ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ዴሞክራቶች ከዚህ ቀደም ያልታዩ የጄፍሪ ኤፕስቲን ፎቶዎችን ይፋ አደረጉ
በአሜሪካ ኮንግረስ የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑ ዴሞክራቶች፤ የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን መኖሪያን የሚያሳዩ እና ከዚህ ቀደም ያልወጡ ፎቶዎችን ይፋ አደረጉ።
ይፋ ከተደረጉት ቪድዮ እና ፎቶዎች መካከል 'ቨርጂን አይላንድስ' ተብሎ በሚጠራው የአሜሪካ የደሴት ግዛት በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መኝታ ቤቶችን የሚያሳዩ ይገኙበታል። የወንድ ፊትን የሚያሳይ ቅርጽ ግድግዳ ላይ የተሰቀለበት አንድ ክፍል እንዲሁም ስሞች የተጻፉበት የቤት ስልክም በወጡት ፎቶዎች ላይ ይታያሉ።
ከአምስት ዓመት በፊት በ2020 የተነሱ ፎቶዎች፤ የጥርስ ሕክምና ወንበር የሚመስል መቀመጫ እና ጥቁር ሰሌዳ የተሰቀለበት አንድ ክፍል አሳይተዋል። በጥቁር ሰሌዳው ላይ "እውነት"፣ "ማታለል" እና "ኃይል" የሚሉ ቃላት ተጽፈውበታል። ፎቶው የወጣው አንዳንድ ቃላት እንዲሸፈኑ ተደርገው ነው።
ኮሚቴው ረቡዕ ዕለት በሁለተኛ ዙር 200 ገደማ ፎቶዎች እና ቪድዮችን ለቅቋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ በመጀመሪያው ዙር በተለቀቁት ፎቶዎች ላይ የሚገኘውን ክፍል እና ወንበር በቅርበት የሚያሳዩ ናቸው።
በቤቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሻምፑ እና ኮንዲሽነር እንዲሁም ሀውልቶች እና ሥዕሎችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን ተለቅቀዋል። ኤፒስቲን እና በእስር ላይ ስለምትገኘው አጋሩ ግሌን ማክስዌል የቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክስርቲያን መሪ ፖፕ ጆን ፖል ሁለተኛን ሲያገኙ የተነሳ ፎቶም ይፋ ተደርጓል።
የፎቶዎቹ የተነሱት ኤፕስቲን ከሞተ አንድ ዓመት በኋላ በ2020 እንደሆነ በምሥሎቹ ላይ የተቀመጠው ሜታዳታ ጠቁሟል።
በኮሚቴው የዴሞክራቶች መሪ የሆኑት ሮበርት ጋርሺያ ባወጡት መግለጫ፤ ፎቶዎቹ እና ቪድዮው በጥቅሉ ሲታዩ የኤፕስቲን ዓለም ያለውን "የሚረብሽ ገጽታ" እንደሚያሳዩ ገልጸዋል። እንዲለቀቁ የተደረገውም "የሕዝብ ግልጽነትን ለማረጋገጥ" እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መንግሥት ከግለሰቡ ጋር በተያያዘ የያዛቸውን ሰነዶች እንዲለቅቅ የሚያዝ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል። ይህ ትዕዛዝ ሕግ ሆኖ መውጣቱ የሰነዶቹን መለቀቅ በተመለከተ ለወራት ሲደረግ የነበረውን ፍትጊያ አቅጣጫ ቀይሮታል።
በርካታ ተጎጂዎች፤ 'ሊትል ሴንት ጄምስ' ወደ ሚጠራው እና ኤፕስቲን በአውሮፓውያኑ 1998 ወደ ገዛው ደሴት እንደተወሰዱ እና ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ይናገራሉ።
አሁን የተለቀቁት ፎቶዎች የተገኙት ከቨርጂን አይላንድ አቃቤ ሕግ እንደሆነ የዴሞክራቶች የቁጥጥር ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ፎቶዎቹ የተላኩት፤ ስለ ኤፕስቲን እና ግሌን ማክስዌል ለሚደረገው ምርመራ መረጃዎች እንዲላኩ ከሁለት ሳምንት በፊት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት መሆኑንም ገልጿል።
በኮሚቴው የዴሞክራቶች መሪው ጋርሺያ፤ "እነዚህ አዳዲስ ምሥሎች የጄፍሪ ኤፕስቲን እና የደሴቱ ዓለም ያላቸውን የሚረብሽ ገጽታ የሚያሳዩ ናቸው" ብለዋል።
እነዚህን ፎቶዎች እና ቪድዮዎች እየለቀቅን ያለነው በምርመራችን ውስጥ የሕዝብ ግልጽነትን ለማረጋገጥ እና ትናንሽ ነጥቦችን በማጣመር የኤፕስቲንን አሰቃቂ ወንጀሎች ሙሉ ምሥል ለማግኘት ነው" ሲሉም አክለዋል። "የኤፕስቲንን አሰቃቂ ወንጀሎች ሙሉ ምሥል እስከምናሳይ ድረስ መታገላችንን አናቆምም" ሲሉም አቋማቸውን አስታውቀዋል።
ግራሺያ እንደሚናገሩት በኤፕስቲን መዝገብ ውስጥ ከግዙፉ የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋም ጄፒ ሞርጋን እና ደች ባንክ ጋር የተያያዙ መረጃዎች የተገኙ ሲሆን "በመጪዎቹ ቀናት" ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
'ሊትል ሴንት ጄምስ' ኤፕስቲን በቨርጂን አይላንድስ ከገዛቸው ሁለት ደሴቶች አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም የአካባቢው ባለሥልጣናት "በርካታ ታዳጊ ሴቶች እና ህጻናት" ወደ ሁለቱ ደሴቶች እንደሚወሰዱ፣ እንደሚደፈሩ እና ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው በመጥቀስ ውንጀላ አቅርበው ነበር።
ይህንን ተከትሎም በ2022 የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ105 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ገንዘብ ድርድር ጉዳዩ እንዲቋጭ አድርጎ ነበር።