ዩናይትድ ኪንግደም የተዘረፉትን የጋና 'የአክሊል ጌጣጌጦች' በብድር ልትመልስ ነው

እንግሊዝ አንዳንድ የጋና "የአክሊል ጌጣጌጦችን" ከአሳንቴ ንጉስ ፍርድ ቤት ከዘረፈቻቸው 150 ዓመታት በኋላ በብድር ለመመለስ ወስናለች።

በረዥም ጊዜ የብድር ስምምነት ከሚመለሱት 32 ዕቃዎች መካከል የወርቅ ቱቦ አንዱ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (ቪ ኤንድ ኤ) 17 ቅርሶችን ሲያበድር 15ቱ ደግሞ ከብሪቲሽ ሙዚየም የሚሰጡ ናቸው።

ከበርካታ ትውልዶች ቁጣ በኋላ “አዲስ የባሕል ትብብር ስሜት” እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ የጋና ዋና ተደራዳሪ ገልጸዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አንዳንድ ሙዚየሞች ክርክር ያለባቸውን ቅርሶች በቋሚነት እንዳይመልሱ በሕግ ተከልክለዋል።

እንደዚህ ያሉ የብድር ስምምነቶች ቅርሶችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንደ አማራጭ መንገድ ይወሰዳል።

ቅርሶቹ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ የሚያነሱ አገሮች ግን የብድር ስምምነቱ እንግሊዝ ቅርሶቹ ባለቤት እንደሆነች እንደተቀበሉ ለማመልከት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ብለው ይፈራሉ።

የቪ ኤንድ ኤ ዳይሬክተር የሆኑት ትሪስትራም ሃንት የፍርድ ቤት ወርቅ ዕቃዎች "ከእኛ ዘውድ ጌጣጌጥ" ጋር እኩል ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በብድር ከሚሰጡት አብዛኛዎቹ ቅርሶች የተወሰዱት በ19ኛው ክፍለ ዘመን በብሪታንያ እና በአሳንቴ ጦርነት ወቅት ነው።

ሰይፍ እና የንጉሱን ነፍስ የማንጻት ኃላፊነት ባላቸው ባለስልጣናት የሚለበሱ የወርቅ ኒሻኖች ይገኙባቸዋል።

ሃንት አክለውም ሙዚየሞች “በጦርነት እና በወታደራዊ ዘመቻዎች የተዘረፉ ቅርሶችን በፍትሃዊነት እንዴት ማካፈል እንደምንችል የማሰብ ኃላፊነት አለብን” ብለዋል።

"እንዲህ አይነት ሽርክና እና ልውውጥ ከፈጠርን ሙዚየሞቻችን የሚዘጉ አይመስለኝም።"

አዲሱ የባህል ሽርክና "በኋላ በር የመመለስ አይደለም" በማለት አጥብቀው ተናግረዋል። ይህም በቋሚነት ንብረቶቹን ለጋና የሚመልስበት መንገድ አይደለም ማለት ነው።

የሦስት ዓመት የብድር ስምምነቶች (ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት የማራዘም ዕድለም አለው) ከጋና መንግስት ጋር የተደረገ ሳይሆን ከአሁኑ የአሳንቴ ንጉስ አሳንቴሄን ዳግማዊ ኦቶምፎ ኦሴይ ቱቱ የተደረሰ ነው።

ግዛቱ አሁን የጋና የዘመናዊ ዲሞክራሲ አካል ቢሆንም አሳንቴሄኔ አሁንም ተደማጭነት ያለው ሥርዓት ነው።

ቅርሶቹ የአሳንቴሄንን የብር ኢዮቤልዩ በሚከበርበት በአሳንቴ ክልል ዋና ከተማ ኩማሲ በሚገኘው በማኒሺያ ቤተመንግስት ሙዚየም ለዕይታ ይቀርባሉ።

የአሳንቴ የወርቅ ቅርሶች የአሳንቴ ንጉሣዊ መንግሥት ምልክት ሲሆኑ ከቀድሞው የአሳንቴ ነገሥታት መንፈስ ጋር የተሳሰሩ እንደሆነ ይታመናል።

ለጋናም ከቤኒን ብሮንዝ ጋር የሚወዳደር ጠቀሜታ አላቸው። ቤኒን ብሮንዞች በዘመናዊቷ ደቡብ ናይጄሪያ ውስጥ ከቤኒን ቤተ መንግስት በብሪታንያ የተዘረፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቅርጻ ቅርጾች እና ሐውልቶች ናቸው። ናይጄሪያ እንዚህ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለአስርተ ዓመታት ስትጠይቅ ቆይታለች።

የጋና የባህል ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ናና ኦፎሪያታ አዪም ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ጠቀሜታም አላቸው:: የአገሪቱ ነፍስ አካል ናቸው:: ወደ ራሳችን የምንመለስበት ቅርስ ነው::"

ብድሩ በዘረፋው ዓመታዊ በዓል ላይ መሆኑ "ጥሩ መሠረት ከመሆን ባለፈ ለተፈጠረው ሁከት የፈውስ እና የመታሰቢያ ምልክት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ሙዚየሞች ከጋና የተወሰዱ በርካታ ቅርሶችን ይዘዋል። በጣም ዝነኛ ከሆኑት መካከል የአሳንቴ አካል ከሆኑት አንዱ የሆነውን በሰው ፊት ቅርጽ የተሠራው ወርቅ ይገኝበታል።

አሳንቴዎች በአንድ ወቅት በምዕራብ አፍሪካ ከነበሩት ግዛቶች መካከል በጣም ኃይለኛ እና ጠንካራ ከሆኑት አንዱን ከመመስረት ባለፈ ወርቅ እና ጨርቃ ጨርቅ ንግድ ይሳተፉ ነበር።