የወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲን 13 ምሥሎች ይፋ ከተደረጉ በኋላ መሰረዛቸው ጥያቄ አስነሳ

የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ አድርጓቸው ከነበሩ የጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነዶች ውስጥ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምሥልን ጨምሮ 13 ምሥሎችን ከድረ ገጹ መሰረዙ ተገለጸ።

መሥሪያ ቤቱ በኤፕስቲን ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሰዎች በደረሰው ቅሬታ መሠረት ምሥሎቹን መሠረዙን ምክትል ዐቃቤ ሕግ ቶድ ብላንኬ ተናግረዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ የሰረዘው የትራምፕ ምሥል፤ ማንነታቸው መደበቅ ሲገባው ምሥላቸው እንዲጠፋ ያልተደረገ ሴቶችን ፎቶ ያካተተ እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም ምሥሎቹ የተሰረዙት በትራምፕ ምክንያት ነው መባሉን አስተባብለዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ይፋ ካደረጋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች መካከል የሰረዘው 13 ምሥሎችን ነው።

ዴሞክራቶች የምሥሎቹ መሰረዝ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ዋና ዐቃቤ ሕግ ፖም ባንዲን "ምን ለመደበቅ እየሞከራችሁ ነው?" ሲሉም ጠይቀዋል።

የኒው ዮርክ ዳኛ ትራምፕ ያሉበት ምሥል "ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ደኅንነት አስጊ ነው" ማለቱን ተከትሎ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ እርምጃውን ወስዷል።

ምሥሉን በጊዜያዊነት ከድረ ገጹ አግዶ ምርመራ ካደረገ በኋላ ከምሥሎቹ አንደኛው በድጋሚ በድረ ገጹ እንዲወጣ ወስኗል።

"ምርመራ ካደረግን በኋላ ምሥሉ ላይ በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን ስላመንን ፎቶውን በድጋሚ አውጥተናል" ሲል የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ውሳኔውን አብራርቷል።

የተቀሩት ምሥሎች ግን ከተሰረዙ በኋላ በድረ ገጹ በድጋሚ አልወጡም።

ምክትል ዐቃቤ ሕግ ቶድ ብላንኬ ምሥሉ የተሰረዘው በትራምፕ ምክንያት ነው መባሉ ግን "አስቂኝ ነው" ብለዋል።

"ይፋ የተደረጉ ብዙ የትራምፕ እና ኤፕስቲን ምሥሎች አሉ። አንድ ፎቶ ላይ ብቻ ትራምፕ ስላለ ከድረ ገጽ አውርደውታል መባሉ አስቂኝ ነው" ሲሉም አክለዋል።

የኒው ዮርክ ዳኛ፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ማሳሰባቸውን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ትራምፕ በፎቶ ላይ ከኤፕስቲን ጋር ቢታዩም ስህተት አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል። በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎችም ትራምፕን አልከሰሱም።

በእነዚህ ምሥሎች ላይ መታየት ጥፋት መፈጸምን የሚያመላክት አይደለም።

የፍትሕ መሥሪያ ቤት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ሁሉንም የኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ ባለማድረጉ እየተወቀሰ ነው።

የኮንግረስን ውሳኔ ተከትሎ ከኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ምሥሎች፣ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እና የምርመራ ሰነዶች ይፋ ወጥተዋል።

ሰነዶቹ ይፋ እንዲደረጉ ጫና ያደረጉት የኮንግረስ አባል ቶማስ ማሲ እንዳሉት፤ የትራምፕ አስተዳደር ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ፍትሕ ለማስፈን ዳተኛ ሆኗል።

ከተሰረዙት ምሥሎች አንደኛው ኤፕስቲን ቤት ባለ መሳቢያ ውስጥ የትራምፕ እና የኤፕስቲን እንዲሁም የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ እና የኤፕስቲን አጋር ማክስዌል ፎቶዎችን ያሳያል።

አንድ የማሳጅ አልጋ ያለበት ክፍል ውስጥ ግድግዳ ላይ የተለጠፉ የሴቶች እርቃን ምሥሎች ይታያሉ።

የሴቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ምሥላቸው እንዲደበዝዝ ተደርጓል።

የአሜሪካ መንግሥት የኤፕስቲን ሰነዶችን ይፋ ያደረገበት መንገድ ላይ ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱ ባለበት ወቅት የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ አድርጓቸው የነበሩ ምሥሎችን ከድረ ገጹ ማውረዱ ነገሮችን አባብሷል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤት በበኩ የኮንግረስን ውሳኔ አክብሮ ሰነዶቹን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ከጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ይፋ የተደረጉበት መንገድ እንዳሰጋቸው ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎችም ተናግረዋል።

የሚወጡት ሰነዶች በከፊል ይዘታቸው የሚሸፈን ከሆነ ለሴራ ትንታኔ እንደሚዳርግ የሕግ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤት እንዳለው፤ ከሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ እና ከአካላዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ እንዲሁም "የፌደራል መንግሥት ምርመራን ሊያሰናክሉ የሚችሉ" አልያም "የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቀም የሚጎዱ" የተባሉ ይዘቶች ይፋ ከተደረጉት ሰነዶች ላይ ተቀንሰዋል።