የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተጠረጠሩትን አማካሪ ከሥልጣን አነሱ

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ዶክትሬት ድግሪያቸው ሐሰተኛ ነው በሚል የተጠረጠሩትን የምጣኔ ሃብት አማካሪን ከሥራ አሰናበቱ።

ታቢ ሌኦካ በዶክትሬት ድግሪ ከለንድን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተመርቂያለሁ ቢሉም የቢዝነስ ደይሊ እና ደይሊ ማቭሪክ ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ዲግሪን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻሉም።

ቢቢሲ በበኩሉ ሌኦካ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ስለመመረቃቸው ትምህርት ቤቱን ጠይቋል። ትልቅ ስም ያለው ዩኒቨርሲቲም አማካሪዋ ከዩኒቨርሲተው አለመመረቃቸውን አረጋግጧል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሌኦካ ትልቅ ስም ካላቸው ሁለት ኩባንያዎች የቦርድ አባልነት እራሳቸውን አግልለዋል።

ከኩባንያዎቹ መካከል አንዱ የሆነው አንግሎ አሜሪካን ፕላቲኒየም ሌኦካ በጤና እና የትምህርት ማስረጃቸውን በተመለከተ እየተነሱባቸው ባለው ጥያቄ ከቦርድ አባልነታቸው ተነስተዋል ብሏል።

ሌላኛው የቴሌኮም ኩባንያ ኤምቲኤን ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።

የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌኛ ከትምህርት ማስረጃቸው ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄ ምክንያት ሌኦካ “ከፕሬዝዳንቱ የምጣሄ ሃብት አማካሪ ምክርት ቤት አባልነት በአስቸኳይ እንደተነሱ ተነግሯቸዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፕሬዝዳንቱ የምጣኔ ሃብት አማካሪ ካውንስል ለደቡብ አፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅ የማማከር ሥራን ይሠራል።

ቀደም ሲል የደቡብ አፍሪካው ዴይሊ ማቭሪክ ሌኦካ የትምህርት ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ሲጠይቃቸው አማካሪዋ በጤና እና በሥራ ምክንያት የትምህርት ማስረጃቸውን የሚያቀርቡበት ጊዜ እንደሌላቸው መልስ መስጠታቸውን ዘግቦ ነበር።

“አሁን አገር ውስጥ አይደለሁም። ግላኮማ ስላለብኝ ማያሚ የዓይን ሆስፒታል ነው የምገኘው፤ አሁን ላይ የቀኝ ዓይኔን ብርሃን አጥቻለሁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ሌኦካ የትምህርት ማስረጃ ሐሰተኛ ነው ከተባለ በኋላ የቀረበባቸውን ክስ ለመከላከል አንድ የራዲዮ ጣቢያ ላይ ቀርበው ነበር።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ስለማቅረባቸው ጥያቄ ሲቀርብላቸው፤ “ይህ እውነት አይደለም” ከማለት ውጪ የዶክትሬት ድግሪያቸውን ትክክለኛነት የሚያረጋገጥ ማስረጃ ማቅረብ ተስኗቸዋል።