በሺዎች የሚቆጠሩ የወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ መደረግ እና ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ስጋት

ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ይፋ የተደረጉበት መንገድ እንዳሰጋቸው ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ተናግረዋል።

የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ሰነዶቹን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ተወስኗል። ከሰነዶቹ የተወሰኑት ከዚህ ቀደም ይፋ ሲደረጉ በከፊል ለሕዝብ ያለተገለጹ ይዘቶች ያላቸው ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ከዚህ ቀደም ይፋ አልወጡም።

የሚወጡት ሰነዶች በከፊል ይዘታቸው የሚሸፈን ከሆነ ለሴራ ትንታኔ እንደሚዳርግ የሕግ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

ምክትል ዐቃቤ ሕግ አንቶኒ ቶድ እንዳሉት ሰነዶች ይፋ በተደረጉበት ዕለት ከ1,200 በላይ በኤፕስቲን ብዝበዛ የደረሰባቸው ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዳይጎዱ ማንነታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች እንዳይወጡ ተወስኗል።

ኤፕስቲን ከአጋሩ ማክስዌል ጋር በዳውኒንግ ስትሪት ሳሉ የሚያሳይ ምሥልን ጨምሮ ሌሎችም መረጃዎች ይፋ ወጥተዋል።

ኤፕስቲን በማራ-ላ-ጎ የ14 ዓመት ታዳጊን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር እንዳስተዋወቀ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ምሥልም እንደተገኘ የሚጠቁሙ ሰነዶች ይገኙበታል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው ይፋ ከተደረጉት ሰነዶች ቢያንስ 15 ያህሉ ከፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ወርደዋል።

የቢል ክሊንተንን ምሥል የሚያሳየው ሰነድ እና ቁም ሳጥን ውስጥ የትራምፕ፣ ኤፕስቲን እና ማክስዌል ምሥል የሚገኝበት ሰነድ አልተገኙም።

የማሳጅ ጠረጴዛ እና እርቃናቸውን ያሉ ሴቶች ምሥል የሚታይበት ክፍል ሰነድም በድረ ገጹ አይታይም።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ "በሕግ መሠረት ምሥሎች እና ሰነዶች እየታዩ ይፋ የሚደረጉት ይወሰናሉ" ብሏል።

ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር ስላላቸው ግንኙነት የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል። ክሊንተን ስለ ኤፕስቲን የወሲብ ንግድ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ሚክ ጃገር፣ ማይክል ጃክሰን፣ ዳያና ሮስ እና ፒተር ማንደልሰንን ጨምሮ የሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ምሥሎች ተገኝተዋል።

በምሥል ላይ መታየት ወይም የስም በሰነድ ውስጥ መካተት ወንጀል መፈጸምን አያመለክትም።

ከዚህ ቀደም ከኤፕስቲን ጋር በተያያዙ ሰነዶች ስማቸው የተገኘ ሰዎች ምንም አለማጥፋታቸውን ገልጸዋል።

ከሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ እና ከአካላዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ እንዲሁም "የፌደራል መንግሥት ምርመራን ሊያሰናክሉ የሚችሉ" አልያም "የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቀም የሚጎዱ" የተባሉ ይዘቶች ይፋ ከተደረጉት ሰነዶች ላይ ተቀንሰዋል።

የፖለቲከኞችን ስም ከሰነዱ ላይ እንዳልፋቀ የገለጸው የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ የተቀነሱ መረጃዎች "ሕግን የተከተሉ ናቸው" ብሏል።

"ፖለቲከኞቹ ተጎጂዎች ካልሆኑ በስተቀር ስማቸው ከሰነዶቹ እንዲወጣ አይደረግም" ሲልም አክሏል።

ጠበቃው ጆን ዴይ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ይፋ ከተደረጉት ሰነዶች ውስጥ ይዘታቸው የተሸፈነ በርካታ ናቸው።

ይዘቶች መቀነሳቸው "ለሴራ ትንታኔ ያጋልጣል" ብለዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ የቀነሳቸውን ይዘቶች በ15 ቀናት ውስጥ ለኮንግረስ ማሳወቅ ይጠበቅበታል።

በ14 ዓመቷ በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባት ማኒና ላካርዳ እንዳለችው ጥቃት የደረሰባቸው እና በማገገም ላይ ያሉ ሰዎች የኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ የሚደረጉበትን ቀን ሲጠባበቁ ነበር።

"አሁንም መረጃዎችን መቀነሳቸው አሳዝኖናል። ጥቃት የደረሰባቸወ ሰዎች የተቀሩት ሰነዶች ይፋ በወጡበት መንገድ ላይ ደስተኛ አይደሉም። አሁንም የተቀነሰ መረጃ መኖሩ ጥያቄ ያስነሳል" ብላለች።

ሌላዋ በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባቸው ሊዝ ስቴን "የኤፕስቲን ፋይሎንን ይፋ የማድረግ መርሕን" የጣሰ ነው ብላለች።

"መረጃው ቀስ በቀስ መውጣቱ በአውድ ውስጥ ትርጉም እንዳይሰጥ ያደርጋል። ስለተፈጸመው ወንጀል ያለው መረጃ በአጠቃላይ እንዲወጣ እንፈልጋለን" ብላለች።

በዩናይትድ ኪንግደም የሰብአዊ መብት ጠበቃዋ ሔለን ኬኔዲ "ተጨማሪ ጥያቄዎች በሕዝብ ላይ እንዲፈጠር መደረግ የለበትም" ብለዋል።

አብዛኞቹ በኤፕስቲን ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ሰነዶቹ ይፋ እንዲወጡ እንደሚፈልጉም አክለዋል።