አውጪ አሌክሳንድራ ጊስ "አብዛኞቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ሱስ አስያዥ ገጽታቸውን በመጠቀም በርካቶችን ይበዘብዛሉ። ማስታወቂያ በመግፋትም ትርፍ ያጋብሳሉ። ይህም ለሕጻናት እና ወጣቶች ጤና አደገኛ ነው" ብለዋል።